የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -3

ቍጣ የሚመጣባቸው ብዙ ምክንያች አሉ፡-

በራስ መናደድ

ሰዎች ይሰሙናል፣ ልባችን ግን አይሰማንም ። ልባችን ለልባችን ብዙ መክሮታል ። ነቢይ በገዛ አገሩ አይከብርምና ልባችን ሊሰማን አልቻለም ። በሕይወታችን ውስጥ የምንወደው ሌላ ነው፣ የምንሆነው ሌላ ነው ። ልባችን ጽድቅ እያየ እግራችን ኃጢአት ይረግጣል ። ሽሽታችን ውጤታማ አልሆን እያለን ፣ ደግመን እንወድቃለን ። ብዙ ጊዜ የቃላችን እስረኞች እየሆንን ካላሰብንበት እንውላለን ፣ ቃል መግባት አንፈልግም ግን እናደርገዋለን ። በትክክለኛ ቦታ ላይ ሳይሆን በስሜት በረቱን ቦታ ላይ ገንዘባችንን ፣ ጊዜአችንን እናባክናለን ። ርቀትን ጠብቀን ስለማንጓዝ መጋጨት ይፈጠራል ። ትላንት የሠራሁትን እንዴት ዛሬ እደግመዋለሁ በማለት በራሳችን በጣም እንበሳጫለን ።

ከራስ ወዳዶች ጋር መኖር

ራስ ወዳዶች አይሞቱም ፣ ሌላውን ግን ያዳርሱታል ። በራሳቸው ፍቅር የተለከፉ ፣ ለራሳቸው መሶብ ሙሉ ለሌላው ግን ቁራሽ አይድረስ የሚሉ ራስ ወዳዶች የቍጣ ምክንያት ናቸው ። ሰው አመመኝ ሲል እኔንም አሞኛል ፣ ሰው ቸገረኝ ሲል እኔም ስላልተናገርሁ ነው እንጂ በጣም ቸግሮኛል የሚሉ ያለ ማቋረጥ ስለ ራሳቸው የሚያወሩ ፣ የሌላውን ስሜትና ጥቅም የማይጠብቁ ራስ ወዳዶች የቍጣ ምክንያት ይሆናሉ ። ለራሳቸው ከጫፍ አገር ድረሱልኝ የሚሉ ለሌላው ግን ተነሥተው ውኃ የማያቀብሉ ፣ መልካም እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ መልካም ማድረግ ግን የማይፈልጉ ራስ ወዳዶች አስፈሪዎች ናቸው ። ከእነዚህ ሰዎች መራቅ ካልቻልን ዕድሜአችን ሊያጥር ይችላል ። ወይም አጉል ነዋሪ እንሆናለን ።

ቅንዓት

ቅንዓት ሳናውቀው የሚቆጣጠረን ነው ። ጥርሳችን እየሳቀ ያ ሰው ባገኘው ነገር ውስጣችን ስለት የሚስል ከሆነ ከባድ ነው ። ቅንዓት የእኔ ብቻ ይሁን የሚል ሳይሆን የእኔ ካልሆነ የማንም አይሁን የሚል ገዳይነትም አለው ። ቅንዓት ቍጠኛ ያደርጋል ። ቅንዓት ራሱ ርኵስ ነውና ሰዎች ርኵስ ፣ ልክስክስ ሆነው ይታዩታል ። ለንጹሖች ሁሉ ንጹሕ ነው ፣ ለርኵሳን ሁሉም ነገር የረከሰ ነው እንደሚባል እንዲሉ ለቀናተኞች ያ ሰው መጥፎ ግብር ሠሪ ሁኖ ይታያቸዋል ። ሰይጣን ለወዳጆቹ የሚጋብዘው ፊልም አለ ፣ እርሱ በቅንዓት መነጽር የሚታይ ሲሆን የሚታየውም ጻድቁን ሰው ርኵስ አድርጎ የሚያሳይ ነው ። ብዙ ትዳር የፈረሰው በቅንዓት ነው ። ቅንዓት በአጋንንት ቁጥጥር ሥር መዋል ነው ። ቅንዓት ፍቅር አይደለም ፣ ፍቅር አይቀናምና ።

አትኩሮት መፈለግ

አትኩሮትን መፈለግ ከልጆች እስከ አረጋውያን ድረስ የሚታይ ጠባይ ነው ። ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች አትኩሮት ያጡ ሲመስላቸው አስደንጋጭ ነገር መፍጠር ይጀምራሉ ። እንክብካቤአችን የቆመ ወይም ወደ ሌላ የዞረ ሲመስላቸው መነጫነጭ ፣ አመመኝ ማለት ይጀምራሉ ። አጠገባቸው ካለው ሰው ጋር በመጣላት ገላጋይ ይፈልጋሉ ። ይህ ትልቅ የሕሊና ስቃይ ያለው ፍላጎት ነው ። አትኩሮትን የለመዱ ሰዎች ከአደባባይ ሲርቁ የሞቱ ያህል ይሰማቸዋል ። ሚዲያ ላይ መታየት የለመዱ ያንን ካጡ በፍርሃት መናጥ ይጀምራሉ ። ይህ ዓለም ትንሽ ተደብቀው ቢኖሩበት መልካም ነው ። እዩኝ እንዳሉ ደብቁኝ የሚባልበትም ጊዜ ይመጣልና ። አትኩሮትን ፈልገው ያጡ ወገኖች ብስጩና ቍጠኛ እየሆኑ ይመጣሉ ።

እንዳሰቡት አለመኖር

እኛ እንዳሰብነው ቤተሰቦቻችንም እንዳሰቡልን ሳይሆን እግዚአብሔር እንዳሰበልን እንኖራለን ። የእርሱ አሳብ ይበልጣል ። ብዙ ሰው አንድ ቀን እሄዳለሁ ብሎ የፈረንጅ አገር ካርታን ሲያጠና ይኖራል ። ራሱን እዚህ ሲያገኘው ግራ ይጋባል ። ወደ ሰው አገር የሄደውም ያሰበውና የገጠመው ሲለያይበት ለጭንቀት ይዳረጋል ። የእናቱ ቤት ያልደላውን የሰው አገር ይደላኛል ብሎ ማሰቡ ቀድሞም አለማወቅ ነው ። እንደ ለፉት መጠን ያላገኙ ፣ ያልተከበሩ ፣ ሥራቸው እውቅና ያልተሰጠው ብዙ አዋቂዎች ብስጩ ይሆናሉ ። ትዳርን እናት ፈልጎ የገባ ባል ሚስት ስትገጥመው ብስጩ እየሆነ ይመጣል ። እንደ ድመት እንክብካቤና ምቹ ነገር ፈላጊ ትዳሩ ሊጎዳበት ይችላል ። ምክንያቱም ትዳር የጋራ ፍቅር ነውና ። ምንም ጥሩ ብትሆን ሚስት እናት አትሆንም ። እናት ያለ ምክንያት ያለ መጠበቅ የምትወድ ስትሆን ሚስት ግን ፍቅርን ትፈልጋለች ። ነገሮችን በልክ ለማየት ማንበብ ፣ ታሪክን ማወቅና ከአዋቂዎች ጋር መዋል ያስፈልጋል ። እንዳሰቡት አለመኖር ቍጡ ያደርጋል ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ