የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በተዘጋው የሚመጣ /4/

 “ያም ቀን እርሱም ከሳምንቱ ፊተኛው በመሸ ጊዜ ፥ ደቀ መዛሙርቱ ተሰብስበው በነበሩበት ፥ አይሁድን ስለ ፈሩ ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ ፥ ኢየሱስ መጣ ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ።” /ዮሐ. 20፡19 ።/
ሦስት ዓይነት መሰባሰቦች እንዳሉ እናያለን ። ደቀ መዛሙርት በምሴተ ሐሙስ ፣ በሰንበት ፣ በእሁድ ምሽት የተሰባሰቡት መሰባሰብ ልዩ ልዩ ፍቺ አለው ። በምሴተ ሐሙስ ክርስቶስ መምህረ ፍቅር ወትሕትና ሁኖ ኪዳን ያደረጉበት ነው ። ሰንበት ሕግን በማክበር አንድ ላይ የሆኑበት ነው ። እሁድ ምሽት በፍርሃት ብርድ ተመትተው እንዲሞቃቸው የተጠጋጉበት ነው ። ከመከራ ሰዓቶች በፊት አስደናቂ ኅብረቶች ይታያሉ ። የክርስቶስን ፍቅር የሚካፈሉበት ፣ ትሕትናን እንደ ልብስ የሚታጠቁበት ውብ ጊዜዎች ያልፋሉ ። ይህን ኅብረት አንዳንድ ጊዜ መከራ ያፈርሰዋል ። መከራው የክርስቶስ ፣ ፈተናው ግን የደቀ መዛሙርቱ ነበረ ። እርሱ መከራ ለተቀበለ እነርሱ ተናወጡ ። እኛ ለተጎዳን ሰዎች መራቃቸውና መለወጣቸው ይገርመን ይሆናል ። በጌታችን የሆነውም ይህ ነው ። ሰንበት የሰበሰባቸው ሕግን መተላለፍ ስለማይችሉ ነው ። ሰንበትን የተላለፈ ታላቅ ቅጣት ይገጥመው ነበር ። የሕግ ቅንዓት የሚሰበስበው ኅብረት አለ ። ይቀጣ ፣  ይወገዝ ፣ ይወገድ ፣ ይወገር የሚሉ አንቀጾች አንድ የሚያደርጉአቸው ፣ በሌሎች ለመፍረድ የሚሰባሰብ ሸንጎ አለ ። ይህ ኅብረት ሰንበት ሲያልፍና መውጣት ሲቻል ይበተናል ። ጉዳያቸው ያሰባሰባቸው ጉዳያቸው ሲሞላ ይለያያሉ ። ድንበር ላይ የሚሰባሰቡ ድንበሩ ሲከፈት ይለያያሉ ። ሌላውን ለማጥፋት የሚሰባሰቡ በመጨረሻ ይጠፋሉ ። የእሑድ ስብስብም ፍርሃት የወለደው ስብስብ ነበር ። ብርድ ሲያንቀጠቅጠን እርስ በርስ እንጠጋጋለን ። የጋራ ችግርና ፍርሃት አንድ የሚያደርጋቸው ሰዎች አሉ ። እውነተኛ ኅብረት ግን በክርስቶስ ፍቅር ተማርኮ ፣ በክርስቶስ ትሕትና ለመኖር የሚፈልግ ነው ።

ለክርስቶስ ብዙ የሚጋደሉ ፣ እስከ ሞት ድረስም አብረውት የሚቆሙ የሚመስላቸው ደቀ መዛሙርት ስሜታቸውና እውነታቸው ተለያየ ። የተሰማን ሁሉ ቢሆን ጠቃሚም ጎጂም ነው ። ስሜት የእርግጠኛ ጉዳትና የአጠራጣሪ ጥቅም መገኛ ነው ። ብናገኝ ወርቅ የምናለብሳቸው የሚመስለን ሰዎች አሉ ። ስናገኝ ትዝ አይሉንም ። ስንሾም አማካሪ የምናደርጋቸው የሚመስሉን ሰዎች አሉ ። ስንሾም እንደ ተቀናቃኝ እናያቸዋለን ። ጊዜውን ስንቀበል በቅን እንደምንፈርድ እናስባለን ። ጊዜን ስንቀበል ግን ቅንቅን እንሆናለን ። ወዳጃችን ቢነካ ከፊት ለፊቱ ቆመን፡- “እኔን በመጀመሪያ ግደሉኝ” የምንል ይመስለናል ። ወዳጃችን ሲነካ ግን፡- “ይህ ዓለም ለደጎች አይሆንም” እያልን ሹልክ እንላለን ። ስለራሳችን ያለን ከፍ ያለ ግምትና ስለ ሰዎች ያለን ዝቅ ያለ ግምት በትንሣኤው መነጽር መስተካከል አለበት ። ስንት ዘመን ተፈትነን ቀለን ተገኘን ? ጎረቤታችን ተርቦ መቼ አካፈልነው ? የምንወደው ሰው ታሞ መቼ ጠየቅነው ? የሥራ ባልደረባችን ታስሮ መቼ ጎበኘነው ? በልጅነታችን በጣም ይወደን የነበረውን ያንን ሽማግሌ መቼ አሁን ፍቅር ሰጠነው ? እርሳስ የገዙልንን መቼ አስታወስናቸው ? ቃለ እግዚአብሔርን ያስተማሩንን መምህራን መቼ እግዚአብሔር ይስጥልኝ አልናቸው ? መስቀሉ ዛሬም አለ ። ትንሣኤም ዛሬ አለ ። መስቀል መሆንና መስቀል መሸከም ግን ልዩነት አለው። ለሌሎች መከራ መሆንና የሌሎችን መከራ መካፈል ልዩነት አለው ።
ብዙ ብናበላ ብዙ የሚደርስልን ወገን የምናገኝ ይመስለናል ። ይህ ፍጹም የተሳሳተ ግምት ነው ። ዓርብ ሲመጣ የበሉ አይገኙም ። እንዲሁ ደግ እንሁን እንጂ ለዓርብ/ለመከራ ቀን እያልን ገንዘባችንን አንጨርስ ። ዓርብ ሲመጣ እስከ መስቀል የሚጓዙ ወዳጆች ብቅ ይላሉ ። እነዚህ የማይፎክሩት እመቤታችንና ዮሐንስ ወንጌላዊን የሚመስሉ ናቸው ። በሩቅ የሚከተሉ ከኅሊና ክስና ከልብ ፍቅር ጋር የሚታገሉ ጴጥሮሶች አሉ ። ገበያ ከተገኘ የማይሸጥ የለም ብለው እንደ ይሁዳ የሚሸጡንም አሉ ። “መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል” እንዲሉ ። ሰንበት የበለጠ ቁጭ ያደርጋል ። የሮጠም የበረረም የግድ መቀመጡ አይቀርም ። መቀመጥና ማረፍ ግን ልዩነት አለው ። መቀመጥ በሕግ ፣ ማረፍ ግን በክርስቶስ ነው ። ዓርብ ምሽት የገባው ሰንበት ቁጭ ባያደርጋቸው ኖሮ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌምን ለቀው ፣ ድንበርም ጥሰው ደማስቆ ይገኙ ነበር ። እስከ መጨረሻው እንዳንቀል እግዚአብሔር ሰንበትን ያመጣል ። እሑድ ጠዋት ጉዞ እንዳይጀምሩ መግደላዊት ማርያምን ላከባቸው ። ክህደትን ያልጀመረ የለም ፤ ያልጨረሰ እንጂ ። የሕይወት ሰንበት ሲመጣ ማለት በእስር ቤት ፣ በአልጋ ፣ በማጣት ፣ በብቸኝነት ስናሳልፍ ጨርሰን እንዳንጠፋ መጠበቂያ ነው ። እግዚአብሔር ምሽትን እያመጣ ሰውን ባይሰበስበው ኑሮ ስንቱ እቤቱ ሳይገባ ያረጅ ነበር ። ብቻ ዕድሜአችን ሲገፋ ዓለምን ለማትረፍ ክርስቶስን መካድ ከንቱ መሆኑን እንረዳለን ።
ቅዱሳን ሐዋርያት አይሁድን በጣም ፈርተው ነበረ ። አይሁድ እነርሱን እንዳይፈልጉም ክርስቶስ ቤዛ ሁኖላቸዋል ። ጨካኞች እኛን የማይፈልጉን ለእኛ ቤዛ የሆኑ ሰዎች ስላሉ ነው ። ያለ ቤዛ መኖር ይቅርና መዋል አይቻልም ። ተክሉ ተቆርጦ ሲቀቀል እኛን ለማጥገብ ነው ። ለማኖር መሞት አለበት ። በጉ ታርዶ ሲበላ ይህም እኛ እንድንኖር ዛሬ የሞተ እንስሳ አለ ማለት ነው ። ከበደል በኋላ ሕይወት ያለ ቤዛነት አይቀጥልም ። ደቀ መዛሙርቱ የፈሩት የሚያስፈራ ነገርን ሳይሆን የሚያስፈራራቸውን የአእምሮ ሥዕል ነው ። ራሱ ፍርሃት እንጂ ሌላ አስፈራሪ አልመጣባቸውም ። ፍርሃት ቁልፍ ይወዳልና የውጭውን በር ቆለፉት ። ፍርሃት ቁልፍ አይጠግብምና የሳሎኑን በር ከረቸሙት ። ፍርሃት ልክ የለውምና ወደ ሰገነቱ የሚያወጣውን የደረጃውን በር ቀረቀሩት ። ፍርሃት እስከዚህ አይልምና የሰገነቱን በር ዘጉት ። ይህ ሁሉ ሁኖ በፍርሃት ይናጣሉ ። የተዘጋው ደጅ ሳይሆን ደጆች ናቸው ። ከኤማሁስ የተመለሱ ሉቃስና ቀለዮጳ የሆነውን ሁሉ ተናገሩ ። ችግር ለየራስ ነውና የኤማሁስ መንገደኞች ተስፋ መቍረጥ ፣ ሐዋርያትን ደግሞ ፍርሃት ይዋጋቸው ነበር ። ተመስጠው ያንን የኤማሁስ ገጠመኝ ሲሰሙ ጌታችን በመካከላቸው ቆመ ። በር አልተንኳኳም ። በሩን ቢያንኳኳ ልባቸው የሚከዳቸው ፣ ደማቸው የሚፈላባቸው ብዙዎች ነበሩ ። ጌታ ግን አቅማቸውን አየ ። አዘነላቸው ። ያሉበት አቅም የበር ማንኳኳትን እንኳ የማይቋቋም እንደሆነ ተረዳላቸው ። የስልክ ጥሪ የሚረብሻቸው ፣ የደወሉለት ሰው ስልክ ካላነሣ የሚጨንቃቸው ፣ መረሳት የሚያስፈራቸው ፣ ለአትርሱኝ ሰው የሚበጠብጡ ብዙ ናቸው ። ጌታ ለእነዚህ ሁሉ ደንባሮች “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ይላል ።
ቅዱሳን ሐዋርያት የተነሣውን ጌታ በዓይናቸው አዩ ። እኛ ደግሞ በዓይናቸው ያዩት የመሰከሩልንን እናምነዋለን ። አይተው አመኑ ፣ አምነን እናያለን ። ከፊት ለፊት ያለውን ያመኑ ነቢያት ተባሉ ። ከኋላ ያለውን ያመኑ ሐዋርያት ተባሉ ። ነቢዩ ኢሳይያስ፡- “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች” ብሎ ስለ አማኑኤል ተናገረ ፣ አመነ ። ሐዋርያት ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ አመኑ ። ከሞት ከተነሣ ሰው ጋር ግንኙነት አድርገን ብናውቅ ብዙ ነገሮች ይገቡን ነበር ። ከሞት የተነሣ ወዳጅ ስስት ነው ። ክርስቶስ ከሞት የተነሣ ወዳጃችን ነው ። እናቶቻችን፡- “የሞት ትራፊዬን አትንኩብኝ” ይላሉ  ። አዎ እርሱ ተነሥቷል እኛም እንነሣለን ። ከሞት በፊት የሚያውቁትን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በኋላም አውቀውታልና እኛም በሰማይ እንተዋወቃለን ። በትንሣኤ አካል እንከን የለም ። ዛሬ ዓይኑ የታወረ ፣ እግሩ የሚያነክስ በትንሣኤ አካል ሙሉ ነው ። የማይታየው አብን ወልድ እንደ ተረከው ክርስቶስም ወደ ረቂቅ ግዛቱ ሲገባ ሐዋርያት ተረኩት ። እንዲተረክልን እንሰወር ።
ተፈጸመ
የመስቀሉ ገጽ 9/መ
ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ