ቍጣን ለማብረድ
ትሕትናን ገንዘብ ማድረግ
ቍጣ በሕመም ስሜት ከማለፍ የተነሣ ይመጣል ። በሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች ቀን ዕረፍት ፣ ሌሊት እንቅልፍ የላቸውምና ቍጠኛ ይሆናሉ ። አእምሮአቸው ስለ ሕመማቸው የሚነግራቸው ብዙ ነገር አለና ከዚያ የተነሣ ብስጩ ይሆናሉ ። ቍጣ ይቅርታ ካላገኘ ግንኙነት ሊነሣ ይችላል ። ይቅርታ ማጣት የሚያስደስተው ነገር በቶሎ መለያየት ነው ። ሰዎች ተቀያይመው አብረው ይኖራሉ ። አብረው መኖራቸው ግዳጅ የወለደው እንጂ በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አይደለም ። ቂም በማያቋርጥ ቍጣ መኖር ነው ። ሰው ወዳጁን ከሚያስበው በላይ የጠላውን ያስባል ። በግንኙነት ውስጥ ያለ ምክንያት ቍጣዎች ሲኖሩ ይቅር ያልተባለ ጉዳይ አለ ማለት ነው ። ያለፈው ዘመኔ ባክኗል ብሎ የሚጸጸት ሰው ቍጠኛ ይሆናል ። በትምህርቴ ፣ በሥራዬ ፣ በወዳጅነቴ ፣ በትዳሬ ፣ በልጆቼ ውጤታማ አይደለሁም የሚል ስሜት ውስጥ የገባ ሰው ቍጠኛ ነው ። ከዚህ በኋላ የማድሰው ኑሮና ሕይወት የለም ብሎ ስለሚያስብ ነው ። ነገር ግን በዚህ ዓለም እስካለን ድረስ እያንዳንዱ ደቂቃ የለውጥ አጋጣሚ ነው ።
ቍጣ የሚነሣው ትሑት ማንነትን በማጣት ነው ። ሰዎች ውስጣቸው በኩራት ሲወጠር ትዕቢት ይታይባቸዋል ። ከፍተኛ ዕጢ የተሸከመ ሰው ውጫዊ አካሉም አብጦ ይታያል ። የኩራት ዕጢ በትዕቢት ይገለጣል ። ትዕቢት ሲነገረን ካደግንበት ሁኔታ ይነሣል ። አንተ እኮ ቆንጆ ነህ ፣ አንቺ እኮ ከሁሉ ትበልጫለሽ በሚል ነፋስ ሲሞሉ ያደጉ ማበጥ ግዳቸው ነው ። ትዕቢት ከዝሙት በላይ ብርቱ ፈተና ነው ። የበታችነት ስሜት ፣ በድህነት ውስጥ ማደግ ፣ እናቃለሁ ብሎ ማሰብ የትዕቢት መገኛ ነው ። አምባገነን ነገሥታት ሁሉ ይህ ስሜት ነበራቸው ። ትዕቢት በጨፍጫፊነት የሚጠናቀቅ ነው ። ሁሉንም እንደ ጠላቱ ያያልና ። የሚገርመው የመንፈሳዊነት መገለጫ ኩራት እየመሰላቸው ፣ በዓለም ሳሉ ተግባቢ የነበሩ አሁን መንፈሳዊ ሲሆኑ ለመናገር መጨነቅ ይጀምራሉ ። የሰባኪ ድምፅ ጎርነን ያለ ነው ብለው በማሰብ ድምፃቸውን ናዳ የሚያደርጉ ሰዎችም ይኖራሉ ። አስደናቂው ነገር እቤታቸው መጥቶ የሚጸልይላቸውን ካህን ንቀው የማይመጡና የማያናግሩ ካህናትን የሚያከብር ሕዝብ መፍጠራችን ነው ። ኩራት የብቃት ምልክት እየመሰላቸው ብዙዎች ትሕትናን አጥተዋል ። አንድ ትዕቢተኛ ጸጋ በዝቶለታል ቢባል ሐሰት ነው ። ምክንያቱም ጸጋ የሚበዛው ለትሑታን መሆኑን መጽሐፍ ይናገራልና ።
ትሑት ማንነት ስናጣ ነጭናጫ እየሆንን እንመጣለን ። ትዕቢተኛ ሰው እንደ ጣዖት መታየት የሚፈልግ ፣ ምቾቱን አምላክ ያደረገ ነው ። ሰዎችንም የሚፈልገው ምቾቱን ለማዳበር ነው ። ምቾቱን የማይጠብቁ ሰዎችን እንደ ጠላት ያያል ። የአገልጋይነት ስሜት የለውም ፣ ሁልጊዜ መገልገል ይፈልጋል ። ምን እሰጣለሁ ( ሳይሆን ምን እቀበላለሁ ( ብሎ የሚያሰላ ነው ። የሚያደርገውን መልካም ነገር እንኳ ለገበያ ያውለዋል ። አንድ ሚሪንዳ ለታማሚ ካጠጣ እርስዋንም ቪድዮ ቀራጭ አቁሞ ነው ። መልካም ማድረግ አይገባኝም ብሎ ያስባልና ትዕቢተኛ ምስኪን ነው ። የተሰጠውንም አካላት ያባክናል ። እጁ የተሰጠው ሠርቶ እንዲበላና እንዲያበላበት ነበር ። እግሩም የተሠራው ወንጌልን ዞሮ እንዲሰብክበት ነበር ። ጆሮው የተጨነቁ ምእመናንን እንዲሰማበት የተፈጠረ ነበር ። ትዕቢት ማባከን ነው ። የሌለውን ክብር የሚፈልግ ሰው ያለውን ክብር ያጣል ። እግዚአብሔር ሲያከብር እንጂ ክብር በትግል አይገኝም ።
ትሕትናን ስናጣ ሰው መራጭ እንሆናለን ። ሰዎችን ለመውደድና ለመቅረብ ሰውነታቸው በቂ እንዳልሆነ እናስባለን ። በደረጃ መዋል የሚባለው የዓለም ስሌት ውስጥ እንገባለን ። ተፈላጊ የሚያደርጉ ሰዋዊ ስልቶችን ማጥናት እንጀምራለን ። ኑሮን በኮድ እንጂ በእምነት ለመኖር አናስብም ። እስካለን ድረስ ልንቆም እንችላለን ። የወደቅን ቀን ግን የሚያነሣን የለም ። ትሕትናን ስናጣ ጽዩፍ እንሆናለን ። የቆሸሸ የለበሰን ሰው በአምስት ደቂቃ ማጽዳት ይቻላል ፣ የእኛ ትዕቢት ግን በውኃ የሚጸዳ አይደለም ። የቆሸሸው ድሀ እኛን ቢንቅ የበለጠ ቆሽሸናል ። ትዕቢት ንጹሕ ለብሶ መቆሸሽ ፣ ወይም ቆሻሻነትን በንጹሕ ልብስ መደበቅ ነው ። የእኛን መጨረሻ አናውቀውምና በሽተኛን መጸየፍ አይገባም ። እንደውም ጊዜ ሰጥተን ማስታመም ፣ በየሆስፒታል እየሄድን መጠየቅ ይገባናል ። በሕይወት መጨረሻ ላይ ከሚጸጽቱ ነገሮች አንዱ እንዲህ ዓይነት በጎ አድራጎት ላይ አለመሳተፍ ነው ።
ትሕትና ማጣት ብቸኛ ያደርጋል ። ሰዎች አይመጥኑኝም ብሎ በመስፈርት የሚጠብቅ ሰው የእርሱን መስፈርት የሚያሟላ የለም ። የፈጠረ አምላክ እንኳ ይህን አላገኘም ፣ ደግሞም ባለመስፈርቱ ራሱ ያንን መስፈርት አያሟላም ። በአጭር ቃል ትዕቢተኛ በገደል አፋፍ ላይ የሚሮጥ ፣ ውድቀቱ ቅርብ የሆነ ነው ። ትዕቢተኛ በልብ የሚንቅ ፣ በአፉ የሚሳደብ ፣ መልሶ ጌታ ይቅር ይበላቸው በማለት ትሑት ለመምሰል የሚጥር ነው ። ትሑት ለመባል ትሑት የሚሆን ትዕቢተኛም አለ ። ብዙ ሰዎች አንገታቸው ይቅለሰለሳል ፣ ልባቸው ግን ከዳሸን ተራራ ይልቅ ቆሟል ። ትሑት መሆን ቍጣን ይቀንሳል ። የብዙ ቍጣ ምንጩ ተነካሁ ፣ ተናቅሁ የሚል ነውና።
ይቀጥላል
መጋቢት 14 ቀን 2018 ዓ.ም.