የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -2

ቍጣ የሚመጣባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-

ከታመቀ ስሜት

ፍቅራችንንም ሆነ ቅሬታችንን መግለጥ በማይችል ባሕል ማደግ ፣ እርሱ እኮ ሁሉ በሆዱ ነው በሚል ሙገሳ መኖር የታመቀ ስሜትን ይወልዳል ። ሁሉም ሰው ለማንም ያልነገረው የራሱ ምሥጢር አለው ። የራሱ እስረኛ የሆነ እየመሰለውም ይማቅቃል ። የውስጡን ለመናገር የክብር ፍርሃት ፣ የማኅበረሰብ ተጽእኖ ፣ የሚረዳኝ ሰው የለም የሚል ተስፋ መቍረጥ ይይዘዋል ። እነዚህ የታመቁ ስሜቶች ልጅነትን እንደ በሉ ወጣትነትንም የመብላት አቅም አላቸው ። ምንም እንኳ በዓለም ላይ አዲስ ነገር ባይኖርም አጉል ምሥጢረኛነት ግን እኛ ጋ ብቻ ያለ ጉዳት አስመስሎ ይስልብናል ። በዚህ ምክንያት በውስጤ እንደ ታፈንሁ ወደ መቃብር እወርዳለሁ የሚል መሐላ ውስጥ እንገባለን ። ከልጅነት ጀምሮ በውስጣችን የያዝነውን ጉዳት ፣ ቁጭትና ቂም ለመንፈሳውያን አባቶች ሁሉንም በዝርዝር ማውጣት አለብን ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን እስክንረካ ድረስ ማውራት ያስፈልገናል ። በዚህ ዓለም ላይ እንደ መናገር ያለ ፈውስ የለም ። የምንናገርበት ቦታ ግን ትክክለኛ መሆን ያስፈልገዋል ።

ፍቅርን ሳያገኙ ማደግ

በእጓለ ማውታ ስፍራ የሚያድጉ ልጆች ትልቁ ችግራቸው የሚያቅፋቸው ሰው ማጣት ነው ። በዚህ ምክንያት ቍጡዎችና ታማሚዎች ይሆናሉ ። ፍቅርን ማግኘት ብዙ አቅም ይሰጣል ። ፍቅር ሞትን የማገድ አቅም አለው ። ሰዎች መኖርን እንደገና እንዲጀምሩ የምናደርገው ፍቅርን ስንሰጣቸው ነው ። በልጅነታቸው በብዙ መገፋት ያደጉ ፣ አባትን እየፈለጉ አባት የራቃቸው ፣ እናትን እየፈለጉ ማግኘት ያልቻሉ ፣ ማኅበረሰቡ ገና ከጠዋቱ ያገለላቸው ልጆች ቍጠኛ ይሆናሉ ። ፍቅር ቍጣን ያበርዳል ፣ ፍቅር ያለው ይታገሣል ። እነዚህ ሰዎች ፍቅርን ባለማግኘታቸው ያለ ማቋረጥ የሚንቀለቀል የቍጣ እሳት በውስጣቸው አለ ። ቤተሰባቸውም የተገለለ ከሆነ ፣ በድህነት ምክንያት አባት እናታቸው ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩ ከሆነ እነዚህ አቅም የለሽ ልጆች ቍጠኛ ይሆናሉ ። የወላጆቻቸውን ስድብ ማስቀረት አልቻሉምና ያላቸው ብቸኛ አቅም መበሳጨት ይሆናል ። አጉል ቅጣት እየቀጡ ልጆችን ማሳደግ ፣ ከልክ በላይ መንቀፍ ብስጩ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ። ብዙ አምባገነን መሪዎች ፍቅርን ሳያገኙ ያደጉ ናቸው ፣ በዚህ ምክንያት ሚሊየኖችን ዋጋ አስከፍለዋል ። እግዚአብሔር ደጋጎችን ፈጠረ ፣ ክፉዎችን እኛ እንፈጥራቸዋለን ።

ሐሰተኛ ይቅርታ

አብረን ለመኖር ብለን የውሸት ይቅርታ እናደርጋለን ። የተዳፈነው ጠባችን እነዚያ ሰዎች ትንሽ ሲሳሳቱ ይወጣል ። “ያኔም እንዲህ አድርጋችሁ ነበር” በማለት ይቅር ካልነው ጥፋት እንጀምራለን ። በዚህ ምክንያት አዲሱ ችግር የቆየውን እየቀሰቀሰ ግንኙነታችን መጨረሻ ላይ ይደርሳል ። በትልቁ ችግር አልፈናቸው በትንሹ ችግር ስንቆጣቸው እንዴት አብረን መዝለቅ እንችላለን በማለት ይሸሹናል ። የእኛ እውነተኛው ቍጣ ግን በዛሬው ሳይሆን በቆየው ችግር የመጣ ነው ። እነርሱ ደግሞ እንዴት በዚህች ትንሽ ነገር አያልፉኝም ይላሉ ። ሐሰተኛ ይቅርታ የቍጣ መነሻ ነው ።

ፍጹምነትን መጠበቅ

ያልተማረው ወላጅ ልጁ ሳይንቲስት እንዲሆንለት ይፈልጋል ። ከወንበሩ ያልተነሣው ሊቅ ደቀ መዝሙሩ አገርን እንዲወርስና ስሙን እንዲያስጠራ ይከጅላል ። የትልቅነት ስሜት ከራስ አልፎ ወደ ታች የመውረድና ያንን ካልሆናችሁ አትገቡም የሚል ቍጣ ይወልዳል ። ምንም ብንወዳቸው ልጆቻችን ይሳሳታሉ ፣ ምንም ብናስተምራቸው ደቀ መዛሙርት እየወደቁ ይነሣሉ ። ፍጹምነት የሌለና ልንጠብቀው የማይገባ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ መልካም ሰው ካገኘንም ትልቅ ነገር ነው ። በዚህ ዘመን ደግሞ ደግ የሚያደርግ ሳይሆን ደግ ሲደረግለት የሚያመሰግን ማግኘትም ብርቅ እየሆነ ነው ። ሰዎች እንደ እኛ መሆናቸውን ስናስብ ለራሳችን ያለ ማቋረጥ ይቅርታ እንደምናደርግ ለሰዎቹም እናደርግላቸዋለን ።

ይቀጥላል
የካቲት 16 ቀን 2018 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ