ቍጣን ለማብረድ
መወሰን
መወሰን የእግዚአብሔር ጠባይ ነው ። እግዚአብሔር ልጆቹ እንድንሆን ፣ ጽድቁን እንድንካፈል ፣ እርሱን እንድንመስል ፣ መንግሥቱን እንድንወርስ አስቀድሞ ወስኗል ። ውሳኔ የእግዚአብሔር ልጆች መገለጫ ነው ። እግዚአብሔር ጠላቶቹ እንድንሆን ፣ በኃጢአት ባሕር እንድንዋኝ አልወሰነም ። በመንግሥተ ሰማያት ያለው መቀመጫ ለሰውም ለመላእክትም የሚበቃ ነው ። ሰው መርጦ ወደ ሲኦል ቢወርድ የእርሱ ወንበር በመንግሥተ ሰማያት ክፍት ሁና ትኖራለች ። መተካካትና መሸጋሸግ በመንግሥተ ሰማያት የለም ። ውሳኔ ከበጎ ነገሮች ጋር የተያያዘ ነው ። ውሳኔ አማራጭ ሳይሆን ግዳጅም ነው ። ያለ ውሳኔ የራሳችንንም የሌሎችንም ሕይወት መለወጥ አንችልም ። ሰዎች የሚደነግጡት አሳባችንን ሰምተው ሳይሆን ውሳኔአችንን ሰምተው ነው ። እያንዳንዱ ቀን ውሳኔን የሚጠይቅ ነው ። ሰው በዚህ ዓለምም በሰማይም ወራሽ የሚሆነው ሲወስን ብቻ ነው ። መወሰን የአዋቂነት ፣ የመንፈሳዊ ጀግንነት መገለጫ ነው ። በእጃችን ያሉ ጥቂት ድሎች በመወሰን የተገኙ ናቸው ። ያንን ሱስ ለመተው ባንወስን ኖሮ ፣ እነዚያን አጉል ባልንጀሮች ለመራቅ ባንጨክን ኖሮ ዛሬ በሕይወት አንኖርም ነበር ።
ውሳኔ ገንዘብ የማይገዛውን ጊዜ ያተርፋል ። ውሳኔ ስንዴዎችን አስቀርቶ ገለባዎችን ይለያል ። ውሳኔ የትላንትን ገመድ ቆርጦ ዛሬ ላይ ነጻነትን ይሰጣል ። ውሳኔ የሕመም ዘመንን ያሳጥራል ። ውሳኔ ሰው በተፈጥሮው ባለሥልጣን መሆኑን ያሳያል ። ውሳኔ ለመጀመር ለመጨረስ አቅም ይሆናል ። ውሳኔ ከጠላት ጋር እንደ ጴጥሮስ እሳት ከመሞቅ ያላቅቃል ። ውሳኔ የማይቆይን ሰው መለማመጥ አቁሞ እንዲሄድ ይፈቅድለታል ። ውሳኔ እያስፈራራን የሚኖረውን ሰው ልኩን ያሳውቀዋል ። ውሳኔ በደስታ ለመኖር ፣ በጀግንነት ለመሞት ያግዛል ። ውሳኔ አገርን ከሺህ ዓመት አጉል ገመድ ይፈታል ። ውሳኔ አቁሳይ ሰዎችን ለመገላገል ያግዛል ። ውሳኔ ፍርሃትን ይረግጣል ። ውሳኔ ለራሴ የምኖረው መቼ ነው ? ያሰኛል ። ውሳኔ ያለ እንካ ከማይስቁ ሰዎች ይለያል ። ውሳኔ ሆድ አደሮችን ከላብ አደሮች ይለያል ። ውሳኔ ከአጋንንት ቍራኝነት ነጻ ያወጣል ። ውሳኔ ቃላችን ክብር እንዲኖረው ያደርጋል ። ውሳኔ ይህችን አጭር ዕድሜ ጣፋጭ ያደርጋታል ።
ለመወሰን የሚረዱ ነገሮች ብዙ መታገሥ አንዱ ነው ። መታገሥ ነገሮችን አጥርቶ ለማየት ይረዳል ። “ዐሥር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” ይባላል ። መታገሥ አያጸጽትም ። ትዕግሥቱ ፍርሃት ከሆነ ትዕግሥት መሆኑ ይቀራል ። ለመወሰን በዓይናችንም ፣ በጆሮአችንም ፣ በልባችንም ነገሩን ማጣራት ይፈልጋል ። ለመወሰን ከሸንጋይና ከአስመሳይ ሰዎች የተሳሳተ ነገር እንዳይገጥመን ማጣራት ይፈልጋል ። ሸንጋዮች እኛ ጋ ይቅለሰለሳሉ ፣ ዞር ሲሉ በትዕቢት ይራመዳሉ ። የማያልቅ ድራማ የሚሠሩብንን ሰዎች በጥንቃቄ መለየት ያስፈልጋል ። ለመወሰን ወሬዎችን ማጣራት ያስፈልገናል ። ወሬ የሚያመጡትን ራሳቸውን መፈተሽ ግድ ይላል ። የፈጠራ ወሬዎች ብዙ ናቸው ። ደግሞም እገሌን ጥሉልኝ እያሉ የጠብ ደቦ የሚፈልጉ ሰዎች ክፉ ወሬ ያመጣሉ ። ለመወሰን መጸለይ ፣ ከአዋቂዎች ጋር መመካከር ያስፈልጋል ። ውሳኔው በእኩለ ሌሊት አውጥተን የምንጥልበት እንዳይሆን ጊዜውን ማመቻቸት አለበት ። ውሳኔ በጀት ሊፈልግ ይችላል ። ገንዘባችንን ለሰላማችን ካልከፈልነው ለምን እንከፍለዋለን ? ሰጥቶ ማራቅ ፣ የማይላቀቁ ሰዎችን በበጀት መሸኘት ዕድሜን ያረዝማል ።
ለመወሰን የሚያስፈራን ነገር የተሻለ ነገር ያለ ስለማይመስለን ነው ። በጣም የተሻለ ሰው ፣ ስፍራና ሁኔታ አለ ። እግዚአብሔር ያንን ብቻ የፈጠረ እየመሰለን ከሚገድለን ነገር ጋር መኖር አይገባንም ። ብዙ ሟቾች ገዳያቸውን አቅፈው ኖረዋል ፣ ለምን አልወሰኑም ( ቢባል ሌላ ወዳጅ የሚገኝ ስለማይመስላቸው ነው ። ዋጋ ሊከፈልለት የሚገባ ኅብረት አለ ። አንዳንድ የሚከፈሉ ዋጋዎች ግን ተገቢ አይደሉም ። ደስ ሳይለው የሚሠራውን ሠራተኛ እያባበሉ ማኖር አደጋ አለው ። ለመወሰን የምንፈራው ምን ይሉኛልን ስለምንሰጋ ነው ። ኑሮው የእኛ እንጂ የሰዎች አይደለም ። ዓለም የሚውለው በሌላው ገመና ነው ። የዜና አውታሮች ሁሉ የሚያወሩት ስለ ራሳቸው ድርጅት ሳይሆን ስለ ሌላው ነው ። ቢቢሲ ስለ ራሱ አውርቶ አያውቅም ። እኛም እንወስን ሰዎችም ያውሩ ብለን መናቅ አለብን ። ለመወሰን የምንፈራው አጉል ሰዎች የአንድ ነገር ጥገኛ ስለሚያደርጉን ነው ። አሁንም እያስፈራሩን ስለሚኖሩ ነው ። ሁልጊዜ እየፈሩ ከመኖር አንድ ጊዜ ወስኖ የሚመጣውን መቀበል ያስፈልጋል ። ለመወሰን የምንፈራው ያለ ልክ ወደ ኑሮአችን ሁሉንም ሰው ስለምናቀርብ ነው ። ግርግር ፍቅር ሳይሆን ሱስ ነውና ጭር እንዳይልብን መወሰን እንፈራለን ። የሥራ ዕድሎች እንዳይዘጉ ፣ ባለሥልጣኖች እንዳያኮርፉ በደጅ የሚያድሩ መወሰን ያልቻሉ ብዙ ሰዎች ናቸው ። ሰነፎች ማን ያግዘኛል ?ፈሪዎች ማን ይናገርልኛል !ሆዳሞች ማን ያበላኛል ? ብለው አይወስኑም።
ውሳኔ እግዚአብሔርን ይዘን የበሽታችንን ዕድሜ የምናሳጥርበት ነው ። ስንወስን መንፈስ ቅዱስ ያግዘናል ። ከዘመናት ሸክም እንላቀቃለን ። ሰዎች በራሳቸው መቆም እንዲችሉ እናግዛቸዋለን ። የሚመጣውን ነገር ለመቀበል ጀግኖች እንሆናለን ። መወሰን ደስተኛ ያደርገናል ። እያስፈራራን ሰዎችን ከማኖር ፣ እየፈራንም ከመኖር ይገላግለናል ። ቍጣን በዘለቄታው ለማብረድ መወሰን ወሳኝ ነው ።
ይቀጥላል
መጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም.