የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -9

የቍጣ ውጤቶች

ጤና ማጣት

“ተናዳጅ እንጂ አናዳጅ አይሞትም” ይባላል ። ቍጣ ስሜትን ይጎዳል ፣ ለጭንቀት ይዳርጋል ። እንቅልፍ ይነሣል ፣ ሰላምን ያሳጣል ። ጤናን በብርቱ ያውካል ። በሽታ ከጠባያችን ፣ ከአኗኗር ዘይቤአችን ፣ ከአመጋገባችንና ከእንቅስቃሴአችን ጋር ግንኙነት አለው ። ቍጠኛ ሰው ለበሽታ ይጋለጣል ። ራሱን በብርቱ ይጎዳል ። ራሱን በመጉዳቱ የሚደነግጥና የሚለወጥ ሰው ያለ ይመስለዋል ። የሚያናድዱት ግን በእርሱ መንደድ ይዝናናሉ እንጂ ጤናውና ሕይወቱ ግድ የሚሰጣቸው አይደሉም ። ራስህን ከጣልከው ማንም አያነሣውም ። ራስህን ከጎዳኸው የሌሎች ድጋፍ አይጠግነውም ። ጤና እያለ እንደ ቀላል የሚታይ ሲሆን ከሄደ በኋላ ግን በውድ ዋጋ የማይገኝ ነው ። ከአገር እስከ ውጭ የሚንከራተቱ ብዙ በሽተኞችን ስናስብ ለጤናችን መጠንቀቅ እንዳለብን ይገባናል ። የጤና ነገር በአፋፍ ላይ እንደሚሮጥ ሰው ትንሽ ዝንፍ ካለ መመለስ ይቸግራል ። የሚያናድዱን ሰዎች አስቀድመን ሳናጠና የተወዳጀናቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ ። መወሰን ባለመቻላችንም የሕመም ዘመናችንን ያራዝሙታል ።

አብዛኛውን ጊዜ የምንበሳጨው በውስጣችን ቍጣ ስላለ እንጂ በርግጥ የሚያበሳጩን ሰዎች ገጥመውን አይደለም ፤ ምክንያቱም ከዕቃ ጋርም ተጋጭተን እንበሳጫለን ፣ ወርውረን እንሰብራለንና ። ሰዎችን ለመለወጥ ከመታገል ራስን መለወጥ ፣ ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ይገባናል ። ሰዎች ነጻ ፈቃድ ያላቸው በመሆናቸው በግብግብ ልንለውጣቸው አንችልም ። መንገዱን እናሳያቸዋለን እንጂ አንሄድላቸውም ። እያንዳንዱ የራሱን መዳን መፈጸም አለበት ። ልጆቻችንም ቢሆኑ በፈሪሀ እግዚአብሔር ፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲያድጉ ጥረት ማድረግ ይገባናል ። ከዚያ ባለፈ ነጻ ፈቃድ እንዳላቸው የሁሉም ነገር ውጤት ከፊት ለፊት እንደሚጠብቃቸው ማሰብና መረጋጋት አለብን ። እኛ እዚህ የደረስነው ማንም በግብግብ ሕይወታችንን ለውጦት ሳይሆን እግዚአብሔር አግዞን ነው ። ሰዎች እንዲለወጡ ለመንፈስ ቅዱስና ለጊዜ መተው ይገባናል ። የሚለወጡት ለእኛ መስሎአቸው እልህ ውስጥ እንዳይገቡ ተወት ማድረግ ይገባናል ።

የአካል ማጉደል

ቍጣ የሌላውን አካልና የራሳችንን አካል እንድናጎድል ሊመራን ይችላል ። በቍጣ የማይተካውን አካል ያጎደሉ በሕሊናና በሕግ የተከሰሱ ብዙዎች ናቸው ። የአንድን ሰው አካል ስናጎድል ሃያ ዓመቱ ከሆነ ሰማንያ ዓመት ቢኖር ስድሳ ዓመቱን የመከራ አድርገንበታል ። በማንም ሰው ሕሊና ላይ በማንም ሰው አካል ላይ የእኛ ክፉ አሻራ መቀመጥ የለበትም ። ሞትን በደስታ የምንጋፈጠው ፣ ጌታ ሆይ ቶሎ ና ብለን ይህን ዓለም የምንሰናበተው ማንንም ለመጉዳት አልኖርኩም ብለን ለራሳችን መናገር ስንችል ብቻ ነው ። ብዙዎች የሞት አፋፍ ላይ ሆነው በጣም ከሚሰማቸው ነገር አንዱ በትዕግሥት ማለፍ ሲገባቸው የወሰዱት የበቀል እርምጃ ነው ። የእግዚአብሔር ኃይልና በቀል እንደሚበልጥ ዘግይቶ ገብቷቸዋል ። በመጨረሻዋ ሰዓት የሚሰማን ብዙ ነገር አለ ። ለወዳጆቻችን ጊዜ አለመስጠታችን ፣ ለምንወዳቸው ፍቅራችንን አለመግለጣችን ፣ ለፈጠረን ጌታ አለመኖራችን ፣ በዘፈን ዘለን ሳንዘምር ጊዜ በማለቁ ፣ ሳንረዳቸው በስስት የጣልናቸው ዘመዶቻችን ፣ ራሳችንን እፎይታ ነሥተነው እንደ ተቅበዘበዝን መኖራችን ትልቁ ሕመም ይሆንብናል ። ቍጣን ማራቅ በሰላም ለማረፍም አስፈላጊ ነው ። በቍጣ ምክንያት የገዛ ሚስቱን አካለ ጎዶሎ ያደረገ ንዴተኛ አለ ። ሚስት አካል ናት ፣ ልጆች ግን የአካል ክፋይ ናቸው ። የገዛ አካሉን ያጎደለ ሰው በጸጸት ይጎዳል ። እንደ ተናደድን መልስ አለመስጠት ፣ እሳቱ ሲፋፋም ወጣ ማለት ከጸጸት ይጠብቃል ።

ግድያ

ያልታሰበ ግድያ የሚያመጣ ቍጣ ነው ። በወኅኒ ቤት በመግደል ተፈርዶባቸው የሚገኙ ወገኖቻችንን ብንጠይቅ በጊዜያዊ ስሜት ተነድቼ ይህን በማድረጌ ይጸጽተኛል ይላሉ ። ከእስሩ በላይ የሚሰማቸው ያንን ስህተት መፈጸማቸው ነው ። የተቆጣ ሁሉ ላይገድል ይችላል ፣ የገደለ ሁሉ ግን የተቆጣ ነው ። የሰው ልጅ መልአካዊ ባሕርይ ሲያዳብር እግዚአብሔርን ስለ አምላክነቱ ብቻ ያመሰግናል ። ሰዎችንም ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ይወዳቸዋል ፣ ይጠብቃቸዋል ። ትከሻ ለትከሻ እየተነካኩ ሰላምታ መሰጣጠት አስፈላጊ ነው ። በሩቅ ሰላም ማለትና በእጅ ብቻ መጨባበጥ አውሮፓውያን በወረርሽኝ በሽታዎች ያዳበሩት ጠባይ ነው ። ሥልጣኔ የወለደውም አይደለም ። ትከሻ ለትከሻ መሳሳም እኩያ ነን ማለት ነው ። ሰብአዊ ባሕርይ ሲኖር በእኩያነት እንቀራረባለን ። እንስሳዊ ባሕርይ ሲኖረን ያንን ሰው ለዝሙት እንፈልገዋለን ። አራዊታዊ ባሕርይ ሲኖር ያንን ሰው መብላት ፣ ማራቆት ፣ መዝረፍ ያስደስተናል ። ሰይጣናዊ ባሕርይ ሲኖረን ሃይማኖቱን እናስክደዋለን ። ቍጣ አራዊታዊ ባሕርይ ነው ። ያልተገራ ቍጣ ገዳይ ያደርጋል ፣ አንዳንዴም ልጅ ገዳይ ያደርጋል ። በመግደል የተፈረደባቸው የዕድሜ ልክ ፍርደኞች እንዲሁም የሞት ፍርደኞች ናቸው ። በገዛ ፈቃዳችን ኑሮአችንን እንዳንሰርዝ ቍጣን ማራቅ ይገባናል ። ደግሞም የተቆጣንበት ነገርና የወሰድነው እርምጃ አይመጣጠንም ። በውሻ ጠብ ሰው ገድለው ወኅኒ የገቡ ሰዎችን እናውቃለን ። በትንሽ ቃል ክብሬን ተዳፍሯል በማለት ተኩሰው የገደሉ ፣ አገር ካገር ቤታቸውን ጥለው የሚቅበዘበዙ አሉ ። ቍጣ በዐሥር ደቂቃ ትዕግሥት ያልፋልና ዞር እንበል ።

ይቀጥላል
የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ