የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በርጠሜዎስ ነኝ /2/

ጌታዬ ሆይ ያንተ ብርሃን እስኪያስነሣኝ ድረስ ብዙ ዓይነት ሰጪዎችን አይቻለሁ ። ብዙ ዓይነት ስጦታዎችንና ብዙ ዓይነት ተቀባዮችን አውቃለሁ ። መስጠት ሱስ ስለሆነባቸው የሚሰጡ ሰዎችን አውቃለሁ ። የመስጠት ሱስ ስላለባቸው ያደርጉታል ፥ ሱስ ግን ልማድ እንጂ ፍቅር አይደለም ። እነዚህ ሰዎች የባለጠጋ ድሆችን ሲረዱ ይውላሉ ። ገንዘባቸውንም ያለውለታ ይጨርሳሉ ።  ደግሞም ለርኅራኄአቸው ዋጋ የሚከፍሉ ሰጪዎች አሉ ። ዝም ብለው ቢሄዱ ያዩት ጉዳትና ድህነት ቀኑን በሙሉ ሲረብሻቸው ይውላል ። ቀኑ ከሚበላሽባቸው ሳንቲም በመወርወር ያርፋሉ ። ምስኪኑን ሰው ስለወደዱ ሳይሆን ኅሊናቸውን ለማሳረፍ ይጥላሉ ። የተጨነቀው ኅሊናቸውም በሳንቲም ስጦታ ያርፋል ። እነዚህ ሰዎች ለራሳቸው ሰላም የሚመጸውቱ ናቸው ።
የወርቅ ስጦታየሚሰጡ አሉ ። እነርሱ ከፍቅር ጋር እንጀራን የሚቆርሱ ናቸው ። የመዳብ ስጦታ የሚሰጡ አሉ ። መስጠት እየቻሉ አይዞህ እያሉ የሚያጽናኑ ፥ እጸልያለሁ እያሉ የሚዘብቱ ናቸው ። የናስ ስጦታ የሚሰጡ አሉ ። ለታይታ የሚቸሩ ናቸው ። የብረት ስጦታ የሚሰጡ አሉ ። እነዚህ የሰጡትን የሚያወሩ ናቸው ። ስጦታቸውም እንደ ብረት ይከብዳል ። የእርሳስ /የጥይት/ ስጦታ የሚሰጡ አሉ ። እነዚህ አደንዛዥ ዕፅና መጠጥ የሚጋብዙ ናቸው ። ጌታዬ ሆይ ስንት ዓይነት ሰጪዎችን ስንት ዓይነት ስጦታዎችን አይቻለሁ ።
ብዙ ዓይነት ተቀባዮችም አሉ ። የራሳቸውን የግላቸው ፥ የሌላውን የጋራቸው እንደሆነ የሚያስቡ አሉ ። ደግሞም በሌላው እጅ ያለው ሁሉ የሚያምራቸው ፥ በይገባኛል የሚከጅሉ አያሌ ናቸው ። ያገኘ ሰው ሁሉ የሰረቀ ወይም ያስጠነቆለ የሚመስላቸው እግዚአብሔር እንደሚሰጥ የማያውቁ ብዙ ተቀባዮች አሉ ። ሌላው የሰጣቸው ስለፈራቸው የሚመስላቸውና ጨምር ለማለት ዓይናቸውን የሚያፈጡ አሉ ። ለመመረቅ የሚተናነቃቸው ሌሎች የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የሚያስቡም አሉ ። ስጦታው የሚያሳቅቃቸው በተቀበሉ ቊጥር ወይ ዕድሌ እያሉ የሚያማርሩም አሉ ። እነዚህ ሁሉ ክፉ ተቀባዮች ናቸው ። መስጠት ተራ መሆኑን አይገነዘቡም ። የዛሬ ተቀባይ የነገ ሰጪ ፥ የዛሬ ሰጪም የነገ ተቀባይ መሆኑን አይረዱም ። ስለዚህ ለማመስገን ፍቅር ፥ ለመሻገር ትዕግሥት የላቸውም ።
 ጌታዬ ሆይ የድንጋዩ መቀመጫዬ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ቤቴ ነው ። በዚያ መንገድ ብዙዎች በእግር ፥ ብዙዎች በሠረገላ አለፉ ። እነዚህ ሁሉ ችግሬን አተሙት እንጂ አላሳለፉትም ። አንተ ስታልፍ ግን ታሪኬ አለፈ ። የኢያሪኮ መንገድ ከነቢዩ ኤልሳዕ በኋላ ጭርታ እንደ ገጠመው ይሰማኛል ። ዛሬ ግን ደምቋል ። አጠገቤ የሚያልፉት ሰዎች ትላንት በድምፃቸው የማውቃቸው አይደሉም ። “እናንተ ሰዎች እባካችሁ ዛሬ ምን አለ ?” ስላቸው መቶዎች ድምፄን ለመስማትና መልስ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም ። የሚሰሙት የሚያስቡትን ነውና ገንዘብ የጠየቅኋቸው መስሏቸዋል ። ጌታዬ ሆይ ለድሃ የሚያስፈለገው ገንዘብ ብቻ ይመስላቸዋል ። አንተ ግን ከገንዘብ ሌላ የሰጠኸኝ ልዩ ወዳጄ ነህ ። ድሃ የሚመጣው ሁልጊዜ ገንዘብ ፍለጋ አይደለም ። የሚያወራኝ ናፍቆኝ ወደ አንዱ ቤት ስሄድ ሁሉም ሰው ኪሱን ይዳብሳል ። ሰጥቶ ያባርረኛል ። ቆርጠው ከወጡ ገንዘብ አይጠፋም ። ቆርጠው ቢወጡ ግን ፍቅር አይገኝም ። ፍቅር ዘር ነውና ስንዘራው ብቻ ይበቅላል ። ድሃ በዓለም ላይ ትልቁን ስጦታ ይሰጣል ። ራሱን ይሰጣል ። ግን ማንም አይቆጥርለትም ። ለሰዎች ትልቅ ነገራቸው ገንዘብ ነው ። አንተ በእኔ መንገድ የምታልፍ መሆንህን ያወቅሁት ኢየሱስ የሚለውን ስምህን ላይድኑበት ደጋግመው ሲጠሩት ነው ። ጆሮዬን ማመን ስላቃተው እንደ ገና “እናንተ በዚህ የሚያልፈው ማን ነው?” ስል አሥሩ አልፈውኝ አንዱ ፡- “የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው” አለኝ ። ሰው በተወለደበት እንጂ ባደገበት ለምን ይጠራል ? የቤተ ልሔሙ ኢየሱስ ለምን አላሉህም? እያልኩ አስባለሁ ። ለካ ናዝሬት የወንበዴዎች ከተማ ነበረች ። የኃጢአተኛ ወዳጅ መባልን ስለምትፈልግ ነው ። የምናደክምህ ጤና ያጣን ዕውሮች ፥ ገንዘብ ያጣን ድሆች ፥ ጽድቅ ያጣን ኃጢአተኞች ነን ። አንተ ግን እንደ ባለ ጉዳይ እንኳ አላየኸንም ። እንደ ልጅ ተቀበልከን ። እኔ አድናቂህ ሳይሆን ባለ ችግረኛህ መሆኔ ተሰማኝ ። እግዚአብሔርን ቀርቦ ሳለ ጥሩት ፥ በሚገኝበትም ጊዜ ፈልጉት የተባለውን አሰብኩ ። ዛሬ ለእኔ ቊርጥ ቀኔ ነው ።
መቼም ጌታዬ ረጅም ዘመን በብቸኝነት ስለኖርኩ ከሰው ጋር መጫወት አላውቅምና ሁሉንም ላውራህ ። እንዴት እኔ መሆኔን አወቅህ ? መሢሕ መሆኔን እንዴት ተረዳህ ? ብለህ ጠይቀኝ ። አዎ ጠይቀኝ ጌታዬ ። ልመልስልህ ፡- የሰዎች ውድቀት ፥ የመከራ ጽናት ፥ የበሽታ ቊጥር ፥ ልክ የለሽ ሀብትና ልክ የለሽ ድህነት ሲንሰራፋ መምጫህ እንደ ቀረበ አውቄ ነበር።
ሰውንም ስለምን አላፈርኩም ? መስጠት ከማይችለው ከሰው ስቀበልም አልተሰቀቅሁም ። ስለዚህ በልዑል ቃል ፡- “የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ” ማለት ጀመርኩ ። ሊለመኑ የማይገባቸውን ሰዎች ስለምን ማንም አላስቆመኝም ። የሚለመነውን ሰጪ ጌታ ስለምን ግን ሁሉም ዝም በል አለኝ ። እኔ ችግሬ ከብዶኝ እጮኻለሁ ፥ እነርሱን ግን ጸሎቴ ከበዳቸው ። ባለጠጋ ቢጮህ አብረው ይጮኹለት ነበር ። እንደ እርሱም አይደለም። ዘኬዎስ እኮ ባለጠጋ ነበር ። እንዴት እቤቱ ገባህ ብለው ከስሰውሃል ። ሰው የሚወደው የመካከሉን ነው ።
ማርቆስ ድሮ ዮሐንስ ነበረ ስሙ ። የጴጥሮስ ደቀ መዝሙርም ነበር ። ታዲያ ወንጌሉን ለሮማውያን እየጻፈ መሆኑን ነገረኝ ። አሁን አሥረኛው ምዕራፍ ላይ ደርሻለሁና ከአርባ ስድስት ቊጥር ጀምሮ ልጽፍልህ እፈልጋለሁ አለኝ ። ተው ማርቆስ የሚጻፍ ታሪክ የለኝም ፤ ኑሮዬ የድህነት ፥ ዘመኔ የእውርነት ነው አልኩት ። ማርቆስ ትሑት ነውና ታሪክህ የታደሰ ልዩ ፍጥረት ነህ ። ስለዚህ በእግዚአብሔር መዝገብ ያደረከው ቢጠፋ የተደረገልህ ሲነገር ይኖራል አለኝ ። ያደረግኹት ባይኖርም ያደረገልኝ ግን ብዙ ነው ፥ እሺ ጻፈው አልኩት ። ወይ ጌታዬ ማዶ ገዳመ ቆሮንቶስ ይናገራል ፥ በስተቀኜ ማዶውን የኤልሳዕ ምንጭ ያወራል ። የእኔ ድንጋይም ለዘመናት ልትናገር ነው ? አልኩኝ ።
ጌታዬ ያንተን ላንተው ልናገር ። ያንተን ላንተ መስጠት መልካም ነው። “የዳዊት ልጅ ሆይ ማረኝ”  ብዬ ስጮህ ሰዎች ሁሉ ገሰጹኝ ። የሚገሰጽ ያጠፋ ነው ። የጸለየ እንዴት ይገሰጻል ? አልኩኝ ። ገና ስምህን ስጠራ ውጊያ ጀመረኝ ። አንተ ጌታዬ ውስጥህ ሰላም ፥ ዳርህ እሳት ነው ። ለነገሩ ውስጥ ሰላም ሲሆን ዳሩ እሳት ይሆናል ። ውስጡ እሳት ሲሆን ደግሞ ዳሩ ሰላም ይሆናል ። ለእኔ ግን አንተ ትሻለኛለህ ። ተወዳጅ ለማኝ ከመሆን የተጠላሁ ሠራተኛ መሆንን እፈልጋለሁ ። ተወዳጅ ዓይነ ሥውር ከመሆን የተጠላሁ ተመልካች መሆንን መርጫለሁ ። ቃልህ ፡- “ወዶኛልና አዳነኝ” ይላል ። የሚያድን ፍቅር ያንተ ብቻ ነው ። ሰው ቢወድ ፍቅሩ ከሞት አያድንም ። እኔም ቀኔ ዛሬ ነውና በተወደደ ቀን ጠራሁህ ፥ በመዳን ቀንም ረዳኸኝ ። ዝም በል ሲሉኝ እንደውም ባሰብኝ ። ውስጡ የሚጮህበት ቢጮህ አይጠግብም ። ሁሉም ምሕረትህን ለግል መጽናናት ብቻ ይፈልገዋል ። ምሕረትህ ለሰው ሁሉ መሆኑን ግን አይረዳም ። ለካ እንዳልድን የሚጠብቁኝ ፖሊሶች ፥ የእውርነቴ አድናቂዎች አሉ ። ለነገሩ ዓለም የምትወደኝ የእርሷን ካልነካሁ ነው ። በወንበር ካልተጋፋሁ ትወደኛለች ። ካልበላሁ የበቃ የነቃ ነው መናኝ ነው ትለኛለች ። ምሥጢሩ መብላት በልክ ክፉ ሆኖ አይደለም ፥ስላልነካሁባት ነው ። ዮሐንስ መጥምቅን ያከበረችው ምንም አይነካብኝም ብላ ስለተማመነች ነው ። ውሾች ድሃ ላይ የሚጮኹት ምግቤን የሚወስድ መጣ ብለው ነው ። የለበሰውንማ ውሾችም ያከብራሉ ።
እንዲያ ስጮህ አንተ ግን ቆምክልኝ ። በኢያሪኮ ከእኔና ከዘኬዎስ ሌላ የተጠቀመብህ የለምና ለካ የመጣኸው ለእኛ ነው ። እኛ በጸሎታችን የቆምክልን መሰለን ። አንተ ግን የቆምከው እኛ ጋ ስለመጣህ ነው ። አጃቢዎችህ ያላገኙትን የተጠላነው እኛ አገኘን ። ጌታዬ ሆይ ዘኬዎስን አግኝቼው አላውቅም ። ደህና ነው ? በምድርም በሰማይም ቢሆን አንተን ያገኝሃልና አንተን መጠየቄ ትክክል ነው ። አምጡት ስትል ጀማው ፀጥ አለ። ቅድም የገሰጹኝ አሁን አነሡኝ ። አንተ ድምፅህን ስታሰማ የገፋን ያቅፈናል።  እባክህ ድምፅህን አሰማ ። ዛሬም ብዙ ታሪክ ይለወጣል ። ሊለያዩ የተቃረቡ ባልና ሚስት ፍችው ሊቀደድ ሲል ኧረ አብረን እንኑር ይላሉ ። የድምፅህ መሰማት የሞት ሽታን ይለውጣል ። ኦ ጌታዬ ስንጸልይ አንተ ድምፅህን ታሰማለህ ። ለካ የችግራችን ምንጩ አለመጸለይ ነው ። ጌታዬ ሆይ ባንተ ታድሼ ፥ በድምፅህ በርትቼ እንጂ ዕድሜዬ እኮ ገፍቷል ። ያን ቀን ግን በደስታ ስዘል ድሪቶዬ ወለቀ ። ወደ አንተ እንደሚያይ ሰው በሩጫ ስመጣ ለካ የብርሃን ልብስ ይዘህ ትጠብቀኝ ነበር ። ነቢዩ ፡- ብርሃንን እንደ ልብስ የለበስህ ይልሃል ። አዳምና ሔዋንን ይህን የብርሃን ልብስ አልብሰሃቸው ነበር። እኔም ዛሬ ተራው ደረሰኝ ። ጨርሰህ ፥ ሁሉን አዘጋጅተህ ጠብቀኸኛል ። ንጉሥ ነህና አቤቱታዬንና ጥያቄዬን መስማት ይገባሃል ። “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ ?” ስትለኝ ለካ የምንኖረው አድርጉ ያለንን ትእዛዝ ለመፈጸም ብቻ አይደለም ። የምንሻውንም ለማግኘት ነው አልኩኝ ። “መምህር ሆይ አይ ዘንድ” አልኩህ ። ቅድም የዳዊት ልጅ ያልኩህ ዘመዴ ስለሆንህ ነው ። ማረኝ ያልኩህ ምሕረት ገንዘብህ ስለሆነ ነው ። አሁን መምህር ሆይ ያልኩህ መምህር ከጨለማ የሚያወጣ ስለሆነ ነው ። ልቤንም ዓይኔንም ፈውስልኝ ለማለት ነው መምህር ሆይ አይ ዘንድ ያልኩህ ።
አንተም እምነትህ አድኖሃል አልከኝ ። ያዳነኝ ቸርነትህ ቢሆንም ለእምነቴ ዋጋ ሰጠህ ። አዎ ጥቂት እምነት በፊትህ ትልቅ ተራራ ያነሣል ። ያን ጊዜ ተከተልኩህ ። ቤት የለኝ ተመልሼ ልዝጋው አልልም ። ይህን ያህል ዘመን ሲሰጡኝ የነበሩትን ደጎችን ፥ ያዝኑልኝ የነበሩት እውነተኛ እስራኤላውያንን ዛሬ መልካቸውን አየሁ ። የሚያበላኝን አለማየት ፥ የሚወደኝን አለመመልከት ከብዶኝ እኖር ነበር ። ዛሬ ግን ከሰቀቀኔ አወጣኸኝ ። አዎ በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። እኔ ነኝ ያልኩት እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ያለውን ጌታ አግኝቼ ነው ። በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ፡-
ከድንጋይ ትራስ ዳቦ የተንተራስኩኝ ፥ ከመንገድ ጠባቂነት ጌታዬን የተከተልኩኝ ፥ ድምፄ ተለምዶ ጆሮ ያታከትኩኝ ፥ ሕጻን የማይቆምልኝ ዛሬ ግን ንጉሥ የቆመልኝ በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ፤ በማታ የተሠረግሁኝ ፥ የሠርክ ሙሽራ የሆንኩኝ ። በቀድሞ አድራሻዬ የምትፈልጉኝ እንኳን አድራሻዬ ድሪቶዬም ተለውጦ ብርሃን ለብሻለሁ ። አለማየትን ዕውርነትን በነበር እተርካለሁ ። በርጠሜዎስ እኔ ነኝ ። ጌታዬ እንደገና የፈጠረኝ ። ምስጋና ያለባችሁ እንደ እኔ ያለይሉኝታ ጩኹ ፥ አመስግኑ ። ጌታዬ ሆይ ሰማይ ስሚ ምድር አድምጪ ብዬ ብናገርም ምስጋናህን ገና አልጠገብኩም ። ስምህ ቡሩክ ቅዱስ ይሁን ለዘላለሙ አሜን !!!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ