ቍጣን ለማብረድ
“በእያንዳንዱ የተጠራቀመ ሀብት ውስጥ ያልተከፈለ የድሀ ጉልበት አለ” ይባላል ። ብዙ ሀብቶች ደስታ የላቸውም ፣ የድሆችን ጉልበት በግፍ ስለወሰዱ የሕሊና ዕረፍትን አይሰጡም ። ትርፍ ነገር ለማግኘት ሲሉ የድሆችን ዋና ነገር የሚሰርቁ ባለጠጎች አያሌ ናቸው ። ድሀ ለሞት ሲጠራ ለመብል አይጠራም ። ነገሥታትን የሚጠብቅ ፣ አገርን የሚያስከብር ፣ ሕንፃውን ፣ መንገዱን የሚሠራ ድሀ ነው ። ድሀ ሞቶ ባረፈው የሚባል ፣ ሕይወትን የሚመኝለት ያጣ ነው ። ብዙ ሰጥቶ ጥቂት መቀበል የማይችል ድሀ ነው ። ድሀ የሚሰጠው ስለሌለው ራሱን ይሰጣል ። በዚህም በአምሳለ ድሀ የመጣውንና ራሱን ለሁሉ የሰጠውን መድኃኔ ዓለምን ይገልጣል ። የገንዘብ ድሀ የጥበብ ድሀ ማለት አይደለም ። ይህች ዓለም ከተማረው ድሀ ያልተማረውን ባለጠጋ መስማት ስለምትፈልግ ብዙ ጥበብ አባክናለች ። በድሀ ጉልበት የጠነከሩ አገራትና ባለጠጎች ሰውን ገለል የሚያደርግ ቴክኖሎጂ እየፈለጉ ነው ። ለመውጣት ድሀው መሰላል ነበረ ፣ ከወጡ በኋላ ግን ይገፈትሩታል ። በዚህ ዓለም ላይ ዋናና ትርፍ ፍጡር የለም ። መቀነስ አለበት የሚባል እንኳን ሰው ቅጠልም ሊኖር አይገባውም ። ፍጥረት ተደጋግፎ የሚቆም ነውና ሁሉም ፍጥረት አስፈላጊያችን ነው ። ኗሪና አኗኗሪ የለም ። የመኖር መብትን ያገኘነው ከእግዚአብሔር ነው ። ሁሉም በዕድሜ ምጽዋት ያደረና የዋለ እንጂ በራሱ ሕይወተ ባሕርይ የቆመ የለም ። የእስትንፋሳችን ጌታ እግዚአብሔር ነው ።
በአገራችንም፡- “የድሀ ጉልበት በጎመን ዘር ያልቃል” ይባላል ። ጎመን ዘር እኔ በማውቀው ዘመን ስሙኒ ወይም 25 ሣንቲም ይገዛል ። ቀኑን በሙሉ ሲወቀጥ ይውላል ። ጎመን ዘሩ ለምጣድ ማሰሻ የሚውል ነው ። የድሀ ጉልበት ለትንሽ ነገር ብዙ ይባክናል ። ድሀ የተባለ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የዕድሜ ድሀ የሆነ ሰው ለትንሽ ጉዳይ ትልቅ ዋጋ ይከፍላል ። በመንገዱ ከገጠሙት ጋር ሲከራከር ይውላል ፣ መንገዱን ረስቶ ጥላቻ ባሰመረለት መንገድ ይጓዛል ። ሁሉን ያምናል ፣ ሁሉን ለመሆን ይፈልጋል ። ምኞቱ ዳር የለውም ፣ ሁሉን ማድረግ እንደሚችልም ይሰማዋል ። ራሱን በጣም ይሰማል ፣ ወላጆቹን እንደማያውቁ ይገምታል ። በራሱ መቆም ስለሚፈልግ ምርኩዞቹን ከማስቀመጥ ይወረውራል ። የዕድሜ ድሀ የሆነ ሰው ክልከላን እንደ ጭቆና ያየዋል ፣ ሕግን እንደ አጥር ይመለከተዋል ። የዕድሜ ድሀ የሆነ ሰው በዋዛ ፈዛዛ ነገር ጊዜውን ይጨርሳል ፣ በሌሎች ድካም እርሱ ተሞላቆ መኖር ይፈልጋል ። ጊዜውንና ጉልበቱን የሚያባክነው በማይረባ ነገር ነው ። የእውቀት ድሀም ባለማወቅ መንገዱ ዓመት እንደሚፈጅ ፣ ቢያውቀው ግን በዕለት እንደሚደርስ አይገነዘብም ። ለዚህ ዓለም ኑሮ ብልሃት ፣ ጸሎትና መንፈሳዊ ምሪት አስፈላጊ መሆኑን አይረዳም ። ኑሮው በንጽጽር የተሞላ ነው ። የሚያስተምሩትን እየጠላ መጠቀሚያ የሚያደርጉትን ይከተላል ፣ ገንዘቡንም ላዝማሪ ለዘዋሪ ፣ ላወዳሽ ላስለቃሽ ይጨርሳል ። ሀብታም ለመሆን የሚያስብ አስቀድሞ መማር አለበት ። ገንዘብን ያለ እውቀት ማስተዳደር አይቻልምና ።
ለማይረባ ነገር ኃይልን ማባከን አይገባም ። የትልቅ ሰው መገለጫው ጠብን መናቅ ነው ። ያልተገሩ ሰዎች የሚሰጡንን ስም ሁሉ ቆሞ መስማት ዋናውን ተልእኮ መርሳት ነው ። በምንም መንገድ ነገ ላይ የሚኖረው ሥራ እንጂ ስድብ አይደለም ። መሥራት ያልቻሉ የመሳደብ ብቃት ይኖራቸዋል ። ይልቁንም እንዳይሳደቡ ተብሎ በጀት የሚባጀትበት ምድር የእኛ አገር ነው ። የሃይማኖት አባቶች ፣ የአገር አስተዳዳሪዎች እንዳይሳደቡ ብለው ተሳዳቢዎችን ይደጉማሉ ። ገንዘብ አፍ ያሲይዝ ይሆናል ፣ የጎረሰው ሲያልቅ ግን ስድብ ይጀመራል ። በገንዘብ ፍቅርን መግዛት አይቻልም ። በሥራችን እስከ ተማመንን ድረስ ስለ አሉታ መጨነቅ የለብንም ። ከምስጋና ባሻገር ያሉ ነቀፋዎች ግን ይጠቅሙናል ። ቀጣይ ሥራችንን በጥራት እንድንሠራ ያደርጉናል ። ይሉኝታ ያላቸው ሰዎች ስህተታችንን አይነግሩንም ፣ ቀናነት የሌላቸው ግን እንኳን የተሳሳትነውን ያልተሳሳትነውንም ይነግሩናል ። ሚዛናዊ ሆነን መስማትና መታረም ይገባናል ።
“የማትናከስ ከሆነ ጥርስህን አታሳይ” ይባላል ። ለሁሉ ነገር መልስ እሰጣለሁ ማለት አድካሚ ነው ። ጠላትን መናቅ ፣ አንዳንዶችን በዝምታ ማለፍ ትልቅነት ነው ። ሰው የሚያመሰግነንም የሚያዋርደንም በአቅሙ መጠን ነው ። ይልቁንም በዕድሜና በእውቀት የገፋው ሰው ከዕድሜ እንጭጮች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባት አይገባውም ። በዝምታ ማለፍ ለእርሱ ክብር ለተሳዳቢዎች ግን ውርደት ነው ። ታላላቆችን የሚሳደብ መጻሕፍት የጻፉ ፣ ንግግር ያደረጉ ሁሉ ቅስማቸው ተሰብሮ ፣ በጸጸት የሚኖሩ ናቸው ። ስሜት ዛሬ ላይ ትክክል ናችሁ ሲለን ለዘላለም ግን መሳሳታችንን ይነግረናል ። መፎከር መሸለል አስፈላጊ አይደለም ። ውሳኔዎቻችንን ስንወስን ማሳወቅ ፣ እቅዶቻችንን በየሜዳ አለመዝራት ይገባናል ። ይህን አገኘሁ እያልን ማውራት ፣ ቤት ሠራሁ መርቁልኝ ማለት ይህ ሁሉ ያለ መብሰል ምልክት ነው ። በሚረባው በማይረባው ነገር ፍርድ ቤት ሰውን ማቆም የራስንም ጊዜ መግደል ነው ። ወዳጅን ትቶ ጠላትን እያሰቡ መዋል ቀንን ማበላሸት ነው ።
ኃይል እንዳይባክን የሚያስፈልጉን ነገሮች አሉ ። እኛ የምንኖረው ለራሳችን ዘብ ስለቆምን ሳይሆን ፈቃደ ሥላሴ ስለሆነ ነው ። የሰዎች ፉከራ የሚያጨልመው ሕይወትን አልተቀበልንም ። የሕይወት ብርሃን ከግድቦች ሳይሆን ከሕይወት ምንጭ ከእግዚአብሔር የሚገኝ ነው ። የተፈጠርንበትን ዓላማ መለየት ፣ ራእያችንን ማወቅ አለብን ። አውሬ እንኳ ከሺህ መንጋ አንዷን አይቶ ለመያዝ ይሮጣል ። አጠገቡ የተሻለ ቢኖሩም እነርሱን አይዝም ። አብራው በመሮጥ የደከመችውን ይይዛል ፣ መንገዱ ላይ የሚያገኛቸውን ለመያዝ ቢሞክር ግማሽ ጉልበቱን ጨርሷል ፣ አዲስ ሯጭ ይገጥመዋል ። ያየነውን ፣ ያየልንን ፣ የታየልንን ለመያዝ መሮጥ አለብን ። በየመንገዱ የሚገጥሙንን ዕድልም እንቅፋትም መመርመር አለብን ። ኃይላችን እንዳይባክን አባወራዎች በትዳር ፣ አሠሪዎች በመሥሪያ ቤት ፣ ሽማግሌዎች በእርቅ ፣ ገዥዎች በአገር አስተዳደር ፣ ወዳጆች በጓደኝነት ፣ አፍቃሪዎች በታሪክ የገጠማቸውን ነገር ማወቅ ያስፈልጋል ። ቍጣችንን ለማብረድ ለማይረባ ነገር ኃይሌን አልጨርስም ማለትን መልመድ ያስፈልጋል ።
ይቀጥላል
መጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም.