ቍጣን ለማብረድ
የሰዎችን ጠባይ ማወቅ
ሰዎች ከእውቀት ማነስ ፣ ትክክል ነው ብለው ከያዙት አቋም ፣ ከደረሰባቸው ጉዳት ፣ ካልታከመ ችግራቸው የተነሣ የሚያዳብሩት ጠባይ አለ። ቤተሰብና ማኅበረሰብ የሚሰጠው ጠባይ እንዳለ ሆኖ ሰው በተፈጥሮውም ደካማ ነው። ዓይኑ ጽድቅ እያየ እግሩ ኃጢአትን ይረግጣል። የሰውን ድካም አንተ ታውቀዋለህ የሚለው ድንቅ ጸሎት ነው። ሰዎች በሰውነት የራሳቸው ድካም እንዳላቸው ሁሉ በጾታቸው ደግሞ የተለያየ ክፍተት አለባቸው። ሰውነታቸውን ወደ መልአክነት መለወጥ አይችሉም። ወንዱም ሴት፣ ሴትም ወንድ መሆን አይችሉም። ከአንድ ጾታም የተለያየ ጠባይ እናገኛለን። የሰው ጠባይ በሚጠሉት እያዘነ የሚወዱትን የሚገፋ ነው። ለክፉ ጌታ እየታዘዘ ደግ አሠሪ ሲገጥመው የሚለግም ነው። የሰው ጠባይ ከሚያልፍበት ችግር የተነሣ ተለዋዋጭ ነው። ስሜቱን መግዛት የሚችል የመንፈሳዊነት ማማ ላይ የወጣ ፣ በልዩ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ያለፈ ፣ በራሱ ላይ የሞራል አብዮት ማድረግ የቻለ ብቻ ነው። እንደ ቀኑ አየር ንብረት ሲለዋወጥ የሚኖር ቢኖር ሰው ብቻ ነው:: እንደ አገርም ጠባያችን የተለያየ ነው። ያልተቀበልከው ምን አለና እንደ ተባለ ከማኅበረሰቡ ያልተቀበልነው ምን አለና !
አየር ንብረቱ ምቹ በሆነበት፣ በቀላሉ ምግብ በሚገኝበት አካባቢ ያደጉ ብዙ ጊዜ ሰነፍ ናቸው። የሰውን ጥንካሬ የሚያወጣው የተፈጥሮ ትግል ነው። ጦርነት ከማይጠፋበት አካባቢ ያደጉ ተጠራጣሪ ናቸው። እንደ አህጉርም ጠባያችን ይለያያል። አውሮፓውያን ሥራን ሲወዱ ማኅበራዊነት ግን አምልጧቸዋል ፤ አፍሪካውያን በኅብረት ይኖራሉ ፣ሥራ ግን አይወዱም። የሚገርመው በነጮች አገር ላይ በትጋት የሚሠሩት ጥቁሮች በአገራቸው ሰነፎች ናቸው። ወንዶች ቶሎ መንቃት ይቸገራሉ፣ መፍዘዝ ይታያል። ሴቶች በማለዳ ሥራ ሲገቡ ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ግን ወጣ ገባ ማለት ይወዳሉ። ወንዶች ግዴለሾች፣ ሴቶች ስጉ ናቸው። እጅግም ጥንቃቄ ስህተት ይወልዳልና የወንዶች ለቀቅ ማለት ይረዳል።
ሰዎች ከሃይማኖታቸው የተነሣ የሚያዳብሩት ጠባይ አለ ። ጠባያቸው፣ አመጋገባቸው ፣ ርእዮተ ዓለማቸው ፣ ማኅበራዊነታቸው በሃይማኖታቸው የተቀረጸ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ የዓለምን ሰላም የዓለም ሃይማኖት እያገዘው አይደለም። የተለያየ ፍልስፍና ውቅር የሆነ ሰው ወደ እኛ ሲመጣ ያንን ሰው መረዳትና መምራት ያስፈልጋል። ልክ ነው ብሎ ለረጅም ዘመናት ያዳበረውን ጠባይ በአጭር ጊዜ መተው አይችልም ። ስልጠና ግን እንኳን ሰውን እንስሳንም ይለውጣልና ማሰልጠን አለብን። ገንዘብም፣ ክፉ ጓደኛም አመል ያወጣልና በሰፊው ማየት አለብን። ጌታችን የጴጥሮስን ችኩልነት ለፈጣን ተልእኮ ፣ የዮሐንስን ትዕግሥት ለረጅም ተልእኮ ተጠቀመበት ። ስለዚህ ጴጥሮስ 66 ዓ ም. ሥራውን ፈጸመ ፣ ዮሐንስ 96 ዓ.ም. ሥራውን ፈጸመ። የሰዎችን ጠባይ ካወቅን ጠቃሚ ልናደርጋቸው እንችላለን። ብዙ የተማረ ፣ ልምድ አለኝ የሚል ከገጠር በመጣችና ለነገሮች እንግዳ በሆነች ሠራተኛ ቢያዝን ጥቅም የለውም። ካላወቁት እንኳን የሕይወት መንገድ የአዲስ አበባ መንገድን ማቋረጥም ከባድ ነው።
ይቀጥላል
የካቲት 27/2018 ዓ.ም.