መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » በቅጡ መች ላኩኝና

የትምህርቱ ርዕስ | በቅጡ መች ላኩኝና

 ሰውዬው ሀብታም ናቸው አሉ ። የእናታቸው ነገር ያሳስባቸው ነበር ። በሕይወት አሉ ቢባል ለመሄድ ስንፍና ይዋጋቸዋል ፣ ሞቱ ቢባል ባለመጦራቸው ኀዘኑ ታላቅ እንደሚሆንባቸው ያስባሉ ። አሳብ እግርን አይተካምና ዘመን አልፎ ዘመን መጣ ። አንድ ቀንም ሎሌውን ይጠሩና፡- “ቆላ ወርደህ የእናቴን ነገር ተመልከትና ስትመለስ ፣ ጤና ሆናም እንደሆነ ፣ ሞታም እንደሆነ አትንገረኝ” አሉት ። ሎሌውም የተባለበት ቦታ ደርሶ አጥሩ አጠገብ ሲደርስ ሰዎች ይሯሯጣሉ ። እኒያ የሀብታሙ እናት ሞተው አርባቸውን ለማውጣት ወዳጅ ሁሉ ይሯሯጣል ። ያም ሎሌ በረፈደው ሰዓት አዝኖ ሊመለስ ሲል የተሰጠው ትእዛዝ ትዝ አለው ። “ጤና ሆነውም እንደሆነ ሞተውም እንደሆነ አትንገረኝ” ያሉት እንደገና በጆሮው አቃጨለ ። በመጨረሻም ግማሽ ፀጉሩን ተላጭቶ ፣ ግማሹ ፀጉሩን አጎፍሮ ተመለሰ ። ጌታውም የተላጨውን አይተው፡- “ምነው ደህና አይደለም ወይ ? እናቴ ሞተች እንዴ ?” ሲሉ ሎሌውም፡- “ቢሞቱ ኖሮ መች ፀጉሬን አጎፍር ነበር” አላቸው ። “ታዲያ እናቴ ደህና ነች ወይ ?” ቢሉት “ደህና ቢሆኑ መች ፀጉሬን እላጭ ነበር” አላቸው ። በዚህ ጊዜ ተናደዱና፡- “ለምን በቅጡ አትነግረኝም” አሉት ። እርሱም፡- “መች በቅጡ ላኩኝና” ብሎ መለሰላቸው ይባላል ። 

መስማት የማንፈልገው ክፉ ነገር አለ ። መሥራት የሚያስፈልገንን ግን አናከናውንም ። ስናስበው የሚዘገንነን ነገር ብዙ ነው ። መምጫውን ለመዝጋት ግን ከአልጋችን አልወረድንም ። ውለታቸውን እያሰብን በእንባ የምናስታውሳቸው ሰዎች አሉ ። ቆርጠን ግን ሄደን አንጠይቃቸውም ። “ለእገሌ ይህን በሽታ ይስጠው !” እያልን ከእንቅልፍ ነቅተን የምናዝንላቸው ሰዎች አሉ ፣ በጠዋቱ ግን ሄድን ከመጠየቅ የፌዝ ጓደኞቻችንን ስናስስ እንውላለን ። ይህ ነገር አስቸኳይ ነው በማለት ልባችን በስጋት ይደልቃል ፣ የማያስቸኩልና የማያስፈልግ ነገር ላይ ግን ተጥደን እንውላለን ። “እገሌ እኮ” ሲባል “አሁን ሳስበው ነበር” በማለት የወሬ ጨው ጣል እናደርጋለን ፣ አሁን ተነሥተን ለመጎብኘት ግን ልምሾ እንሆናለን ። “ለእገሌ ውለታ አንድ ጥሩ ቤት ገዝቼ ባሳርፈው” እንላለን ፣ ዛሬ የሚፈልገውን ዳቦ ለመስጠት ግን እንለግማለን ። እገሌም ታዲያ እኛን ሲያስብ “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ፣ ገብስ የሚደርሰው ለፍልሰታ” እያለ ያዝንብናል ። የረፈደ ደግነት ከንፍገት እኩል ነው ። በጊዜው ያልሆነ እርዳታ ኪሣራ ነው ። “ለእገሌ ቆንጆውን የሬሳ ሳጥን  አድርጉለት ብለን ገዝተናል ፣ በቁሙ ግን ይህችን ለቤት ኪራይ አውላት አላልነው ። የሬሳ ስፖንሰር መሆን ያስደስተናል ፣ የቁም ረዳት መሆን ግን ይቀፈናል ። “እገሌ ቤት እሄድ የነበረው ሲርበኝ ነው ፣ እርሱም እንዲህ አድርጎ ይጋብዘኝ ነበር” እንላለን ፣ “ራበኝ” ብሎ ደውሎ ግን ጨክነንበታል ። 

ሞቱን መስማት የማንወደውን ሰው ኑሮውን እናጣፍጥለት ። መታመሙ የሚቆረቁረንን እንዳይታመም ትንሹን በሽታ እናክምለት ። “እርሱ እኮ የልጆቹ ነገር አያስችለውም” ከማለት ልጆቹ ሲቸገሩበት ቀኑን እናብራለት ። “እርሱ እኮ ሰው የጠገበ አይመስለውም ነበር” ከማለት የአንድ ቀን ምግቡን እንግዛለት ። ያልተመለሰ ደግነት ዕዳ ነው ። እግዚአብሔር ዛሬ በእጃችን በረከት ሲያኖር በበረከታቸው ያሰቡንን እንድናስብ ነው ። እነርሱ በረከታቸውን ወደ ራሳቸው ብቻ ቢያፈስሱ ኖሮ ዛሬ አንደርስም ነበር ። እኛም በረከታችንን መልቀቅ አለብን ። እግዚአብሔር የሚጎርስ ብቻ ሳይሆን የሚያጎርስ እጅ እንደሰጠን እናስተውል ።

ስለ እናቱ እያወራ ሃያ ዓመት በሰው አገር የቀረ ሰው አለ ። ስለ አባቱ እየተናገረ ከአገር ከወጣ ሠላሳ ዓመት የሆነው አለ ። የእናቴን ክፉ አያሰማኝ እያለ እጆቹ ግን ዱሽ የሆኑ ስንት ሰው አለ ! ጸሎት ተግባር ፣ ተግባርም ጸሎት መሆኑን የረሳ ብዙ ነው ። ስልክ እንኳ ደውሎ ፣ ራሱ መጥቶ የማያይ በሰው ሰው የራሱን ወገን የሚጠይቅ ፣ እናቱን የጎረቤቱ ጥገኛ ያደረገ ፣ ከእገሌ ውሰጂ እያለ ሰው ያየውን ስጦታ የሚያበረክት ብዙ አለ ። ሰው ያየው ስጦታ አይበረክትም ። ሰው ያየው ስጦታ የሚያየውን ለምቀኝነት ፣ የሚቀበለውን ለመሳቀቅ ይዳርጋል ። ምንም ነገር መስማት አልፈልግም ብለው ስለ አገር ፣ ስለ ሕዝባቸው ጆሮአቸውን ጠቅጥቀው የሚኖሩ አሉ ። አትንገሩኝ በማለት የሞተው ሳለ የሰሙት የሚንጣጡበት ብዙ ቲያትር አለ ። “የምጣዱ ሳለ ፣ የእንቅቡ ተንጣጣ” ይባላል ። እሳቱ ላይ ያለው የምጣዱ ታግሦ ፣ የበረደው እንቅብ ላይ ያለው አቃጠለኝ ማለቱ የማይመስል ነገር ነው ። አንዳንድ ነገሮችን በመልእክተኛ ሳይሆን ራሳችን ማየት አለብን ። ደብዳቤ እንደ ቃል ፣ ጆሮም እንደ ዓይን አይሆንም ። አገሩንም መጥቶ ማየት ፣ ወገንንም ቀርቦ መዳሰስ ይገባል ። የኖርንበትን ሰፈርና ቤት ፣ አብሮ አደግ ጓደኞች ፣ ያሳደጉንን ሽማግሌዎች ለማየት የማንጓጓ ከሆነ ፣ አቅም እያለንም ቆርጠን ካልተነሣን ከሰውነት አንሰናል ማለት ነው ። 

ሁልጊዜ ስለዚያ ሰው ደግነት የምናወራላቸው ሰዎች እግራችን ሰንፎ ፣ አፋችን ሲተጋ ይታዘቡናል ። “እንዲህ እየወደድከው እንዴት እስካሁን አስቻለህ” ይሉናል ። የትዝታን እሳት መሞቅ እንጂ የዛሬን ፍቅር መግለጥ አለመቻል ትላንትን መኖር ፣ ዛሬን መሞት ነው ። የምንልካቸው ሰዎች ራሱ ሄዶ ቢያይ ይላሉ ። የማንጨነቅ ከሆነ ይጨነቁልናል ። ስንደነድን ሌሎች ይፈሩልናል ። ለእናታችን ከእኛ ይልቅ ጓደኛ አይቀርብም ። ለአገራችንም ከእኛ ይልቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች አይቀርቡም  ። የሚያሳስቡንን ነገሮችን በጸሎትና በተግባር ልንወጣቸው ግድ ይላል ። አሊያ ወደፊት ላለመደሰት በራሳችን ላይ እንፈርዳለን ። ሰዎች ቆመው የሚጠብቁን አይደሉም ። በዛሬው ዘመን ከተሞች እንኳ እየፈረሱ ፣ ሐውልቶችም እየወደቁ ፣ ቅርሶችም እየወደሙ ነው ። ሰው ከእነዚህ ይልቅ ለማለፍ ስንዱ ነው ። ሞትን ተሸክሞ የሚጓዘውን ወዳጅ በቶሎ ማየት ከጸጸት ይጠብቃል ። በዚህ ዓለም ላይ ያለው ትልቁ ዋጋ ተገናኝቶ መጨዋወት ፣ ፍቅርን መግለጥ ነው ። እየቻልን ማርፈድ ኃጢአት ነው ።

ግልጽ ተልእኮ ግልጽ ግብ ይኖረዋል ። ሰዎች በቅጡ እንዲመልሱልን በቅጡ ልንልካቸው ያስፈልጋል ። ለዚህ ደግሞ ራእይ መሠረት ፣ ዓላማ ሕንፃ ፣ ተልእኮ ምሰሶ ፣ ጉልላት ግብ ሆነው መቀመጥ አለባቸው ። ባልገባን ነገር ላይ መተንተን ፣ በማናውቀው ነገር ላይ አሳብ መስጠት ፣ ሰዎች ሲሉ የሰማነውን ራእዬ ነው ማለት ፣ ሠርቶ ከመብላት ሰዎች የሠሩት ላይ ታጥቦ ቀረብ ማለት የትም አያደርስም ። በቅጡ ያልላክናቸው ሰዎች በቅጡ ባይሠሩ የሚደንቅ አይደለም ። ዝም አላልኩም ብለን የምንልከው ፣ የተልእኮውን መልስ ለመስማት የማንፈልገው ነገር ከሆነ መናገራችንም መላካችንም የውሸት ነበር  ማለት ነው ። የእናታችንን መኖርም መሞትም መስማት የማንፈልግ ከሆነ መስማት የምንፈልገው የራሳችንን ነገር ብቻ ነው ። ባሕላዊው የፖለቲካ ብሒላችን፡- “እንዳያማህ ጥራው ፣ እንዳይበላ ግፋው” ይላል ። ደግሞም፡- “ውጣ አትበለው ፣ እንዲወጣ አድርገው” ይባላል ። 

ምድራችን ፣ አገልግሎታችን ፣ ራእያችን ግማሽ ልጩ ፣ ግማሽ ጎፈሬ ነው ። አለ እንዳይባል የሞተ ነገር ይታያል ፣ የለም እንዳይባል የሕይወት ምልክቶች ይታያሉ ። ነገር ግን ግማሽ ልጩ ግማሽ ጎፈሬ ከሕይወት ይልቅ ለሞት ይቀርባል ። ጎፈሬው መስማት ለምንፈልገው ነገር ነው ። ልጩው ደግሞ ለእውነቱ ነው ። መስማት የምንፈልገውና የሆነው ነገር በጣም የተለያየ ነው ። ለዚህም እግር የሌለው አሳባችን ፣ ጊዜን የማያከብረው ራእያችን ፣ ግልጽ ነገር የሌለው ተልእኮአችን በዋናነት ተጠያቂ ነው ። 

ስለዚህ ቀዳሚ ተግባራችንን መለየት አለብን ። ለተግባራችንም ራሳችን መነሣት አለብን ። እውነት ተሰምቶን ከሆነ ነገ ማለትን መጠየፍ አለብን ፣ አሁን መጀመር አለብን ። 

ጌታ ሆይ ግማሽ ልጩ ፣ ግማሽ ጎፈሬ የሆነውን ኑሮአችንን ነፍስ ዝራበት ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም