የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -4

ቍጣ የሚመጣባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-

የሌሎችን ጭካኔ ማየት

ይህ ዓለም በጨካኞች እጅ ወድቋል ። በሰው ሠራሽ ረሀብ የሚሰቃዩ ምስኪኖች ፣ በቦምብ የሚጋዩ ሕፃናት የዕለት ዜና ናቸው ። የምድር ገዥዎች የተሰጣቸውን አደራ ባለመወጣት ፣ እግዚአብሔር የፈጠረው ላይ እንዲህ በመጨከን ይዝናናሉ ። የየትኛውም ድሀ አገር ገዥ የገዛ ልጆቹ ሰላም ባለበት አገር እንዲማሩ ሲያደርግ በድሀው ልጅ ግን ቁማር ይጫወታል ። ፖለቲከኞች በራስ ወዳድነት ስሜት ተይዘው ማየት ፣ ሲገለባበጡ ምንም የማይጨንቃቸው ዓይናቸውን በጨው ያጠቡ መሆናቸውን መመለከት ዕለታዊ ትዝብት ነው ። አሁንም ለሚሞተው ድሀ አስቦ እስቲ ዘንበል እንበል የሚል መጥፋቱ ተመልካቹን ውስጣዊ ቍጣ ይጭርበታል ። የጭካኔ ተግባራት በብዙ ቦታዎች እየበዙ ናቸው ። በገዛ ትዳራቸው ለሞት የሚዳረጉ ፣ በወላጆቻቸው የሚጎዱ ልጆች እየበዙ ነው ። ይህን ሁሉ ግፍ መቀበል ያቃተው ሕሊና ቍጡ ይሆናል ። እውነተኛ መሆን እንጂ እውነትን ከዚህ ዓለም መፈለግ አድካሚ ነው ። የሐሰት ኑሮ የሰለቻቸው ሰዎች ቍጡ ናቸው ። የልጆቻቸውንና የወዳጆቻቸውን የድራማ ሕይወት ማየት ተራራ የመግፋት ያህል የከበዳቸው ሰዎች ቍጠኛ ይሆናሉ ። ምክራቸውን ሊሰሙ ካልቻሉ ሰዎች ጋር የሚኖሩ ፣ የወደፊቱ ክፉ ውጤት የሚታያቸው ቍጡ መሆናቸው የታወቀ ነው ። ያለ እግዚአብሔር ጸጋ የሰው ቍጣ ብቻውን የመለወጥ አቅም የለውም ።

የደከምንላቸውን መክሰር

ራስን ሲጥሉ ልጅም አይወድም ። ራሱን ጥሎ ልጁን የሚያሳድግ ፣ ልጁ ትልቅ ቦታ ሲደርስ በወላጁ ያፍርበታል ። እንደ ልጅ ከዳተኛ የለም ። ውደዱ ተብሎ ፍርጃ ወድቆብን እንጂ ሸርታታና ጥቅመኛ ቢኖር ልጅ ነው ። እኛም ሁሉም ልጃችን እንደሆነ ለማሰብ ዘረኝነት ይታገለናል ፣ ጠባብነት ያፍነናል ። ቤታቸውን ሸጠው ልጃቸውን የሚያስተምሩ ውጤታማ አይደሉም ። ልጅን አዋቂ የሚያደርገው ትምህርት ቤቱ ሳይሆን ትጋቱ ነው ። ትልልቅ ትምህርት ቤቶች ትልልቅ ጉድ ያለባቸው ናቸው ። ያ ልጅ ቤት ተሽጦ ተማር ሲባል ጭንቀት ውስጥ ይገባል ፣ የነበረውን አቅም መጠቀም እያቃተው ወላጆቼን ቤት አልባ አድርጌ ባይሳካስ የሚል ፍርሃት ይይዘዋል ። መምህራንም የሚያገለግሉትን ሕዝብ ራሳቸውን ክደው እንጂ ራሳቸውን ጥለው ማገልገል አይገባቸውም ። ወደ መንፈሳዊ አገልጋዮች የሚመጣው ሕዝብ ተጠቅሞ የሚጥል ፣ ያንን ክፉ ቀኑን አብረውት ያሳለፉትን አገልጋዮች እንደ ጠላት የሚያይ ውለታ በላ ነው ። በእውቀትም በአቅምም አገልጋዮች ከሚያገለግሉት ሕዝብ ማነስ አይገባቸውም ። አገልግሎት በእኛ አገር ክብር የለውምና ። የደከምንላቸው ዘረ ቆርጥም መሬት ሲሆኑ ቍጣ ይጀምራል ። ልጆቻችን እንኳን ሊፈልጉን ስንፈልጋቸውም ሲሸሹን የደከምኩት ለማን ነው ? በሚል ስሜት ኀዘን ውስጥ እንገባለን ። አይ ሞኝ ቀሪ ገንዘብ መድኃኔ ዓለም ብቻ ነው ።

ሁሉም ነገር አልፏል የሚል ስሜት

አርጅተው ገና ነኝ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ገና በጠዋቱ የመሸ የመሰላቸው ወጣቶችም አሉ ። እርጅና የአካል ሳይሆን የሕሊና ነው ። እግዚአብሔር ዋና ዕድሜና ቅራሪ ዕድሜ ብሎ አልሰጠንም ። እያንዳንዱ የዕድሜ እርከን ዋጋ አለው ። የምንሠራውን ስላላወቅን እንጂ ሁሉም ዕድሜ ሥራ ተሰጥቶታል ። ሽምግልናም ትልቅ የሥራ ዕድሜ ነው ። እስካለን ድረስ ምንም ያለፈ ነገር የለም ። ዛሬም መማር ይቻላል ። አንድ ሊቀ ጳጳስ በ54 ዓመታቸው ቋንቋ ማጥናት ጀምረው አሁን የስድስት የዓለም ቋንቋ ተጠያቂ ናቸው ። በዘጠና አምስት ዓመታቸው ሃያኛ ቋንቋ የሚያጠኑ ሰው አሁንም በውጭ አገር አሉ ። እኒህ የካህን ልጅ ኢትዮጵያዊ ናቸው ። ፀሐይን በገባዖን ያቆመ የኢያሱን አምላክ ይዘን ያለፈ ጊዜ የለም ። አሁንም በጣም ውብ ፣ ንግግራችሁ የሚማርክ ነው ። ፍቅር ያለ ቦታው አባ ጨጓሬ ነው እንዲሉ የማይገባቸው ሰዎች ላይ ስላፈሰሳችሁት እንጂ እናንተ ተፈላጊ ሰዎች ናችሁ ። ወላዲተ አምላክን ራሳችሁን ተቀበሉት ። እግዚአብሔርን የተስማማውን ዕድሜና ውበታችሁን ማንም ሊያጣጥለው አይችልም ። ተመስገን።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 18 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ