የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በመልካም ሽምግልና መቀበር

“አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ።” ዘፍ. 15፡15 ።

“አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ ፣
የቀለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ ፤”

ይህ የኀዘን ቅኔ ፣ የኀዘን ሙሾ የቀረበው ለመምህር አካለ ወልድ ሠርፀ ወልድ ነው ። ሞታቸው በተሰማ ጊዜ በሸዋ ውሎ ተዋለ ። የወንድማቸው የልጅ ልጅ የሆኑትም ሴት ከላይ የቀረበውን የኀዘን ቅኔ አሰሙ ። መምህር አካለ ወልድ ከ1824-1912 ዓ.ም በዚህች ምድር ላይ ለ88 ዓመት የኖሩ ታላቅ ሊቅ ፣ ድንግል መነኵሴ ፣ ቅዱስ ባሕታዊ ፣ መፍቀሬ ደቀ መዛሙርት ፣ ለምእመናን የረሀባቸው ዱላ ፣ የሚናገሩት የነበራቸው አዋቂ ፣ ሙስሊምና ክርስቲያኑን በችግር ዘመን ሳያዳሉ የመገቡ የክርስቶስ እንደራሴ ነበሩ ። ገጽ አይተው የማያደሉ ፣ ነገሥታትን የሚመክሩና መንገድ የሚያሳዩ ፣ የቍጣ ሰይፍ ሲመዘዝ በትምህርት የሚያበርዱ እውነተኛ የመንጋ እረኛ ነበሩ ። መምህር አካለ ወልድ የአራቱ ጉባዔያት ሊቅ ፣ የቅኔ መምህር ፣ የዜማው አዋቂ ፣ አራት ዓይና ፣ ሊቀ ሊቃውንት ፣ የቀለም ቀንድ ነበሩ ። የቀለም ቀንድ መሆናቸውን ዐፄ ቴዎድሮስም መስክረዋል ። ዐፄ ቴዎድሮስ ብዙም የካህናት ፍቅር ያላቸው ባይመስሉም መምህር አካለ ወልድን ግን አድንቀዋል ፤ አድናቆታቸውም ዘመን ተሻጋሪ የሙገሳ ስም ሁኖ ቀርቷል ። ያደነቁትም ከጦር ጀግናቸው ከፊታውራሪ ገብርዬ ጋር በማነጻጸር ነው፡-

ይማሯል እንደ አካልዬ ፣
ይዋጓል እንደ ገብርዬ ፤

ብለዋል ። ንጉሡ በጦር ሜዳ ጀግንነትን ከሚቀዳጀው ወታደር ጋር ፣ መምህርንም አነጻጽረዋል ። መምህር ድንቍርናን የሚዋጋና ድል የሚነሣ ነው ። ተማሪ ሰብስቦ የሚያስተምር መምህር ፣ ወታደር ሰብስቦ ከሚዋጋ የጦር መሪ ጋር እኩል ተጋድሎ ያደርጋል ማለታቸው ነው ። ይህን የመሰከሩት ደግሞ የቤተ ክህነት እውቀት የነበራቸው ፣ በጦር ጀግንነት የታወቁ ፣ ሰውን አይተው መመዘን የሚችሉ ፣ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የደከሙ ዐፄ ቴዎድሮስ ናቸው ። በንጉሡ አፍ የተነገረው ይህ ሙገሳ ለመምህር አካለ ወልድ የጦር ሜዳ ኒሻን ነበር ።

መምህር አካለ ወልድ የሃይማኖት ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ ፖለቲካውን ተረድተው ሰላምን የሚፈጥሩ ፣ አገርን ከደም መፋሰስ ብዙ ጊዜ የታደጉ ፣ ነገሥታትን ያሸማገሉና ያስታረቁ ብእሴ ሰላም ናቸው ። መናኔ ንብረት ሁነው የተሰጣቸውን ርስት አንዱንም ለእኔ ሳይሉ ለደቀ መዛሙርትና ለሕዝብ ያከፋፍሉ ነበር ። በዐፄ ቴዎድሮስ ፣ በዐፄ ዮሐንስ ፣ በዐፄ ምኒልክ ቤተ መንግሥት የተከበሩና ተጠያቂ ሰው ነበሩ ። በአልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ ዘመንም ለሦስት ዓመታት ያህል ቆይተዋል ። መምህር አካለ ወልድ ብዙ መምህራንን ያፈሩ ሲሆን የመጀመሪያዎቹን ጳጳሳት አቡነ ይስሐቅን ፣ አቡነ አብርሃምን ፣ እንዲሁም ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስን ያስተማሩና ያወጡ ፣ ቍጥር የሌላቸውን ደቀ መዛሙርትም ያበረከቱ ባለ ውለታ ፣ ግን የተረሱ ሰው ናቸው ። መምህር አካለ ወልድ በተከሉት ፣ ባስተማሩበት በቦሩ ሜዳ ሥላሴ ይታወቃሉ ። የቀለም ቀንድ የሚል የሙገሳ ስም አግኝተዋል ። የተወለዱ በ88 ዓመታቸው ኅዳር 9 ቀን ቀን በዚህ ሰሞን አርፈዋል ።

“አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ ፣
የለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ ፤”

የቀለም ቀንድ ይሰበራል ። ምሁራን ድንጋይ አይችሉም ። ያልተማሩትና ክፉዎች በመግፋት የታወቁ ናቸው ። አገር አይለቁም ፣ ሊቁን ግን ይነቅላሉ ። አይሰደዱም ፣ አዋቂዎችን ግን ያሳድዳሉ ። የቀለም ቀንዶች ግን በቶሎ ይሰበራሉ ። ሥራ እንጂ ሴራ አያውቁምና ክፋት መሥራትን ይጸየፋሉ ። አትሮኖንስ ሥር እንጂ ሰደቃ/ገበታ ላይ መዋልን አይመርጡም ። መስቀልን እንጂ ካባን አይሹም ። ግን በቶሎ ይሰበራሉ ፣ ድንጋይ መሸከም አይችሉም ። አገር ለቀው የሚሄዱት ፣ አዝነው ዝም የሚሉት ፣ እንደወጡ የማይመለሱት ፣ ተበሳጭተው በቤት የሚቀሩት ሊቃውንቱ ናቸው ። መማር ዕዳ በሚመስልበት አገራችን ብዙ የቀለም ቀንዶች ድንጋይ ተጭኖባቸው ተሰብረዋል ። ክፉዎች ግን አንለቅም ብለው ስንቱን እየነቀሉት ይገኛሉ ። ሊቃውንት የክፉዎችን ያህል ስለማይጨክኑ ፣ የአገሬ ሰውም ጨካኝን አወዳሽ ሁኖ ስለሚኖር ደጎች የማይበረክቱባት አገር ተፈጥራለች ። የማሸማቀቅ ስልት ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል ። አዋቂውን አሸማቀው ፣ ያለ ስሙ ስም ሰጥተው በትልቅ ድንጋይ ይሰብሩታል ።

በመልካም ሽምግልና መቀበር ፣ ድንቍርናን ተጋፍቶ ፣ የተጣላውን አስታርቆ ፣ ጉልበተኞችን ዳኝቶ ፣ ደቀ መዛሙርትን ትቶ ማለፍ ነው ።

ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ