የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በርጠሜዎስ ነኝ

 ጌታዬ ሆይ ያለ ማየትን ዘመን በማየት ለውጬ ፥ የሚያዩኝን ለማየት በቅቼ ፥ ብርሃንን ከብርሃናት አምላክ ተመጽውቼ የምኖር በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። እኔ ነኝ ለማለት ድሮ የማልደፍር፥ ክፉውን ታሪኬን ወደ ኋላ የጣልኩኝ ፥ የማያዩ አይመሩኝም ፥ ዓይን የሌለው በትር ገደሉን እንጂ መድረሻውን አይጠቁመኝም ብዬ የጣልኩኝ ፥ ዓይን አውሱኝ እያልኩ ስጣራ የኖርኩኝ ፥ መቶዎችን ለምኜ አንዱን የማራራ እኔ ነኝ በርጠሜዎስ ከመቃብር በላይ የዋልኩኝ ። የድሮ ዕውር የዛሬ ተመልካች ፥ የድሮ ተመሪ የዛሬ መንገድ አመልካች ፥ የድሮ ተመጽዋች የዛሬ ሠራተኛ በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ሁለተኛ የተሠራሁኝ ። ጌታዬን አግኝቼ ከሰው መከጀልን ያቆምሁ ፥ የችግሬ ወራጁ ሳይሆን ምንጩ የተገደበልኝ እኔ ነኝ በርጠሜዎስ ድሪቶዬን ጥዬ ብርሃን የለበስኩኝ ። የሠራውን ዓለም ሳላይ ኖሬ ሠሪውን ባየሁ ቀን ሥራውንም ለማየት የበቃሁ እኔ ነኝ በርጠሜዎስ የማየት ወግ ያገኘሁኝ ። ዓይናማ አይደለሁም ፥ ነገር ግን የማይ ነኝ ። በዓይን ቅርጽ ሳይሆን በማየት የተባረኩኝ በርጠሜስ እኔ ነኝ ። ዓይኔም ልቤም የተፈወሰልኝ ። ዘመናት ያልሰጡኝን በአንድ ቅጽበት ያገኘሁ በርጠሜስ እኔ ነኝ ። የጊዜ ችሮታን ሳይሆን የጊዜን ባለቤት የማምን በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። መጀመሪያ ያመንሁ ቀጥሎ ያየሁ በርጠሜስ እኔ ነኝ ። የማመን ዋጋው ትልቅ ነውና እባክህ ሁልጊዜ እንዳምንህ እርዳኝ ። ዓይነ ሥውርነት በሽታ አይደለም ። የሚቀበሉት ጉዳይ ነው ። ጸሎትም አይደረግበትም ። እኔ ግን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኝ ጌታ በአጠገቤ ሲያልፍ እንደ ገና ሥራኝ ልለው ወደድኩ ። ልመናዬ ከእርሱ በላይ ትልቅ አይደለም ። ተካክሎም እኩያው አይደለም ። ልመናዬ በፊቱ እንደ ኢምንት ነው ። አምላኬን በአቅሜ አለካውም ።
ጌታዬ ሆይ ወደ ኢያሪኮ ያን ጊዜ እንዴት መጣህ ? እንዴት ላጋጣሚ ነው ፥ አጋጣሚን የማትወድ አምላክ ነህና ለምን መጣህ ? ልበልህ ። ኢያሪኮ ወደ እርስዋ የሚመጣባት ምንም ነገር የለም ። ብቻዋን ትልቅ ሆና ትልልቆች ሦስት ጊዜ አፍርሰው የሠሯት የሚታይ የሌላት ከተማ ናት ። ትልቅነት የአፍራሾች ዒላማ መሆን ነው ። ታሪክ ወዳዶች ቢመጡባት ልክ ናቸው ። አንተ ግን የታሪክ ባለቤት ነህ ። ያለፈውን ሺህ ዓመት እንደ ትላንት የምታስታውስ በዘላለም አሁን የምትኖር ነህ ። እኮ ታዲያ ለምን ወደ ኢያሪኮ መጣህ ? በደብረ ዘይት ሽቅብ ስታርግ ያየሁህ ፥ የኢያሪኮ አፈር መቼም አይናፍቅህም ። ወደ ዓለሙ ሰውን አድራሻ አድርገህ መጣህ ። በወደ ኢያሪኮ ግን እኔን አድራሻ አድርገህ መጣህ ። እኔን ፈውሰህ ደግሞ ዘኬዎስን ፍለጋ ተጓዝህ ። እኔም እርሱም አንድ ነን ። እኔ በድህነቴ ፥ እርሱ በሀብቱ የተጠላን ነን ። እኔም እርሱም እውነተኛ ፍቅር የማንቀበል ፥ ሰዎች በገደብ የሚቀርቡን ነን ። እኔም እርሱም ከቤት ወጥተናል ፥ እኔ ድንጋይ ላይ ተቀምጬ ፥ እርሱ ዛፍ ላይ ሆኖ ይጠብቅሃል ። የላይ ፈሪ የታች ፈሪ አቤት ፥ አቤት ይልሃል ። እኔም እርሱም ልናይህ ናፍቀናል ። አዎ ዓለም እጅግ ድሃውን ፥ እጅግ ባለጠጋውን ፤ እጅግ ክፉውን እጅግ ደጉን አትፈልግም ። ይህንን ቀራንዮ ላይ አይቼዋለሁ ። ነፍስ አጥፊ ሽፍቶችና አዳኝ ጌታ በአንድነት ተሰቀላችሁ ። ያልበላቸውን የሚገድሉ ሽፍቶችና ለበደሉት ይቅርታ የሚያደርግ ጌታ በአንድነት ዋላችሁ ። በዓለም ላይ እጅግ ክፉና እጅግ ደግ አይፈለጉም ። ሁለቱም በፍርድ ይወገዳሉ ። ዓለም የምትፈልገው ልምጦቹን ፥ ተጣጣፊዎቹን ነው ። ርኩሱም በሚረክስበት ፥ ቅዱሱም በሚቀደስበት ዘመን ከደግነትና ከክፋት የተቀመመ ማንነት ያላቸው ብቻ ይኖራሉ ። የአስመሳዮች ፥ የግብዞች ፥ የጭንብል አጥላቂዎች ዓለም ላንተ እንደማትሆንህ እኔው አውቀዋለሁ ። እኔን በሳንቲም ፥ ዘኬዎስን በጥርስ የሚሸኘን ዓለም እንደሆነ ተረድቻለሁ ። አንተ ግን ሰዎችን ታውቅ ነበርና ደግሞም ያለ አስረጂ ታውቃቸው ነበርና አልተደገፍካቸውም ።
እኔንና ዘኬዎስን አድራሻ አድርገህ እንኳን መጣህልን ። ዘኬዎስ ከዛፉ በኋላ ወደ ቤቱ ጋበዘህ ። እኔ ግን ቤቴ ጎዳናው ነውና ከድንጋዩ መቀመጫ ሌላ የት ልቀበልህ ? ቤት የለኝምና ። ገና የምቋቋም ፥ እንደ ገና የተወለድሁ ነኝና በልቤ ጋበዝሁህ ። ድህነት ጥሩነቱ ምግብን ሳይሆን ፍቅርን ፥ ቤትን ሳይሆን ራስን የሚጋብዝ ነው ። በእኛ በድሆቹ መልክ ስለመጣህ በእውነት ትልቅ ነህ ። ጌታዬ ሆይ የኢያሪኮ ድንጋይ ለዘመናት ያልሰለቸኝ ፥ የሄደው ሲመለስ የተመለሰው ሲሄድ የማይበት አደባባይ ነው ። ዓይኑ አያይም ብለው ንቁ ጆሮዬን ተጠራጥረውት ብዙ እየተናገሩ ያልፋሉ ። ዛሬ ግን አንተ እንደምታልፍ ሲያወሩ ሰማሁ ። ለእኔ ለመንገር ብለው ሳይሆን ለራሳቸው ለመድገም ሲናገሩ ሰማሁ ። ለድሃ ክርስቶስ ያስፈልገዋል ብሎ ማንም አያስብም ። እስከ ዛሬ ያልሰማሁትን ሰማሁ የመሢሑን መምጣት ሰማሁ ፥ ጎዳናው እኔ ብቻ ሳይሆን ሰዎች መራቆታቸውን ያወቅሁበት ነው ።
ለማኝ ፥ ሕጻንና እንስሳ ይታዘባል ብሎ ማንም አይጠነቀቃቸውም ። ስለዚህ ሁሉን የሚሰማ ጆሮዬ ዛሬ ያንተን ዜና ሰማ ። ለካ ስፈልግህ አልቀደምኩህም ። ፈልገኸኝ የመጣኸው በፍቅር ቀዳሚው አንተ ነህ ። እስከ ዛሬ ያልለመንኩትን ለመንኩ ። አምስት አሥር ሳንቲም እንጂ ብርሃንን ለምኜ አላውቅም ። ዛሬ ግን ማየትን ለመንኩ ። እስከ ዛሬ ያላየሁትን አየሁ ። አይቼ አላውቅም ነበር ፥ ዓይኔ ሲበራ ግን ያበራልኝን አየሁ ። ከዚያም የበራላቸውን አየሁ ። መጀመሪያ ያየኹት እርሱን ነውና ተከተልኩት ። ይህች ቀን ለእኔ ልዩ ናት ። ትልቅ ዜና ለትልቅ እምነት ፥ ትልቅ እምነት ለትልቅ ጩኸት ፥ ትልቅ ጩኸት ለትልቅ ተቃውሞ ፥ ትልቅ ተቃውሞ ለትልቅ ፈውስ ፥ ትልቅ ፈውስ ለትልቅ መከተል ያስተላለፈኝ ቀን ነው ። ጌታዬን ያገኘሁባት ቀን ዕለተ ወርቅ ናት ።
ጌታዬ ሆይ አሥር ሳንቲም ሰጥተው የአሥር ሺህ ብር ንግግር የሚናገሩ ሰዎችን ማምለጥ እንዴት ይቻለኛል ? እነርሱ ይሄዳሉ ንግግራቸው ውስጤ ይቀራል ። ቃላቸው ሲያዋራኝ ይኖራል ። ደግሞ ልረሳው ስል አንዱ ያድስልኛል ። ሰንሰለታማውን የሰው አንደበት ፥ ቆሰልኩ እንጂ አቆሰልኩ የማይለውን ባሕርየ ሰብእ ዛሬ ተገላገልኩ ።
የሰው ፊት ፥ የሰው ፊት እሳቱ
ፍምም አልወረደው እንደ መፋጀቱ
ጌታዬ ሆይ ሰውን ከምከጅልበት ፥ ከራሱ ጋር ታግሎ ለራሱ ኅሊና ዕረፍት ሲል ሳንቲም ከሚጥልበት ወንበሬ አስነሣኸኝ ። ልመናን ሥራ ብዬው ከሠራተኛ በፊት ብገኝም ኑሮዬ እልፍ አላለም ። ኑሮዬ እልፍ ብሎ ከልመና ብላቀቅ እንኳ የሰጡኝ ሁሉ መስጠታቸውን ሊያስታውሱኝ ይጥራሉ ። በእኛ ነው ለዚህ የበቃኸው ይላሉ ። ባልኮራ እንኳ የኮራሁ ይመስላቸዋል ። ደግነቱ የእነርሱ እርዳታ ሳያስነሣኝ ያንተ የብርሃን ስጦታ አስነሣኝ ። ድህነቴን ነግረህ አልሰጠኸኝም ። እምነቴን ነግረህ ሰጠኸኝ ። ካንተ በቀር ብርሃንን ቀልሎት የሚቸር ከቶ ማንም የለም ። ጌታዬ ሆይ የሰው ምጽዋት ከልመና ወንበር አያስነሣም ። ሰው የችግሩን ወራጅ እንጂ ምንጩን አይገድብምና ። አንተ ግን የችግሬን ምንጭ አለማየቴን አስወገድክልኝ ። አለማየት ወዳጅና ጠላትን አይለይም ። አለማየት በችርቻሮ ሳንቲም ሲደለል ይኖራል ። አለማየት ሁልጊዜ ተስፈኛ ነው ፥ ባለው አይደሰትም ። አለማየት ጠላት እንጂ ወዳጅ አለኝ አይልም ። አለማየት ካልለመዱት መልአክ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል ይላል ፥ ለለመደው ነገር ታማኝ ለመሆን እውነትን ይገፋል ። አለማየት የሌሎችን ንቀት ይቀበላል ፥ ተቀባይ እንጂ ሰጪ አይደለምና ።
ጌታዬ ወዳጄ ሆይ ልቤ ያየህን ዓይኔም ደገመህ ። እኔንና የሠራሁትን ሳያይ አይሙት ብለህ ፈረድክልኝ ። በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። ተቀምጬ ስጓዝ የነበርኩኝ ፥ ዛሬ በእግሬ ገሰገስኩኝ ። በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ፥ ለመሪ የምከፍል ፥ ወደ ማልወደው ልመና ለሚያደርስ ቀረጥ የምቀርጥ ፥ ድንጋይ ለሚያስመታ ለልበ ዕውር የምከፍል ፥ ዛሬ ግን በነጻ ብርሃንን የለበስኩ በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። የምስጋናው አደባባይ አይጠብም ። እንደ እኔ የተቀበላችሁ አመስግኑ ። የምትበሉት እንዲጣፍጣችሁ ፥ የራቃችሁ እንዲቀርባችሁ አመስግኑ ። ድል አለ በምስጋና እኔ ልንገራችሁ ።
                                                  ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ