በአውቶቡስ ውስጥ ሲጓዙ ወጣቱ ቁጭ ብሎ ሽማግሌው እየተብረከረኩ ቁመዋል ። ከአሁን ካሁን ይነሣልኛል እያሉ ሲጠባበቁ ወጣቱ ግን በኩራት እያያቸው አንድ ጥያቄ ሊጠይቃቸው ይዳዳል ። በወጣት አነጋጋር፡- “ሽሜ እናንተ እያላችሁ ወጣቱ የሚሞተው ለምንድነው ?” አላቸው ። እርሳቸውም፡- “መልአከ ሞት እኛን ፍለጋ ሲመጣ በእኛ ወንበር ላይ ተቀምጣችሁ የሚያገኛችሁ እናንተን ስለሆነ ነው” አሉት ይባላል ።
እኒህ አባት ሁለት ነገሮችን እያስተላለፉ ነው ። ድካማቸውን አይቶ ስላልተነሣላቸው ኀዘናቸውን እየገለጡ ነው ። ዳግመኛም ድፍረቱን አይተው ዘመኑ አጭር መሆኑን እየተናገሩ ነው ። ከሰውም ከእንስሳም የመጀመሪያ ቀን እንግድነት ትቶ አስተናጋጅ የሚሆን ፣ ጭርታውን ሽሮ ግርግር የሚያበዛ ፣ የፈሩትን አስከትቶ የሚዘምት ፣ ባለቤቶቹን የሚያስተናግድ ፣ የራቁትን ቶሎ ብሎ የሚያቀርብ … የሚቆይ አይደለም ። የዓመቱን በዕለት ስለሚጨርሰው ወደ ሌላ ቦታ ይጓዛል ። ጎርፍ በደቂቃ መጥቶ አፈሩን ሁሉ ይዞ ይሄዳል ፣ ነጠብጣብ ግን ቀስ እያለ መሬቱን ያርሰዋል ። አጣቢ ጎርፎች በቶሎ መጥተው በቶሎ ይሄዳሉ ። ማደሪያ የላቸውም ነገር ግን ግንድ ይዘው ይዞራሉ። የሚያረሰርሱ ግን ቀስ ብለው የሚናገሩ ፣ ቀስ ብለው ሥራቸውን የሚሠሩ ናቸው ። አዎ የብዙ ወጣቶች ነገርም ልክ እንደዚሁ ነው ። ሁሉንም ነገር በአንዴ መጨበጥ ፣ ሁሉንም ነገር በአንዴ ማጣት የወጣቶች መገለጫ ሁኗል። ለሁሉም ነገር ፈጣን የሆኑት ፣ በአውቃለሁ ስሜት የተሞሉት ፣ ብልህ እንደሆኑ የሚናገሩት ወጣቶች ለሞት ግን ሞኞች ናቸው ። አርባ ዓመት፣ አቀበት የማይወጣ ዳገት የሆነበት ወጣት በጣም ያሳዝናል ። አዎ ታናናሾቻችንን ስናይ ሰርክ በጅምር መሆናቸው ያሳዝነናል ።
አንድ ትልቅ አባት ናቸው ። በጊዜአቸው በቤተ ክህነት ትልልቅ የኃላፊነት ሥራ ላይ ሠርተዋል ። ኋላ ላይ ፍጹም ድሃ ሁነው በየመንገዱ ይዞራሉ ፣ ይናገራሉ ፣ ይለምናሉ ። ታዲያ ከዓመታት በፊት ነው ፣ ከአንድ ዲያቆን ጋር በመንገድ ስንሄድ ፊት ለፊታችን ሲመጡ ዲያቆኑ ዘወር አለና ሸሸ ። እኔም ፊት ለፊት ተገናኝተን ሰላም ስላቸው ፣ እኔን ትተው ዲያቆኑን መፈለግ ጀመሩ ። “አንተ ፣ አንተ አልፈኸኝ ልትሄድ ነው ?” አሉት ። እርሱ ግን “አላየሁም” ብሎ ዋሸ ። እርሳቸውም፡- “ምነው ልጄ እንደሚሰነብት ብትሆን ?” አሉት ። አዎ እንደሚሰነብት ብንሆን መልካም ነው ።
ብዙ ወጣቶች በሽማግሌዎች ቦታ ተቀምጠዋል ። ይልቁንም ሁልጊዜ በማያልቁ ጅምሮች ውስጥ በሆነችው አገራችን ቦታ መለዋወጥ የተለመደ ሁኗል ። ወጣቶች ሽምግልናን እንደናቁት ፣ ሽማግሌዎችም ሽምግልናን አልተቀበሉትም ። ክብሩ ነውር ፣ ነውሩም ክብር እየሆነ ነው ። ብቻ ሽማግሌዎች ቁመዋል ፣ ወጣቶችም ተቀምጠዋል ። ሁሉም እንደ ጊዜው መሆኑን ያልተረዱ ሽማግሌዎች እነርሱ ካረጁ ዓለም የጀመረች እየመሰላቸው ከክብር ዝቅ ብለዋል ። አዎ የሽማግሌው ልብ እየጎረመሰ ፣ የወጣቱ ልብ እየተነፈሰ ከመጣ ከባድ ነው ። እግዚአብሔር የሰጠው የክብር ዘውድ ፣ ብዙ ዘመን የመራመድ ምልክት የሆነው ፣ ነጩ ወርቅ ያ ሽበት እየተጠላ ነው ። ስለዚህ የሚመክርና የሚመከር እየጠፋ ሁሉም ልጅ እየሆነ ነው ። በድልድይ ከመገናኘት በዝላይ ለመገናኘት እየተፈለገ ስብራት እየበዛ ነው ።
ብዙ ወጣቶች የተቀመጡት በሽማግሌዎች ቦታ ላይ ነው ። ሽማግሌዎችም ልጆቻቸው ተምረው ሲመጡ ወንበሩን ለእነርሱ ያስረክባሉ ። ልጆቹ የተማሩት የሕይወት እውቀት ሳይሆን የእንጀራ እውቀት ነው ። በብዙ ትዳሮች ልጆች ወንበሩንና መሪውን ጨብጠዋል ። የቤት ቀለብ የሰፈረ ልጅ ወላጆቹን መምራት ይፈልጋል ። ፈረንጆቹስ ስንዴ ሰጥተው አይደል ሊገዙን የሚፈልጉት ? በትልልቅ ግዛቶች ውስጥ ትንንሽ ግዛቶች አሉ ። በደግነት የኖሩት ወላጆች ልጆቻቸው ሰልጥነው ከመጡ በኋላ ምግብ መቆለፍ ተምረዋል። ይህን ሁሉ ዘመን በእምነት ኑረው አሁን በመጨረሻ ሰዓት በስሌት ሲኖሩ ያሳዝናሉ ። ልጆች ያሉት እንጂ ትዳር ያለው የማይሰማበት ዘመን ይመስላል ። ብዙ እናቶች የትዳር አጋራቸውን ጥለው ልጆቻቸው ጋ ናቸው ። በየፈረንጅ አገር ባል አልቦ የሆኑ ብዙዎች ናቸው ። በስተርጅና ሙሽርና ማለት ይህ ነው ። አገሩ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ለምን ጀማሪ ሆነ? ለኖርንባቸው ዓመታት ፣ ለኖርንባቸው መንደሮች ፣ አብረናቸው ለኖርናቸው ወገኖች ክብር መስጠት አለብን ።
በሽማግሌዎች ወንበር ወጣቶች ተቀምጠዋል ። ደርግ እንደ መጣ ከአርባ ዓመት በላይ የሆነው ማዳበሪያ ይሁን የሚል ንግግር በወጣቶች በዝቶ እንደ ነበር የሰሙት ሲናገሩ ቆይተዋል ። ወጣቶችም ያው የተናገሩትን ማለፍ አቅቷቸው ሁሉም ማዳበሪያ /አፈር/ ሆኑ ። ለካ ንግግር በራስ ላይ መሰናክል ማስቀመጥ ነው ። እግዚአብሔር የተናገርነውን ፍርድ በእኛ ላይ ማጽደቁ የተለመደ አሠራሩ ነው ። ወጣቶች አገርን ሲቆጣጠሩ አገር መርጋት ያቅተዋል ። ወጣቱ ሮብዓም ያለ አማካሪ በመንገሡና ቢጤዎቹን በመሰብሰቡ አንዲቱ እስራኤል ለሁለት ተከፍላለች ። መለያየትም የሚያመጣውን ጥፋት ቀምሳለች ። ወጣቱ መሪ ሮብዓም መጀመሪያ የጠላው ሽማግሌዎችንና ምክራቸውን ነው ። ቀጥሎ ከራሱና ከቢጤዎቹ ጋር መከረ ። ከመሰሎች ጋር መመካከር የምናውቀውን መልሶ መስማት ነው ። የሽማግሌዎች ምክር እውነት ተኮር ነው ፤ የወጣቶች ምክር ራስ ተኮር ነው ። የሽማግሌዎች ምክር ተሸንፎ ማሸነፍ ነው ፣ የወጣቶች ምክር አሸንፎ መሸነፍ ነው ። አንድ ከፍተኛ የደርግ ባለሥልጣን የነበሩ ሰው በእስር ቤት ውስጥ አግኝቻቸው እንዲህ ብለው አጫውቱኝ ፡- “እኔ ወደ ሥልጣን ስመጣ ገና ሃያ ስምንት ዓመቴ ነበር ፣ በአደባባይ የወደቀው ሰው ብቻ ሳይሆን አእምሮም ነው ። የንጉሡን ባለሥልጣኖች በሰላም ወደ ቤታቸው ብንሸኛቸው የገዛ በሽታቸው ይገድላቸው ነበር ። እነርሱን መግደላችን ይጸጽተኛል ። ይህን ሁሉ ያደረገው ግን ወጣትነታችን ነው ።” ብለውኛል ። እነዚህ ወገኖች ዛሬ መርተው ቢሆን ኑሮ ይህን ስህተት አይፈጽሙትም ነበር ። ሽምግልና ጥፋትን ባያስቀር እንኳ ይቀንሳል ።
በዳኝነት ወንበር ላይ የተቀመጡት ወጣቶች ናቸው ። ዳኝነት ፈሪሃ እግዚአብሔርና ልምድ በጣም ይጠይቃል ። ተፈጥሮአዊ ጸጋም ያስፈልገዋል። የሕግ ዓላማ መበቀል ሳይሆን ማስተማር ነው ። በአንዳንድ የሰለጠነ አገር ሕግ የሚያጠኑ ተማሪዎች ሊመረቁ ወራት ሲቀራቸው በአንድ ሰበብ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ ይደረጋል ። እስር ቤቱን ለወራት ታስረው ያዩታል ። ዓላማው በፍርድ ወንበር የተቀመጡ ቀን እስረኛውን ወዴት እንደሚልኩት እንዲያውቁና ትክክለኛ ብይን ከሰብአዊነት ጋር እንዲሰጡ ነው ። ይህን ያላየ በፍርድ ወንበር ላይ የተቀመጠ ወጣት ግን ወደ መዝናኛ ቦታ የሚልክ ይመስለዋል ። የአንድ አገር ሉዓላዊነትና ጽናት የሚረጋገጠው በፍርድ ነው ። ፍርድ የማይሸጥበት አገር ብቻ ይለመልማል ። በፍርድም ዙፋን ይጸናል ። ሽማግሌዎችና ብስለት ያላቸው ሊቀመጡበት የሚገባ ስፍራ በወጣቶች ከተያዘ አደገኛ ሊሆን ይችላል ። ራሳቸውንም አገርንም ይዘው ገደል ሊገቡ ይችላሉ ። በተማሩበት ዓመት መጠን ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ የተሻለ ነው ። አንድ ታክሲ ውስጥ የተሳፈርኩት ከሾፌሩ አጠገብ ነው ። ሃምሳ ዓመት መኪና እንዳሽከረከሩና ቅጣት እንኳ ተቀጥተው እንደማያውቁ ነገሩኝ ። ስለ አሁን አሽከርካሪዎች ሲናገሩ ግን፡- “መኪናው ልጅ ፣ ሾፌሩ ልጅ ሁሉም አለቁ” በማለት ተናገሩ ።
በሕክምና ስፍራ ወጣቶች በዝተዋል ። መርፌ የሚወጉን ከፌስ ቡክ በግድ ነጥለናቸው ነው ። አእምሮአቸው ያለው ወሬው ላይ ነው ። ባልተሰበሰበ አእምሮ መድኃኒት እየሰጡ ስንቱ አለቀ ? ግን የሚያልቀው ድሃ ነውና ማነው ያዘነ ? ድሃው ለቤቱ ሀብታም ነው ። መስጠቱ ሳይሆን መውጣት መግባቱ ለቤቱ አስፈላጊ ነው ። ኃላፊነት የሚሰማቸው ፣ የዕድሜ ረሀብ የሌለባቸው ፣ ልባቸው የሸመገለ ሊታጩ ይገባል ። ዛሬ ያጨድናቸው ሽማግሌዎች ነገ በስእለት አይገኙም ።
በሃይማኖት ስፍራዎች ብዙ ሰባኪዎችና አገልጋዮች ልጆች ናቸው ። ባልረጋ እውቀት አብደው ስንቱን ሕዝብ ያሳብዱታል ። ባነበቡት ጽሑፍ በቀን ሦስት ጊዜ የሚያብዱ ፣ ሁልጊዜ መሠረት የሚመሠርቱ ፣ አንድ ጉልላት የሌላቸው እየበዙ ነው ። የኖረ ኑፋቄ ሲሰሙ አዲስ መገለጥ ያገኙ ይመስላቸዋል ። “ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል” ይባላል ። አንድ ብፁዕ አባት አዲስ አበባ ውስጥ ባለ በአንድ ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ሲያልፉ ሕዝቡ መንገዱን ሞልቶት ማለፊያ አጥተው ቆሙ ። የመኪናቸውን መስተዋት ወረድ አድርገው አንዱን ምእመን ጠሩትና ፡- “ልጄ እዚህ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ምን አለ ?” አሉት ። ምእመኑም፡- “አይ አባታችን የእስልምናው መሪ መሐመድ ኢየሱስ ፍጡር ነው ስላለ መምህር እገሌ መልስ እየሰጠ ነው” አላቸው ። እርሳቸውም፡- “አይ ጉድ ! ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል ፣ መሐመድ ኢየሱስ ፍጡር ነው ያለው እኮ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ነው” አሉ ይባላል ። በእውነት በዛሬ ዘመን እንኳን አዲስ ትምህርት አዲስ ኑፋቄም የለም ። ታዲያ ዕድሜና ትምህርት ያልጠገቡ ፣ እንደሆነ እንጂ ለምን እንደሆነ ስለ አንድ ነገር የማያውቁ ፣ አመክንዮንም እምነትንም ያልተገነዘቡ ወጣቶች ሊሞቱላት የሚገባትን ቤተ ክርስቲያን ከባላጋራዎች ጋር ሁነው ሊያፈርሷት ይነሣሉ ። ፍጻሜው ተያይዞ መውደቅ ነው ።
አንድ ብፁዕ አባት እንደ ገና ካርድ የተቀየሙትን ሰው ሁሉ ውግዘት ስለ መስጠታቸው ራሳቸውንና ሌሎችን ሲወቅሱ እንዲህ አሉ ፡- “በማይገባን ቦታ ስለ ተቀመጥን የማይገባንን ብንሠራ ትክክል ነው።”
አስፈላጊው ነገር የሚብረከረኩትና ወንበሩ በትክክል የሚያስፈልጋቸውን ሽማግሌ ማስቀመጥ ነው ። መቆም የሚያምርበት ወጣት ደግሞ ሊቆም ና ትእዛዝ ሊቀበል ይገባዋል ። ኦሪትም፡- “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፥ ሽማግሌውንም አክብር ፥ አምላክህንም ፍራ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ትላለች /ዘሌዋ. 19፥32/ ።
ጌታ ሆይ በማይገባን ወንበር ከተቀመጥን የሚያገኘን አጥፊው ነው ። እባክህን ስፍራችንን አሳውቀን ። ስፍራውን ባለማወቅ ስንቶ እንጀራ ፈልጎ እንጀራውን ጣለ ። ስንቱ በሚገባበት ዘመን ወጣ ። ስንቱ በሚነሣበት ወንበር ተቀመጠ ። እባክህን አምላካችን ሆይ ከእርስ በርስ ዕድር አውጣንና መንገድ የሚያሳዩ ጥበበኞችን አስነሣልን ። እኛም በመኖርና በማመን የቀደሙንን ለማክበር የቆመውን ልባችንን ዝቅ አድርግልን ።
ለሺህ ትውልድ በሚተርፈው ምሕረቱ ይጎብኛችሁ ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ረቡዕ ሚያዝያ 24/2010 ዓ.ም