የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ

ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ ። አዳም ሲፈጠር የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሁኖ ተፈጥሯልና አዳምን ሊክስ መምጣቱን ለመግለጥ በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ ። የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ በሠላሳ ዓመቱ በፈርዖን ፊት ቆመ ፣ የወደፊቱንም የዓለም ዕጣ ተነተነ ። ሠላሳ ዓመት የሙሉ ሰው ዕድሜ ነው ። ለማግባትም ለመመንኮስም የውሳኔ ዕድሜ ነው ። ሠላሳ ዓመት የማፍራት ዕድሜ ነው ። ሰው እርሱን ከሚመስል ጋር ኅብረት ፈጥሮ የሚያፈራበት ፣ ወዳጅን ለማየት ዓይን የሚገለጥበት ዕድሜ ነው ። ለማፍራት ማበር ያስፈልጋል ። ለመውለድ የወንድና የሴት ኅብረት ይፈለጋል ። እፅዋት እንኳ ወንዴና ሴቴ አላቸው ። የአዲሱ ዓለም ሥርዓት ሴትን ከወንድ ፣ ወንድን ከሴት የሚነጥል ሲሆን ውጤቱ ፍሬ የለውም ። ለማፍራት የሚቃረኑ አንድ መሆን አለባቸው ። በርግጥም የሚለያዩ አንድ ካልሆኑ አንድነት የሚለው ቃል ትርጉም የለውም ። ስንዴ ከስንዴ ጋር አንድ ሆነ አይባልም ። ከበቆሎ ጋር ግን አንድ ሆነ ይባላል ። አንድነት የተለያዩ ነገሮች ማበራቸው ነው ። ጌታችን በዚህ የሰው ልጅ ሙሉ ዕድሜ ፣ በማፍራት ምዕራፍ ፣ በመወሰኛ እርከን ተጠመቀ ።

ጌታችን በሠላሳ ዓመት ተጠመቀ የሚለው የዘወትር ቅዳሴአችን ነው ። “በሠላሳ ክረምት በዮርዳኖስ ተጠምቀ” እንላለን ። በዚህ ዕድሜ ላይ ያሉ የውሳኔ ዕድሜ መሆኑን ማሰብ አለባቸው ። በውሳኔ ራእያቸውን ካልለዩ ቁጭት ብቻ ይዘው ፣ ሌጣ ሁነው ዘመናቸውን ይፈጽማሉ ። የሚመስላቸውን ለማፍራት ይህ ዕድሜ ወሳኝ ነው ። ሠላሳ ከዘለቀ በኋላ ወዳጅ እያነሰ ይመጣል ። በሃያዎቹ የተጀመረው ሱስ አሁን በውሳኔ መቆም ይፈልጋል ። አሊያ የተዋረደ ዘመን ከፊት ለፊት ይጠብቃል ። ሱስ መጨረሻው እጅ እግር እያለ ለማኝ የሚያደርግ ፣ ከማኅበራዊ ክብር የሚያራቁት ነው ። ጥምቀትን ስናከብር ያልወሰንኩት ነገር ምንድነው ? ብሎ ማሰብ ይፈልጋል ። ከሠላሳ ዓመት በታች ወደ ትዳርም ወደ ምንኵስናም የሚሄዱ ብስለት ሊያንሳቸው ይችላል ።

ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሲመጣ ሕዝብ ዮሐንስን ያውቀዋል ፣ ኢየሱስን ግን አያውቀውም ። ዮሐንስ ትልቅ ቁጭት ነበረበት ። ለዚህ ነው ጮኾ ነዋ በግዑ ለእግዚአብሔር – እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ በማለት የተናገረው (ዮሐ. 1 ፡ 29) ። ሰው እነርሱን አውቋቸው ጌታቸው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ካላወቀው የቅዱሳን ኀዘንና ቁጭት ይህ ነው ። ለነቢያት ነቢያት የመባላቸው መሠረት ፣ ለሐዋርያት ሐዋርያት የመባላቸው ነቅዕ ፣ ለሰማዕታት ሰማዕታት የመባላቸው ጽድቅ ፣ ለደናግል ሙሽራይት የመባላቸው መርዐዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ጥምቀቱን ስናከብር የዮሐንስን ምስክርነት በማስታወስ ነው ። “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ። አንድ ሰው ከእኔ በኋላ ይመጣል፥ ከእኔም በፊት ነበርና ከእኔ ይልቅ የከበረ ሆኖአል ብዬ ስለ እርሱ ያልሁት ይህ ነው።” (ዮሐ. ፡ 29-30)። “ተጎንብሼ የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።” (ማር. 1 ፡ 7)። ሌሎች እንደሚዘልፉን አምላክንና ፍጡርን የማንለይ አይደለንም ። ያልተማሩ ፣ የቤተ ክርስቲያን መሠረትና ጉልላት ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን የማያውቁ ይኖራሉ ። እነርሱ ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መልክ መገለጫ አይደሉም ። በገጠር ብትሄዱ አሁን ኢትዮጵያን የሚመራው ማን መሆኑን የማያውቁ አሉ ። በእነዚህ ሰዎች መነሻነት ኢትዮጵያውያን መሪያቸውን አያውቁም ተብሎ ዜና አይሠራም ።

ስለ ኃጢአተኞች በመስቀል ላይ የሚሞተው አሁን በኃጢአተኞች ሰልፍ መካከል ተገኘ ። የዮሐንስ ጥምቀትም ፣ የክርስቶስ ደምም የሚያነጻው ንስሐ የሚገቡትን ነው ። ጌታችን ንስሐን ወዳጅ መሆኑን በዚህ ገለጠ ። የሰው ልጅ ባለመበደል አምላኩን ደስ ማሰኘት አይችልም፤ ምክንያቱም አቅሙ ደካማ ሆኖ ይወድቃልና ። ንስሐ በመግባት ግን አምላኩን ደስ ያሰኛል ። ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ ወይም የዮሐንስ አገልግሎት ዓለም አቀፍ ርእስ ስለነበር ቅዱስ ሉቃስ የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ በመተንተን ይጀምራል (ሉቃ. 3 ፡ 1-2) ። ዮሐንስ መጥምቅ ሄሮድስን ንስሐ ግባ ይለው ነበር ። ሄሮድስ የቄሣር ወኪል የአጥቢያው ንጉሥ ነው ። ሄሮድስ ሲነካ ዓለም አቀፉ መሪ ቄሣርም ይነካል ። ዛሬ ዓለም የሚንጫጫው የንስሐ ስብከት ሲሰበክ እንጂ ስለ መቻቻል ሲወራ አይደለም ። ይህ ነገር ኃጢአት ነው መባልን ዓለም አይፈልግም ። ወደፊት ፣ በቅርብ ቀንም ስብከት መከልከሉ አይቀርም ። ሰውን ይህን ማድረግ አይገባችሁም የሚሉ ትምህርቶች ከዘመናዊ ጣቢያዎች ላይ እንዲወርዱ ይደረጋል ። ይህን አታድርግ ማለት የሰውን መብት መጫን ነው በማለት አንዳንድ አገሮች ስብከትን የሚገድብ ሕግ እያረቀቁ ነው ። ንስሐን ብንሰብክ መሪው ተመሪው ያኮርፋል ። “በደለኛ ነህ” መባልን ይህ ዘመን አይፈልግም ። መጥምቁ ዮሐንስ አንገቱ የተቆረጠው ወንድምህን ገድለህ እንዴት ሚስቱን ታገባለህ ብሎ ዝምድናና ሰውነት መፍረሱን ስለ ወቀሰ ነው ። አዎ የጌታችን ጥምቀት ዓለም አቀፍ ርእስ ነበር ። ዛሬም ጥምቀቱን ዓለም አቀፍ በዓል ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ የንስሐ ጥሪ የምናሰማበት ሊሆን ይገባዋል ።

ጌታ ሆይ እርዳን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ