የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -19

ቍጣን ለማብረድ

ጠብን ማስተዳደር

መጣላት ይኖራል ፣ መጠላላት ግን አይገባም ። ጠብ ካስተዳደሩት ፍቅርን የሚጨምር ሊሆን ይችላል ። ሰዎች ልክ እንደ እኛ ካሰቡ አይጠቅሙንም ። የተለየ አስተሳሰብ ካላቸው ያላየነውን የምናይባቸው ዓይናችን ይሆናሉ ። አለመግባባቶች የመለያየት ምክንያት ላይሆኑ ይችላሉ ። በሃያ ዓመታችን ላይ ትክክል ያልነበረው ነገር በአርባ ዓመታችን ላይ ትክክል ይሆናል ። በሠላሳ ዓመት የነበረው ቍጣ በሃምሳ ዓመት ላይ ፈገግ የሚያደርግ ፣ በስድሳ ዓመት ላይ ከትከት አድርጎ የሚያስቅ ነው ። እያንዳንዱ ሰው በጊዜው የሚረዳው ነገር አለ ። እኛም በጊዜው የምናስተውለው ነገር አለና ያልተግባባነውን ሰው መጥላትና መቆጣት አይገባንም ። ቅዱስ ጳውሎስ ትላንት የሚያሳድደውን እውነት ዛሬ ሰማዕት ሲሆንለት እናያለን ። ሰው ወደ መለወጥ እየተጓዘ ነው ። ሰዎች የነገርናቸውን ነገር ዛሬ ቢገፉት ነገ ይከተሉታል ፣ ምክንያቱም እውነት የእኛ ሳይሆን የመለኮት ገንዘብ ነውና ። ሰዎች የነገርናቸውን ነገር አሁን ይቃወሙታል ፣ አልሰሙንም ብለን ስናስብ በድብቅ ይተገብሩታል ። እንደውም አንገታቸውን እየነቀነቁ ፣ ልክ ነህ እያሉ የሰሙን ሰዎች ላይሰሙን ይችላሉ ። ተቃውሞ ሰዎች ውስጣቸው የተቀመጠው አስተሳሰብ ሲመታባቸው ያሰሙት ድምፅ እንጂ ጥላቻ አይደለም ። ካልተመታ በቀር የሚጮኽ የለምና ። አብረውን ያሉ ዝምታቸው እኛን መጥላት ሳይሆን ለእኛ እያሰቡ ሊሆን ይችላል ። የዝምታ ጊዜ ሲፈልጉ ፣ ከራሳቸው ጋር እንዲያወጉ ዘወር እንበል ። ምክንያቱም ከእኛ ጋር የሚሆኑት ከራሳቸው ጋር ሲሆኑ ብቻ ነው ። ማንበብ ፣ መጸለይ ፣ ማሰላሰል በየዕለቱ አቅም ለመሰብሰብ የሚረዳ ነው ። ድንጋይ ከመፍለጥ በላይ ከባዱ ጉልበት ሌሎችን መውደድ ነው ። ይህን የምናገኘው ከመንፈሳዊው ዓለም ብቻ ነው ።

ጠቦች ሲፈጠሩ ለዘብተኛ መሆን ይገባል ። እሳትን በእሳት ማጥፋት አይቻልምና ። ደግሞም ሰዎች ስህተታቸውን በእኛ የተሳሳተ ምላሽ ውስጥ ይደብቁታልና አጉል መልስ መስጠት አይገባንም ። በገርነት ለመመለስ ካቃተን አካባቢውን ለቀን እንሄድ ። ትንሽ የማሰቢያ ጊዜ ስናገኝ እንረጋጋለን ። ሰይጣን ጊዜ አትውሰድ እያለ ገዳይ ያደርገናል ። መንፈስ ቅዱስ ግን ጊዜ ውሰድ እያለ ራሳችንን ያሳየናል ። ሰው በክፉ መንፈስ ውጊያ ውስጥ መሆኑን የሚያውቀው ሰዎችን በጣም ማየት ሲጀምር ነው ። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዳለ የሚገነዘበው ራሱን ሲያይ ነው ። ራስን ማየት ትሑት ያደርጋል ። ራሱን የሚያይ በክርስቶስ ምሕረት ተደግፎ እንደ ቆመም ይረዳል ። ጠቦች ሲፈጠሩ ወደ ንግግር መምጣትን ፣ መወያየትን መድፈር ያስፈልጋል ። የመነጋገር ጠባይ የለንም ። ይህን ብሰማ የበለጠ እናደዳለሁ በማለት በግምት ብቻ እንሸሻለን ። አለመነጋገሩ ፍቅርን ካላመጣ መነጋገሩ ጠብን አያመጣም ። ሁልጊዜ ስንነጋገር ሰውዬው ለራሱ ያለውን ዋጋ እንዳያጣ በመጠንቀቅ ሊሆን ይገባዋል ። ካሉት ጥሩ ነገሮች በመነሣት ንግግር ከጀመርን ውጤታማ እንሆናለን ፣ ይህ ነገርም መለኮታዊ አካሄድ ነው ። ጌታ የሌለንን ሳይሆን ካለን በመነሣት የሌለንን ያሳየናል ፣ እሺ ስንል ያግዘናል ። እኛው ለተለወጥነው ይሸልመናል ። እነዚህ አራት መለኮታዊ አካሄዶች በራእይ ዮሐንስ በሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ይታያሉ ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ሲገሥጽ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ” አለ እንጂ የሌላችሁ አላላቸውም ። እርሱ አሟጦ አይናገርም ። የጎደለው ግማሽ ሙሉ ነው ማለት ነው ። ንግግር ጦርነትን ያስጀምራል ፣ ጦርነትን ያስቆማል ። ዓለምን የምታባላ ምላስ ናት ።

በንግግራችን ሊያግባባን የሚችለውን በቅድሚያ መነጋገር መልካም ነው ። ከዚያ ቀጥሎ ጠንከር ያለውን ርእስ ማንሣት ይቻላል ። ንግግራችንን ሁሉንም ዛሬ መጨረስ አያስፈልገውም ፣ በይደር ደግሞ ማየት የተሻለ ነው ። ጥፋተኛው ያኛው ሰው ከሆነ የጥፋት ዝርዝሮቹን በአንዴ እርሱ ላይ መልቀቅ ለራሱ ያለውን ግምት ሊያጣ ፣ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል ። ጠብ መጨረሻ ሳይሆን የመኖር አንዱ ሂደት ነው ። በጣም የሚዋደዱ ሰዎች ይጣላሉ ። ምክንያቱም አንዳቸው ካንዳቸው ፍጹም ነገርን ስለሚጠብቁ ነው ። የማይዋደዱ ሰዎች ነገሮችን ቀላልና ለስላሳ በሆነ መንገድ ያሳልፉታል ። አብረውት ከማይዘልቁት ሰው ጋር መጨቃጨቅ አይፈልጉምና ። ልክ ነህ ፣ ልክ ነህ ስንባል መጠራጠር ያስፈልጋል ። በሁሉም ነገር ልክ ልንሆን አንችልምና ።

ጠባችንን እኛ ልንፈታው ካልቻልን በጋራ የምናከብረውን ሰው መጋበዝ አለብን ። ሽማግሌ የትላንት ወዳጆችን የዛሬ ተራርቀው የተቀመጡ አኩራፊዎችን የሚያቀራርብ ነው ። እኔ ነኝ ልክ በማለት የተጣሉት ሰዎች ሽማገሌ ጋ የሚሄዱት ፍርድ ለመስማት ነው ። ሦስተኛ ወገን ልክ አይደላችሁም ካለ መቀበል ይገባል ። የማይቀበል ሰው አስቀድሞ ከወዳጅነቱ ተፈናቀለ ፣ አሁን ደግሞ ከማኅበራዊ ኑሮውም ይፈናቀላል ። ከሁሉ በላይ መንፈሳውያን የሆኑ አባቶችና መምህራንን ፈልጎ መሄድ ተገቢ ነው ። ሽማግሌ ዘላቂውን ኑሮ ሲያሳይ መንፈሳውያን ደግሞ ዘላቂውን ሰማይ ያሳያሉ ። ሰማይን ስናይ ራሳችንን እንንቀዋለን ። ጠባችንም አናሳ ይሆንብናል ። የብዙ ጠቦች መነሻ አለመብሰል ነው ። ዕድሜ እየረዘመ ሲመጣ ያንን ሰው የተቀየምነው እኛን ለማስደሰት ባደረገው ጥረት መሆኑ ይገባናል ። ለእኛ ካለው ጥበቃ የተነሣ እዚህ ቦታ አትገኝ አለን እንጂ ነጻነታችንን አልተጋፋም ። ጠብ ከመራን እንጎዳለን ፣ ጠብን ማስተዳደር ከቻልን ግን የበለጠ መልካም ነገር እናገኛለን ። ንግግሮቹ ፣ ግለቶቹ ፣ መፍትሔ ለመፈለግ የሚሰሙ አሳቦች መነቃቃትን ይፈጥራሉ ። የከበደን ነገር ሁሉ ይቀለናል ። መግባባት እንደ ገና መሰረግ ፣ እንደገና አዲስ ግንኙነት መጀመር ነው ።

ቍጣን ለማብረድ ጠብን ማስተዳደር ይገባል ።

ይቀጥላል
መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ