ቍጣ የሚመጣባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-
እንከን አለመፈለግ
ባለሙያና ጥንቁቅ ሰዎች ብዙ ጊዜ ቍጡ ናቸው ። እንደ እነርሱ ያለ ጠንቃቃና ባለሙያ አጠገባቸው ስለማያገኙ ይበሳጫሉ ። ሰዎች የማወቅ ፣ በሥነ ሥርዓት የመኖር ዓላማ ሲያጡ ቍጠኛ ይሆናሉ ። እያንዳንዱ አቀማመጥ ፣ የቤቱና የቢሮው ሥነ ሥርዓት የተለካ መሆን አለበት ። አብረዋቸው ያሉ ሰዎችም ነጻነታቸውን ያጡ ስለሚመስላቸው ደስተኛ አይሆኑም ። አምነውበት ሳይሆን ቍጣን በመፍራት አንዳንድ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እነዚያ ትጉ ሰዎች ይበልጥ ይበሳጫሉ ። ዓላማቸው ማስተማር እንጂ ማስጨነቅ አይደለምና ። ነገር ግን ሁልጊዜም ባይሆን አንዳንድ ጊዜ ልጆች በቤታቸው ፣ ቤተሰብ በጎጆአቸው እንደ ፈለጉት እንዲሆኑ መፍቀድ አለብን ። ቀጣዩ ዓለም የሥነ ሥርዓት ነውና መንገዱን ማሳየትም ይገባል ። ሥራ መሥራት አለብህ ሲሉት የሚቀየም ፣ ሙያ ላስለምድህ ሲሉት ስልኩን ዘግቶ የሚጠፋ ምስኪን ትውልድ ፣ በምኞት የሰከረ ወገን ይዘናልና ብስጭትን መቆጣጠር ይገባል ። የሚሰጠን ስም እገሌ ቍጡ ነው የሚል መሆን የለበትም ። አንዳንድ ነገሮችን አይቶ እንዳላየ ማለፍ ፣ ሠራተኞቻችን ሲያጠፉም የብክነት በጀት መያዝ ይገባል ። ምክንያቱም ሠራተኛ ያስገባነው እኛ ስላቃተን ነውና ።
ዕድሜ የሚያመጣው
እግዚአብሔር የረዳቸው ሰዎች ካልሆኑ ዕድሜ ሲገፋ ቍጡነት ይመጣል ። ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ ከአባቶች ይልቅ እናቶች ቍጡ እየሆኑ ይመጣሉ ። በሕይወታቸው ሺህ ጓደኛ ፣ ሺህ ሠራተኛ አይተዋል ። ከፍቅር ይልቅ ለኃይል ሲገዛ አስተውለዋል ። በዚህ ምክንያት እግዚአብሔር የሚወደውን ሳይሆን ሰው የሚፈልገውን ለመስጠት ይቆርጣሉ ። ሰው ወደዱትም ጠሉትም መሄዱ አይቀርም ። ይልቁንም የባዳ ፍቅር ማሰሪያ ገመድ እያጣ ፣ አብሮ ያሳለፈውን እየረሳ ስለሚመጣ መጨነቅ ያቆማሉ ። ምንም ደግ ቢሆኑላቸው ከደግ ወዳጅ ክፉ ዘመዳቸውን ይመርጣሉ ። በዚህ ምክንያት በዕድሜ የገፉ ሰዎች በቍጣ የሚናገሩና የሚኖሩ ይሆናሉ ። ሲተርቱም፡-
የባቄላ ጠላ የጤፍ አሹቅ የለው ፣
ምን ቢፋቀሩ የባዳ ውል የለው ።
በክርስቶስ መዛመድ ከሁሉ ይበልጣል ። ከማይጠፋ ዘር መወለድ ያስደስታል ። በዚህ ዘመን ግን መንፈሳዊ ዝምድናን የሚያከብር እየጠፋ ነውና ያስፈራል ። መንፈሳዊ ሕይወት የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያስተላልፍ ንጹሕ መስተዋት ነውና ሰውን ሁሉ መውደድ ፣ በይቅርታ ማለፍን ያስተምረናል ።
መርካት አለመቻል
በዚህ ዓለም ላይ የሚያረካ ነገር ማግኘት ከባድ ነው ። ሰው ሁሉ ከልፋቱ እርካታን ይጠብቃል ። ከትምህርቱ ፣ ከሥራው ፣ ከትዳሩ ፣ ከልጆቹ እርካታን ይፈልጋል ። የደከምንለት ነገር የተፈጥሮ ግዳጃችንን የተወጣንበትና የጣርንበት በመሆኑ ከጸጸት ያድናል ። መርካት ግን በእግዚአብሔር ብቻ የሚገኝ ነው ። በኖርንላቸውና በሚኖሩልን ሰዎች እርካታን ብንፈልግ ላናገኝ እንችላለን ፣ የበቃኝ ኑሮ የመደላደል ኑሮ በእምነት ብቻ የሚገኝ ነው ። ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ የሚለው ትእዛዝ የዓለም ደስታ ጊዜያዊ እንደሆነ ሁልጊዜ መደሰት ግን በጌታ ብቻ መሆኑን የሚገልጥ ነው ። ትልልቅ የእርዳታ ሥራዎች ብንሠራም ፣ ለአገር ብዙ ብናበረክትም የምንፈልገውን እርካታ ላናገኝ እንችላለን ። ጥረታችን በርግጥ መኖራችንን ይመሰክሩልናል ። በጨበጠው ነገር እርካታ ያጣ ሰው ቍጡ እየሆነ ይመጣል ።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 19 ቀን 2018 ዓ.ም.