የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በተሰጠን ድርሻ እንገኝ

“ሴት በነገር ሁሉ እየተገዛች በዝግታ ትማር ፤ ሴት ግን በዝግታ ትኑር እንጂ ልታስተምር ወይም በወንድ ላይ ልትሰለጥን አልፈቅድም ። አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና ፥ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች ። የተታለለም አዳም አይደለም ፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች ፤ ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች ።” 1ጢሞ. 2፡11-15
በዓለም ላይ ሰላም ከሆኑ ነገሮች አንዱ እየታዘዙ መኖር ነው ። በረከት ለሚታዘዙ እንጂ ለአዛዦች አይደለም ። እግዚአብሔር ወልድ ሰው ሁኖ የገለጠው ትልቁ ነገር ዝቅ ማለት ነው ። የሰው ልጅ የምድር ገዥ ነው ። ይህ ማለት ምድርን ይጠብቃታል ፣ ይንከባከባታል ማለት ነው ። ምድርም ለሰው ትገዛ ሲባል ታኑረው ፣ ፍሬ አብቅላ ታብላው ፣ መኖሪያና መቀበሪያ ትሁነው ማለት ነው ። ወንድ ገዥ ነው ሲባል አምባገነን ነው ማለት ሳይሆን ሴትን የሚጠብቅ ፣ የሚንከባከብ ማለት ነው ። የገዛ አካሉን የሚጠላ ማንም የለምና ወንድ ሴትን መጠበቅ ይገባዋል ። የገዛ ራሱን እንቢ የሚል አካል የለምና ሴትም ራሷ የሆነውን ወንድን እሺ ልትል ይገባታል ። ምድር ለሰው መኖሪያ እንደሆነች ሴትም ወንድ ልጅን ኑሮ ልታስይዘው ይገባታል ። ምድር ፍሬ አብቅላ እንደምትመግብ ሴትም ራስዋ ነውና ልትመግበው ልትንከባከበው ይገባታል ። ምድር መኖሪያና መቀበሪያ ናት ሴትም ባሏን በሕይወቱና በሞቱ አብራው ልትቆም ይገባታል ።

በዝግታ መኖር ለሴት ብቻ ሳይሆን ለወንዶችም በጣም አስፈላጊ ነው ። በዚህ ክፍል ዝግታ የተባለው ማዳመጥ ነው ። ዝግታ ሕይወት ሊሆን ይገባል ። ብዙ ከመናገር ብዙ መስማት ተገቢ ነው ። ብዙ መናገር እኔ ብቻ አውቃለሁ ባይነት የሚያመጣው ነው ። ብዙ መናገር ጭንቀት ሲጫጫነን የሚመጣ ጠባይ ነው ። ብዙ መናገር ሱስ ሁኖ የሚያስለፈልፈን ነው ። ዝምታ አያጸጽትም ፣ ንግግር ግን ብዙ ጊዜ ያጸጽታል ። መናገር በሚገባ ቦታ ላይ ዝም ማለትም ተጠያቂ ያደርጋል ።
ሴቶች የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና አስተማሪ እንዲሆኑ አልተፈቀደም ። ይህ ሴቶች በሰውነት ትንሽ ናቸው ማለት ሳይሆን ያልተሰጣቸው ድርሻ ነው ማለት ነው ። ሴቶች በወንዶች ላይ እንዲሰለጥኑ አልተፈቀደም ። ሴቶች ሴቶችን እንዲመክሩና ሕፃናትን እንዲያስተምሩ ግን ክልክል ነው አልተባለም ። ሁሉም ወንዶች የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪና ሰባኪ አይደሉም ። የክህነት ማዕረግና አስተማሪነት የተሰጠው ለጥቂቶች ነው ። በብሉይ ኪዳንም ከአሥራ ሁለቱ ነገዶች አንዱ የሌዊ ነገድ ሲመረጥ ፣ ከሌዊ ነገድም የአሮን ቤተሰብ ብቻ ለካህንነትና ለሊቀ ካህንነት ተመርጠዋል ። በአዲስ ኪዳንም ሁሉም ወንዶች ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተዳድሩና የሚያስተምሩ አይደሉም ። ሴቶች ግን በክህነት እንዲያስተዳድሩና እንዲያስተምሩ አልተፈቀደም ።
ይህ መልእክት ጢሞቴዎስ ያስተዳድራት የነበረችውን የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ብቻ የሚመለከት እንጂ ዓለም አቀፋዊ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ ። ሐዋርያው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ መልእክት እንደ ላከ ቀጥሎ እናያለን ። ሴቶች በማኅበር ዝም ይበሉ ፤ ሕግ ደግሞ እንደሚል እንዲገዙ እንጂ እንዲናገሩ አልተፈቀደላቸውምና ። ለሴት በማኅበር መካከል መናገር ነውር ነውና ፥ ምንም ሊማሩ ቢወዱ በቤታቸው ባሎቻቸውን ይጠይቁ” ይላል ። /1ቆሮ. 14፡34-35/ ። የሴቶችን አለባበስና የማስተማር ጉዳይ በዚያ ዘመንም ያልተቀበሉ ሰዎች ነበሩ ። ሐዋርያው ግን የማሰሪያ ምክንያቱ፡- ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ፥ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም” የሚል ነው 1ቆሮ. 11፡16 ። ዳግመኛም ወንዶች እንዲያስተምሩ መፈቀዱን አንዳንዶች ያጉረመረሙበትን ምክንያት ይናገራል ። ምን ነው? የእግዚአብሔር ቃል የወጣ ከእናንተ ነውን? ወይስ ወደ እናንተ ብቻ ደርሶአልን? ማንም ነቢይ ወይም መንፈሳዊ የሆነ ቢመስለው ይህች የጻፍሁላችሁ የጌታ ትእዛዝ እንደ ሆነች ይወቅ” ይላል ። /1ቆሮ. 14፡36-37/። የጳውሎስ ግላዊ አስተሳሰብ ነው ለሚሉ የጌታ ትእዛዝ ነው ደግሞም ሕግ እንደሚል ይላል ።
ሴቶች በክህነትና በማስተማር እንዳያገለግሉ የተከለከለው በአጥቢያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፋዊ ደረጃ ነው ። ምክንያቱ ብሉይና አዲስ ሳይሆን ወደ ጥንተ ተፈጥሮ የሚመልሰን ነው ። ሐዋርያው፡- አዳም ቀድሞ ተፈጥሮአልና ፥ በኋላም ሔዋን ተፈጠረች ። የተታለለም አዳም አይደለም ፥ ሴቲቱ ግን ተታልላ በመተላለፍ ወደቀች” ይላል ። ምክንያቱ ሁለት ነው ። የመጀመሪያው አዳም ቀድሞ የተፈጠረ ሲሆን ሔዋን ደግሞ ከአዳም ጎን የተገኘች ናት ። አዳም ቀዳማዊ በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪነትና አስተማሪነትን ወስዷል ። ሁለተኛው የሰይጣንን ምክር ሰምታ የወደቀችውና አዳምንም ያሳተችው ሔዋን ናት ። በዚህ ምክንያት ከዚህ ታላቅ አደራ እንደገና በቀላሉ በመሳሳት እንዳትወድቅ ተከልክላለች ። ነገር ግን ሴት የተሰጣት ሌላ ትልቅ ድርሻ አለ ።
“ነገር ግን በእምነትና በፍቅር በቅድስናም ራሳቸውን እየገዙ ቢኖሩ በመውለድ ትድናለች” ይላል ። ከላይ ስለ ጌጥ መውደድ ተናግሮ ነበርና እምነት ፣ ፍቅርና ቅድስና እንዲሁም ራስን መግዛት እንደሚሻል እየተናገረ ነው ። ሴት በመውለድ የምትድነው እመቤታችን ድንግል ማርያምና ጌታችን የሔዋን ልጆች ሁነዋልና በመውለድ ትድናለች ። የሞት በር ነበረች ፣ እመቤታችን የሕይወት በር ሆነች ። ሞት በሴት መጣ የሴት ዘር የሆነው ጌታችን ሕይወትን ለዓለም ሰጠ ። በዚህም ካለባት ወቀሳ ከሰሳ በመውለድ ድናለች ።በመውለድ መዳን ትውልድን በማስተማርና በመቅረጽ ኃላፊነቷን ትወጣለች ማለትም ነው ።
1ጢሞቴዎስ 31
ጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ