ቍጣን ለማብረድ
መጸለይ
በማኅበር መጸለይ የሚችል ሰው የቤተሰብ ጸሎት ያለው ነው ። የቤተሰብ ጸሎት መጸለይ የሚችል ሰው የግል ጸሎት ያለው ነው ። ማኅበር ሰላም የሚሆነው በጸሎት ነው ። ለሰላም እንጸልያለን ፣ በጸሎትም ሰላም እናገኛለን ። ጸሎት ራሳችንንና ወንድማችንን በክርስቶስ ፍቅር እንድናየው ያደርገናል ። ከመጠን በላይ ራስን መውቀስ ፣ ወንድምንም መክሰስ የሚመጣው ባለ መጸለይ ነው ። ራስን መውቀስ ለመለወጥ የሚያነሣሣ እንጂ ኑሮ መሆን የለበትም ። ከመጠን በላይ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ እያሉ ማውራት በውስጡ እኔ ጻድቅ ነኝ የሚል መልእክት ያለው ነው ። እኔ ቆሻሻ ነኝ ብሎ ማውራትም አይጠበቅም ፣ መታጠብ መፍትሔ ነው ። ትሕትና እኔ ኃጢአተኛ ነኝ ብሎ መናገር ሳይሆን ኃጢአተኛ ሲሉን በደስታ መቀበል ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከውጭ ቀስት ፣ ከውስጥ ሁከት እያናወጣት ነው ። አንዳንድ ሰዎችም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ሀብት መሆንዋን ረስተው እንደ ግል ንብረታቸው ያለኋት እኔ ነኝ ብለው ያስባሉ ። ቤተ ክርስቲያን የካደውን ማሳመን እንጂ ያመነውን በር ከፍቶ ማስወጣት ተልእኮዋም አይደለም ፣ ይህ ደመ ኢየሱስን ማርከስ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ሰላም የዓለም ሰላም መሠረት ነው ። የሰላም ቤት ከታወከች ፣ ሌላው እንዴት ሰላም ሊሆን ይችላል( የማኅበር ጸሎት የሚሠምረው ከቂም ጸድቶ ሲቀርብ ነው ። ባላጋራ ሁኖ መቀደስ ፣ ለሞት እየተፈላለጉ በአንድ ላይ ቆሞ እግዚኦ ማለት ወደ ተዘጋ ሰማይ መገስገስ ነው ። “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዲሉ ከመጸለይ በፊት ፍቅር መቅደም አለበት።
የቤተሰብ ጸሎት የትዳር ጅማሮ ላይ ይደረግ የነበረ ሲሰነብቱ የሚተዉት ነገር ነው ። አንዳንድ ሰው ክርስትናውን ትዳርና አሜሪካ ሲደርስ አቁሞታል ። ባለትዳሮች ምንም ቢጣሉና ቢካረሩ የጸሎት ሰዓት እስኪደርስ ነው ። የቤተሰብ ጸሎት ካለ በግድ ወደ ይቅርታ ይመጣሉ ። የቤተሰብ ጸሎት የልጆችን ልቡና ቀና ያደርጋል ። የቤቱ ራስም ክርስቶስ መሆኑን ማመንና መሪውን ለእርሱ ማስጨበጥ ነው ። የጎደለው እንዲሞላ ፣ የጠመመው እንዲቀና ፣ ልጆች በፈሪሀ እግዚአብሔር እንዲታነጹ የቤተሰብ ጸሎት አስፈላጊ ነው ። አባወራ የቤቱ ካህን ነው ። በሕገ ልቡና ካህን አባወራ እንደ ነበረ ሁሉ የቤተሰቡ ካህን ባል ወይም አባት ነው ። እርሱም የጸሎት መሪነቱን መወጣት አለበት ። ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥም እንኳ ሌላ አባት እንዳለ ልጆች የሚያውቁት የጸሎትን መስመር ስንጠቀም ነው ።
ክርስትና በግል እሺታ የሚጀመር ፣ ውሳኔ የሚጠይቅ እምነት ነው ። ወላጆቻችን በጥምቀት ወደ ልጅነት ጸጋ እንድንመጣ ቢተጉልንም ወስነንና ዋጋ ለመክፈል ቆርጠን ክርስትናን መከተል አለብን ። የግል የጸሎት ሕይወት ከሌለ የቤተሰብና የማኅበር ጸሎትም ውጤታማ አይሆንም ። ብዙ ሰው የቤተሰብ ጸሎትና የማኅበር ጸሎት ላይ ይገኛል የግል ጸሎትን ግን ችላ ይላል ። እያንዳንዱ የራሱን ዕድገት ሲጠብቅ ከሌሎች ጋር አብሮ ማደግ ይችላል ። በራሱ አየተናደደ የሚኖር ፣ ራሱ ላይ የሚቆጣ ብዙ ምስኪን ሰው አለ ። ይህ ሰው በጸሎት ለእግዚአብሔር መራቆትና የጸጋውን ልብስ መደረብ አለበት ። ጸሎት የግል ፣ የቤተሰብና የማኅበር ብለን በሦስት እንከፍለዋለን ። አንዱ ያንዱ ምትክ አይደለም ። በእምነት ማደግ ስላለብን የግል ጸሎት ያስፈልገናል ፣ ቤተሰቡ በኃይለ ኢየሱስ መታጠር ስላለበት የቤተሰብ ጸሎት ያሻናል ። ክርስቶስ የሞተው ለቤተ ክርስቲያን ወይም ለዳነች አዲስ ዓለም ነውና የማኅበር ጸሎትም አስፈላጊና ግዳጅ ነው ።
የግል ጸሎት ለመጸለይ ሰው እልፍኙን ይዘጋል ፣ በዚህ ምክንያት ከራሱና ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ያገኛል ። ራሱንና ሌሎችን ለመቀበል ይህ ጊዜ ወሳኝ ነው ። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ካልኖረ ከራሱ ጋር መኖር ፣ ከራሱ ጋር ካልኖረም ከሌሎች ጋር መኖር አይችልም ። የቤተሰብ ጸሎትም ቤተሰቡ በአንድነት ለመገናኘት ዕድል የሚሰጥ ፣ ፍቅርን የሚጨምር ነው ። ቤተሰብ ቢያንስ ጠዋትና ማታ አብሮ መመገብና መጸለይ አለበት ። ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር የኮራ ቤተሰብ ጠበቃ ሲያናግር የሚውል ነው ። የማኅበር ጸሎት ለማድረስም በግድ ቤተ ክርስቲያን መሄድ አለብን ። ይህ ማኅበራዊነትን የሚጨምር ነው ። በግል ጸሎት እቤታችን አማኑኤልን ጋበዝነው ፣ በማኅበር ጸሎት ደግሞ እግዚአብሔር ጋብዞን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሄዳለን ፣ ሥጋ ወደሙ እንቀበላለን ።
ጸሎት ያረጋጋል ። ጸሎት ይቅር ለማለት ኃይል ይሰጣል ። ጸሎት ፍርሃትን ያስወግዳል ። ጸሎት የመውጫውን መንገድ ያሳያል ። ጸሎት ከውጊያ ቀናት ይሰውራል ። ጸሎት ከአጉል ውሳኔ ይታደጋል ። ጸሎት ሌሎችን የምንወድበትን ፍቅር ያፈስሳል ። ጸሎት እኔ ከማለት እኛ ወደ ማለት ይመራል ። ጸሎት እውነተኛ ሰው ያደርገናል ። ጸሎት ተራራ የሆነውን ችግር ይደለድላል ። ጸሎት ራስን መግዛት ይሰጣል ። ጸሎት ልክ ነኝ ከማለት ተሳስቻለሁ የሚል ትሕትናን ያስተምራል ። ጸሎት የእንደገና ዕድል እንዳለን ይጠቁመናል ። ጸሎት ለትክክለኛ ውሳኔ ጉልበት ይሆናል ። ጸሎት በቍጣ ስንነድ በጸጋ ያቀዘቅዘናል ። ጸሎት የአእምሮ ጤንነታችንን ፣ የማስታወስ ችሎታችንን ፣ ደስተኛነታችንን ይጠብቃል ። ቍጣን ለማብረድ ጸልዩ ።
ይቀጥላል
መጋቢት 15 ቀን 2018 ዓ.ም.