የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -11

ቍጣን ለማብረድ

ቍጣ የጤና ፣ የመንፈሳዊነት እንቅፋት ነውና መወገድ አለበት ። የምድር ዘመናችንን ውብ ለማድረግ ፣ ባለን ነገር ተረጋግተን ለመኖር ቍጣን መተው ይገባል ። ቍጣን ለመተው የሚረዱ ነገሮች ምንድናቸው?

ፍቅር

ፍቅር ከጠባያቱ የመጀመሪያው ይታገሣል ። ለሚወደው ሰው ዕድል ይሰጣል ። ሁሉንም ሰው እንደ ወንድምና እኅት ስለሚመለከት ቶሎ ለመለያየት አይቸኩልም ። በሌሎች መለወጥ ተስፋ ያደርጋል ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው ዓላማና ትምህርት አለው ። በሕይወት ጎዳና ውስጥ እያሳለፈ ማስተማር የሚችልም አምላክ ነው ። ሕይወታችን በፍቅር ሲቃኝ ክፉ ለመሆንና ለመለየት አቅም እናጣለን ። የሚያፈቅር ሰው ከሰውዬው በደል ፍቅሩ ይበልጥበታል ። ሰውን የምናስተምረው ከመራቅ ይልቅ በፍቅር በመቅረብ ነው ።

ትዕግሥት

በሁሉ ቦታና በሁሉ ጊዜ ትዕግሥት ያስፈልጋል ። የግላችን ዓለም የለችንምና እንደ ሌሎቹ ወረፋ መጠበቅ ፣ ተራችን እስኪደርስ መታገሥ ይገባናል ። ሁልጊዜ ማግኘትም ተገቢ አይደለም ፣ ሌሎች ሲያገኙ ማየትም ያስደስታል ። የሰው ትዕግሥት እየተሟጠጠ ያለበት ዘመን ላይ ነን ። ሰዎች የትራፊክ መብራትን ለደቂቃዎች መታገሥ ባለ መቻል ዘላቂ ችግር ውስጥ ይገባሉ ። ታግሦ ምክር መስማት እየተሳነን ነው ። ማኅበራዊ ሚዲያ የሰውን ትዕግሥት እየወሰደው ነው ። የአንድ ደቂቃ መልእክት መስማት የለመደ ትውልድ አንድ ሰዓት የመማር ትዕግሥት እያጣ ይመጣል ። አንድ አንቀጽ ማንበብ የለመደ ወገን አንድ መጽሐፍ አንብብ ብለው ቢሰጡት የሚሞት ይመስለዋል ። ማኅበራዊ ሚዲያ ትዕግሥትን የሚያሳጣ ሲሆን ሕይወትንም እንድንሰለች ያደርጋል ። ለፍላፊ እንጂ አድማጭ አያደርግም ። ግልብ እውቀቶችን ያመጣል እንጂ የተደላደለ ጥበብን አያስገኝም ። መታገሥ ቍጣን የምናሸንፍበት መንገድ ነው ።

አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ

በተቆጣን ጊዜ አለመናገር ፣ ካስቆጣን አካባቢ መራቅ ፣ የእግር ጉዞ ማድረግ ፣ ውኃ መጠጣት ፣ አየር ወደ ውስጣችን በደንብ ማስገባትና ማስወጣት ጊዜያዊ መባረድን ያመጣል ። የምንወደው ሰው ጋ መገናኘት ቍጣን ይቀንሳል ። ይልቁንም የተቆጣ ሰው አጠገባችን ካለ ማብረድ አለብን ። የምናበርደውም መልስ ባለ መስጠት ፣ ዘወር በማለት ፣ ትክክል ነህ በማለት ፣ እስኪበርድ ድረስ ይቅርታ በመጠየቅ መሆን አለበት ። አሊያ ሁላችንንም የሚጎዳ ውሳኔ ይከሰታል ። ሰውን ከቍጣ ማብረድ ትልቅ ሰብእና ነው ። ያንን ሰው ከሲኦል እሳት ውስጥ እንደ ማውጣት ነው ።

ዓለሙን መረዳት

ቍጣን ለማሸነፍ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ የምንኖርበትን ዓለም መረዳት ነው ። የምንኖረው ጉድለት ገንዘቡ በሆነ ዓለም ላይ ነው ። እንኳን ለእኛ ለምድር ገዥዎችና ባለጠጎችም አልሞላም ። የዓለም ቁንጮ ላይ የወጡት ሁሉ ደስታን እንዳጡት እየነገሩን ነው ። የእነርሱን ቦታ ስንመኝ ደስታ ለማጣት እየከጀልን እንደሆነ አልተረዳንም ። አንድ ቀን የምንለው ብርሃንና ጨለማ ተደምረው እንደሆነ ሁሉ ሕይወትም ደስታና ኀዘን ነው ። ሁሉም ነገር ያለውና ሁሉም ነገር የሌለው ሰው በዓለም ላይ የለም ። ባለንና በሌለን ነገር መደሰትን መልመድ አለብን ።

አስለምደዋለሁ እግሬን ያለ ጫማ
እንዳጌጡ መኖር አይገኝምና

አዲስ ነገር የለም

የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነው ። በዚህ መንገድ ላይ የምናልፍ ብቸኛ ሰዎች አይደለንም ። ብዙዎች አልፈውበታል ። የእግራቸው ዱካ ፣ የጣታቸው አሻራ እንኳ አልተገኘም ። እስካለን ድረስ ብዙዎችን እናስከትላለን ። መከራችን ግን አጋር የለውም ። ስንሞት የሚያስታውሱን ጥቂቶች ብቻ ናቸው ። ዛሬ የምናያቸው ክፋቶች ጥንትም ነበሩ ፣ አዲስ ኃጢአትም የለም ። ነግቶ አዲስ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዓለሙ ሳይንቀን ቀድመን ልንንቀው ይገባል ። ያን ጊዜ መደነቅን እያቆምን “የምድር ዘመኔን በሰላም አስፈጽመኝ” እያልን መጸለይ እንጀምራለን ። የትላንትናዎቹ አልፈው የዛሬዎቹን እናያለን ፣ የዛሬዎቹም ነገ ላይ ያልፋሉ ። ሰጪው ለማኝ ፣ ገዥው እስረኛ ይሆናል ። ቆንጆው በበሽታ ይጎዳል ። የመልክ አድራሻ ፍጹም ይጠፋል ። መለሎው እንደ ሸማ ተጠቅልሎ ይቀመጣል ። ሯጩም የአልጋ እስረኛ ይሆናል ። ዛሬ ብሩህ የሆነው ዓይን ነገ ላይ ይከዳል ። እግርም ምርኩዝ ይፈልጋል ። ሽንትም መቆጣጠሪያው ተጎድቶ እያመለጠ ይመጣል ። የቤቴን አንዲት ሣር መዘዙብኝ ብለን ዛሬ እንጣላለን ፣ መላውን ቤት ጥለነው አንድ ቀን እንሄዳለን ። ይህ ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው ። አዲስ ነገር የለም ። ይህ ሲገባን ቍጣን እንተዋለን ።

ይቀጥላል

የካቲት 26 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ