የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -16

ቍጣን ለማብረድ

ዝምታን መለማመድ

ንግግር በጊዜው የሥልጣን ቃል ነው ፣ ዝምታ በጊዜው ቀኑን ማለፊያ ነው ። ዝምታ በአንደበት ላይ ባለሥልጣን መሆን ነው ። ዝምታ የመናገር አንዱ አካል ነው ። ዝም ማለት መስማማት ነው በማለት ዝምታን የሚተረጉሙ አሉ ። ዝምታ ተቃውሞም መግለጫ ነው ። ዝምታ እግዚአብሔርን የምንጠብቅበት መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ነው ። በዝምታ ውስጥ ኃይልን መሰብሰብ ይቻላል ። በዝምታ ውስጥ ራስንና ዓለምን ማየት ይቻላል ። በንግግራችን ክብር ያልሰጡን ዝም ስንል መደንገጥ ይጀምራሉ ። ሁልጊዜ ዝምታ ዱዳነት ነው ፣ ሁልጊዜ መናገርም እብደት ነው ። ዝምታ ጌጥ ነው ። ዝምታ በመብሰል ፣ በእግዚአብሔር ፍጹም በመታመን የሚገኝ ነው ። ዝምታ መናገር ለውጥ አላመጣ ሲል የምንመርጠው መንገድ ነው ። እኛ ዝም ካላልን እግዚአብሔር አይናገርም ። ዝምታ እግዚአብሔር እንዲናገር መንገድ መልቀቅ ነው ። ዝምታ ተአምራትን የምናይበት ምሥጢር ነው ። ዝምታ ሌሎችን ለማስጨነቅ ሲውል የበቀል መሣሪያ ይሆናልና የተጠላ ነው ። ዝምታ በጽሞና ይጀምራል ፣ በአርምሞ ይጠናቀቃል ። ዝምታ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምትታወቅበት ጠባይ ነው ። እንባዋ ፣ ሕይወትዋ ፣ ጸሎትዋ ቋንቋ ነበረ ። የእግዚአብሔር ማደሪያ ናትና ዝምታን መረጠች ። እግዚአብሔር የሚወደውን የእግዚአብሔር እናት እርስዋ ታውቃለች ።

በድንግልና መፅነስዋ የሰው አእምሮ ፣ በቀመር የሚመራው የፍጡር ልብ የሚቀበለው አይደለምና ዝም አለች ። ለእርስዋ የገለጠ አምላክ ለሌሎች እስኪገልጥላቸው ዝም አለች ። በሥጋና በደም ትግል ፣ በሥጋና በደም መምህር ፣ በሥጋና በደም አእምሮ መረዳት የማይቻለውን ነገር ሰማያዊ መገለጥ ያስፈልገዋል ። የተረዳነውን መንፈሳዊ ምሥጢር ለጋ ለሆኑ ሰዎች ብናስረዳ ፣ በአእምሮ እንጂ በመንፈስ ላልሆኑት ብንነግር ላይገባቸው ይችላል ። እግዚአብሔር እንዲገልጥላቸው በዝምታ መጸለይ ግን አስተዋይነት ነው ። መልአክ አብስሯት በበረት መውለድን መቀበልዋ የሚደንቅ ነው ። በዝምታ ፈጣሪዋን ትሰማ ነበር ። እኛ ስንናገር እግዚአብሔር ዝም ይላል ። ባልገባን ነገር ፣ ከአእምሮችን በላይ በሆነ ምሥጢር ፣ ልንለውጠው በማንችለው ምርጫ ዝም ማለት ይገባል ። ዝምታ ጣዕም አለው ። ዝምታ በውስጡ ከእግዚአብሔር ጋር ንግግር አለው ። ዝምታ የጸሎት እናት ናት ። ጾም የታዘዘው ለዝምታና ለምጽዋት ነው ። ዝምታ ሥጋ ዝቅ ሲል ነፍስ ስታይል የሚመጣ ነው ። ዝምታ ሰማየ ሰማያት ለመውጣት የተመስጦ መሰላል ነው ። በዝምታ ውስጥ የመላእክትን ዝማሬ መስማት ይቻላል ። ስሜታችንን በሙሉ መግለጥ ከሰዎች ጋር መናናቅን ያስከትላል ። ሁሉንም የመናገር ግዴታ የለብንም ። እስከ መጨረሻው ስላወራን ሰዎች ተረዱን ማለት አይደለም ። አንዳንድ ነገሮችን በዝምታ መያዝ አለብን ። ጥብቅ ወዳጅን ፣ የገቢ ምንጭን በዝምታ መያዝ ይገባል ።

ጊዜው እስኪደርስ ዝም እንላለን ። ከጊዜው በፊት የተነገረ ነገር ይባክናል ። ተወልዶ ፍስሐ ፣ ተገልጦ የምሥራች አይሆንም ። ዝምታ ጊዜን መጠበቅ ነው ። ለማጥቃት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሥራ ለማሳየት ጊዜን መጠበቅ እርሱ ዝምታ ይባላል ። ዝምታ ተቆልሎ መቀመጥ አይደለም ። መቆለል ያለ አዋቂነትና የትንሽነት ምልክት ነው ። ሲቀበለው የኖረውን ነገር በሌሎች የሚገልጥ ቁልል ሰው አለ ። ዝምታ ደርባባነት አይደለም ። ደርባባነት ድራማ ሊሆን ይችላል ። ሰው ወደ መልአካዊ ጠባይ ማደግ ግቡ ነው ። መልአክ ለመሆን ደግሞ ክንፉ የቀለለው መሆን አለበት ። ኩራት ባለበት መንፈሳዊ ሽንፈት አለ ። ዝምታ የትሕትና ውጤት ነው ። ዝም ስንል ሊቃውንትን እናዳምጣለን ።

ዝም ስንል ሌሎች እንዲናገሩና አሳባቸውን እንዲገልጡ እናግዛለን ። ማዳመጥ ትልቁ ሥነ ሥርዓት ነው ። ሰዎች ጉዳያቸውን ከመፈጸማችን በላይ ስናዳምጣቸው ደስ ይላቸዋል። ችግራቸውም የሄደ ያህል ይሰማቸዋል ። ለማዳመጥ ዝምታን መለማመድ ያስፈልጋል ። ሰዎች ሰባ ከመቶ ጭንቀታቸው በመናገራቸው ብቻ ይወገዳል ። ስለዚህ ማዳመጥ የሰዎችን ሰባ ከመቶ ችግር ማቅለል ነው ። በፕሮፓጋንዳ የሚያምኑ ፣ የወጡበትን ሕዝብ አታውቅም የሚሉ የዓለም መሪዎች በዝምታ ማዳመጥ አይሆንላቸውም ። ለጋራ አገር መዋሸትና በንግግር የበላይነት ለመደምደም ይጥራሉ ። ሕዝብ ሲደመጥ ደስ ይለዋል ። የዓለምን ችግር በሙሉ የሚፈታ መሪ የለም ። ዓለም በሥሪቷ ጎዶሎ ናት ። መንግሥታት በማዳመጥ ጉድለቱን ሙሉ ማድረግ ይችላሉ ። ደግሞም ሠራዊታቸውና አስፈጻሚዎቻቸው ከሚያግዟቸው ሕዝብ ቢያግዛቸው ይሻላል ። ሕዝብ በቀላሉ አገርን የማሳደግ አቅም አለው ፣ የተሠራውንም የመጠበቅ ብቃቱ የተደነቀ ነው ። በማዳመጥ የሕዝብን ልብ መግዛት ፣ ባለማዳመጥ የሕዝብን ጉልበት እስከ ጊዜው መግዛት ይቻላል ።

ቍጣ ከሚወገድባቸው መንገዶች አንዱ ዝምታ ነው ። አንዳንድ ነገሮች የሚለወጡ አይደሉም ። አንዳንድ ነገሮች ማስታመም ይፈልጋሉ ። አንዳንድ ነገሮች ልጄ ይችለዋል ብሎ አምላክ የሰጠን ነውና እንዳናሳፍረው መጠንቀቅ አለብን ። አንዳንድ ነገሮች እምነታችን ነጥሮ ሲወጣ ለሌሎች ትምህርት የሚሆኑ ናቸው ። መጽሐፈ ኢዮብ 42 ምዕራፎች አሉት ። ሁለቱ ምዕራፍ ታሪክ ነው ። ከምዕራፍ 3-37 ሰዎች ይናገራሉ ። ሰው ዝም ሲል እግዚአብሔር ተናገረ ። በምዕራፍ 42 ላይ ኢዮብ፡- “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ” አለ ። ኢዮብ መከራን የተቀበለው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እንዲገለጥና እጥፍ በረከት ለማግኘት ነው ። ያለ መከራ ጸጋ አይገኝም እንዲሉ ። ጻድቁ ኢዮብ በዚህ መከራ ውስጥ ያለፈው እግዚአብሔር ሳይችል ቀርቶ አይደለም ። መከራውን ከማስወገድ በላይ ኢዮብን በማጽናቱ ኃይሉ ተገልጧል ። በዚህ ውስጥ ማለፋችን ግድ ከሆነ በትዕግሥት ቀኑን እንጠብቅ ።

ተመስገን ያልከው ይሁን !

ይቀጥላል
መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ