የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -6

ቍጣ የሚመጣባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ፡-

መጠበቅ

“የባዳ ሞኝ ከልጅህ እኩል አድርገኝ ይላል” ይባላል ። ምንም መልካም ወዳጅ ቢሆን ያ ክፉ ልጅ ለቤቱ ይበልጣል ። መጠበቅ የብዙ ሰውን ሕይወት ያፈራረሰ ነው ። ሌላውን የሚጠብቅ ሰው የራሱን አይሞክርም ። የሰው ሰጪው አንድ አምላክ ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ሰጥቶ የሚከለክል ፣ እግዚአብሔር ሳይሰጥ የሚቸር ማንም የለም ። ባለሥልጣን ዘመዱን ፣ ባለጠጋ ወገኑን ብዙ ሰው ይጠብቃል ። ለእነርሱ የሰጠ የሁሉ አምላክ መሆኑን ማመን አለበት ። የሌሎችን ስንከጅል ሳናውቀው ጥላቻንና ቂምን እናተርፋለን ፣ ቅንዓትም ሊዋጋን ይጀምራል ። የእኔ ዕድል ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው ብሎ መጸለይ ግን እሮሮ ካለበት ከሰው ስጦታ ያድናል ። እስኪወዱት ድረስ አድፍጦ የሚጠብቅ ሞኝ አለ ። ካልወደድነው በቀር የሚወደን ማንም የለም ። የሚወደንን የምንጠብቅ ከሆነ ዘመናችንን በሙሉ አንድ ወዳጅ አናገኝም ። ጓደኛ መሆን እንጂ ጓደኛ መፈለግ ውጤታማ አይደለም ። ፖሊስ ማማው ላይ ሁኖ እንደሚጠብቅ ስልካቸውን ይዘው የሚጠብቁ ካልተደወለ የሚቆጡ ብዙ ሰዎች አሉ ። ሰው ሁሉ በራሱ ጉዳይ በተያዘበት ፣ ራስ ወዳድነት በሰፈነበት ፣ ላለው ማሸርገድ ባየለበት በዚህ ዘመን መጠበቅ ጉዳት አለው ። በዚህ ዓለም ላይ ሰዎች በረከቶቻችን ሊሆኑ ይችላሉ ፣ ሕይወታችን ግን ክርስቶስ ነው ። መጠበቅ በጸሎት ኃይል እንዳናምን ያደርገናል ። ስጦታ ከላይ መሆኑንም ያስረሳናል ። መልካም ካደረግንለት ሰውም ምስጋና ቀርቶ ልከኛ ስድብ ካገኘን ዕድለኞች ነን ። ክፉዎች ሰውን ክፉ ለማድረግ አቅደው የተነሡበት ዘመን ይመስላል ። መጠበቅ የጠበቅነውን ስለማናገኝ ቍጡ ያደርገናል ።

የሰይጣን ግልጽ ውጊያ

ሰይጣን ከዚያ ሰው እንድንጠብቅ ያደርገናል ፣ ያን ሰው ደግሞ እንዳይገኝ በማድረግ ይዋጋዋል ። የዚያን ጊዜ ብቻዬን ነኝ ፣ የምሮጠው በከንቱ ነው የሚል ተስፋ መቍረጥ ውስጥ እንድንገባ ያደርገናል ። ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጣ በኋላ ጠብ ጨምሯል ። ስልክ ባለ መነሣቱ ብቻ ትዳር ፈርሷል ፣ የብዙዎች ግንኙነት በየቀኑ ጦርነት ሆኗል ። ከቻልን ሰዎች ከደወሉ ወዲያው አሊያም ቆይተን መልስ መስጠት መልካም ነው ። ብዙ የለፋንለት ግንኙነት ሊፈርስ ይችላል ። ፈላጊ አክባሪና ስጦታችን ነውና ለሚደውሉልን ክብር መስጠት አለብን ። ብዙ ዕድሎች ስልክን ባለማንሣት ያልፋሉ ። ባይፈልግ ነው በማለት ሰዎች መንገድ ይቀይራሉ ። ያ ሰው ያለበትን ሁኔታ መረዳት መቻል ብስለት ነው ። በአጠቃላይ በጣም ስስ የሆንበት ዘመን ነው ። ገና ካሁኑ እንዲህ ስስ ሆነን እንዴት ልንከርም ነው ( ጌታ ሆይ! ልበ ሰፊ ፣ ነገር አላፊ አድርገኝ ብለን መጸለይ አለብን ።

የክብር መንገድ ማድረግ

ሰዎች ክብርን ይፈልጋሉ ። ትክክለኛው የክብር መንገድ ሰማይና ምድርን የፈጠረውን ጌታ ማክበር ነው ። ሌሎችን የሚያከብር ሰው ይከበራል ። የምናጭደው የዘራነውን ነውና ክብርን ስንዘራ ክብርን እናጭዳለን ። እያንዳንዱ ሰው ባለጠጋና ባለሥልጣን ስለሆነ ሳይሆን እግዚአብሔር ስለ ፈጠረው ክቡር ነው ። ክብር ወደ ኋላ የመጣለት ሳይሆን በተፈጥሮው ክቡር ነው ። ሁሉም ሰው የራሱን ክብር ይፈልጋል ። ካከበርነው ያንን ይመልስልናል ። ሰዎች ክብርን በተለያየ መንገድ ይፈልጋሉ ። በመቆጣት ፣ በጩኸት እንዲከበሩ ይፈልጋሉ ። ክብር ግን በመኮሳተር ፣ ሌሎችን በመናቅ ፣ ርቀትን በመጠበቅ የሚገኝ አይደለም ። መከበርና መፈራት ልዩነት አለው ። የሰው ትልቅ ዋጋው መፈራት ሳይሆን መከበር ነው ። መፈራትማ አራዊት በጣም ይፈራሉ ። እንደ ሰው መከበር እንጂ እንደ አራዊት መፈራት አንዳች ጥቅም የለውም ። ትዳርም ፣ ወዳጅነትም የሚቆየው በመከባበር ነው ። ክብር ሌላውን በማስጨነቅ የምንሰርቀው መክሊት አይደለም ። በትልቁ ክብር የሚገኘው በቅድስና ነው ።

ይቀጥላል

የካቲት 20 ቀን 2018 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ