የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በቸርነቱ ያዳነን

“ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን ፥ በጸጋ ድናችኋልና ፥” ኤፌ. 2፡3-4 ።

እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ተብሏል ። የዚህ ዓለም ባለጠጎች በቁሳዊ ነገር ባለጠጋ ሊሆኑ ይችላሉ ። በምሕረቱ ባለጠጋ የተባለ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ምሕረቱ ከፍቅሩ ጠባያት አንዱ መገለጫ ነው ። የምሕረቱም ገጸ በረከት ቸርነቱ ነው ። ፍቅሩ እንዲሁ መውደዱ ነው ። ፍቅሩ ዓለም የተፈጠረበትና ዓለም የዳነበት መነሻ ነው ። ምሕረቱ አዳምን በገነት የፈለገበት የንስሐ ድምፅና ሰው የሆነበት ግብር ነው ። ቸርነቱ ተስፋን መስጠቱና ድኅነትን ማግኘታችን ነው ። ፍቅር ፣ ምሕረትና ቸርነት ተናባቢ ናቸው ። የአብ ጸጋ ፣ የወልድ ፍቅር ፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችን ጋር ይሁን የሚለውን ለዋውጠን መጠቀም እንችላለን ። ጸጋ ፣ ፍቅር ፣ አንድነት መለኮታዊ ግብራት ሲሆኑ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ የሚያደርጋቸው በጎነት ናቸው ። እነዚህ ጸጋ ፣ ፍቅርና አንድነት የአንድ መለኮት የባሕርይ ግብር ናቸው ። ፍቅሩን ስናስብ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ምክር እናስባለን ። ምሕረቱን ስናስብ የወደቀን የሚፈልግና ንስሐን የሚወድ አምላክ መሆኑን እንገነዘባለን ። የነቢያት የሐዋርያት አገልግሎትም ንስሐን ለሰዎች ማወጅ ነው ። ቸርነቱ ደግሞ አማኝ የተባልንበት ነው ።

ወደ ምሥጢረ ሥጋዌ ስናመጣው ፍቅሩ እግዚአብሔር ወልድን ከሰማይ ያወረደ ፣ “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ፣ ወአብጽሖ እስከ ለሞት” የተባለበት ነው ። ምሕረቱ ደግሞ በመስቀል ላይ የዋለበት ቤዛነት ነው ። ቸርነቱ የድኅነት ጸጋን የተቀበልንበት ነው ። ምሥጢረ ሥጋዌ ሦስት ክፍሎች አሉት ። የመጀመሪያው ሰው የመሆኑ ምሥጢር ነው ፤ ሁለተኛው በመስቀል ላይ የፈጸመው የቤዛነት ሥራ ነው ። ሦስተኛው የዳነች አንዲት ቤተ ክርስቲያን ወይም ማኅበረ ምእመናን የተመሠረተችበት ነው ። ሰው መሆኑን ፣ ማዳኑንና መዳናችንን አስተባብረን ማየት ይገባል ። ድንሃል የሚለው ቋንቋ ቁንጽል ነው ። ለመዳን የተከፈለውን ዋጋ ማሰላሰል ፣ የመዳንንም ዓላማ ማለትም ቅድስናን ማሰብ ይገባናል ።

በአዳም በደለኞች ተብለን ፣ የበደል ዋጋ የሆነው ሞትም ደርሶብን እንኖር ነበር ። ያ ማለት ግን ጽድቅ መሥራት የማንችልበት የተበከለ ማንነት ተቀበልን ማለት ሳይሆን የአባት ዕዳ ለልጅ መትረፉ እርግጥ ስለሆነ ነው ። አቤል ጻድቅ ነበረ ። ኖኅም በቅድስና ተመላልሷል ። እነዚህ ሁሉ ግን ፍጹማን አልነበሩም ። አዳም ከመበደሉ በፊት የነበረውን ሐዲስ ተፈጥሮ አላገኙትም ። ከሰማዕትነት የሚቆጠረውን ሥጋን እንቢ ማለት ግን ፈጽመዋል ። የአዳም ኃጢአት ያዘጋውን ገነት የእነዚህ ሁሉ ጽድቅ ማስከፈት አልቻለም ። ስለዚህ በቀዳማዊ አዳም የተዘጋ በር በዳግማዊ አዳም በክርስቶስ ተከፈተ ። ይህም ስለሚገባን ሳይሆን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለጠጋ ስለሆነ ነው ። የትኛውም የሰውና የመላእክት በደል ከእግዚአብሔር ምሕረት በላይ አይደለም ። ምሕረቱ ግን አስፈቅዶ ያድናል እንጂ አስገድዶ አያጸድቅም ። ገነት ባልተከፈተበት ዘመን ፣ በመካነ ሲኦል ቅድሳን ቢኖሩም በረድኤተ እግዚአብሔር ተከልለው ይኖሩ ነበር እንጂ እንደ ሌሎቹ ኃጢአተኞች ቅጣትን አላገኙም ። ለዚህም በሉቃ. 16፡19-31 ያለውን ማንበብ ይቻላል ። ሙሴና ነቢያት በነበሩበት ዘመን አብርሃም በረድኤተ እግዚአብሔር ተከልሎ በዓለመ ነፍስ ይኖር ነበር ። የእግዚአብሔር ምሕረት ኃጥኡን ለንስሐ ማብቃት ብቻ ሳይሆን ጻድቁ ከክፉዎች ጋር እንዳይቀጣም ይከልል ነበር ።

የወደደን እግዚአብሔር ነው ። ፍቅሩም በመልኩ በአምሳሉ እኛን የፈጠረበት ፣ የማይሞተው አምላክ ሥጋ ለብሶ የሞተበት ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ፍቅሮች ቢኖሩም ይህ ፍቅር ትልቅ ነው ። ከዘላለም ሞት አይደለም ከሥጋ ሞት የሚያድን ፍቅር በዓለም ላይ የለም ። ትልቁ የእግዚአብሔር ፍቅር ግን በማዳን የበረታ ነው ። እርሱ የወደደን ያልበደለውን ማንነታችንን ብቻ ሳይሆን በደልና ኃጢአት ሙታን አሰኝቶን በነበረ ሰዓትም ወዶናል ። የሞት አጋፋሪ የሆኑት የሥጋ ፈቃድና የዓለም ምኞት እያንገላቱን ዛሬም ይወደናል ። ፍቅሩ ግን ባለንበት ኃጢአት እንድንጸና ፣ አይቶ እንዳላየ የሚያልፍ ሳይሆን ለንስሐ እንድንበቃ የሚተጋልን ነው ። በፍቅሩ ኃጢአተኞችን ቢወድድም ፣ በጻድቅነቱ ደግሞ ኃጢአትን ይጠላል ። በደልና ኃጢአት በዚህ ዓለም የሕሊና ሙት ወይም ሙታነ ሕሊና ሲያደርግ በሚመጣው ዓለም ደግሞ ዘላለማዊ ሙት ያደርጋል ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሞቱ ተነሣ ተብሎ ተነግሮለታል ። ስለ እኛ ሞተ ፣ እኛን ይዞ ተነሣ ። ከክርስቶስ ጋር ሕይወትን አግኝተናል ። መንፈስ ቅዱስም አማኙን ከክርስቶስ ጋር የማዋሐድ ሥራ ይሠራል ። በክፉ ሥራችን ከገነት ብንወጣም ፣ በደግ ሥራችን የገነት ደጃፍን ማስከፈት አልቻልንም ። በክርስቶስ ቤዛነት ፣ በመስቀሉ ሥራ የገነት ደጅ ተከፈተ ። የዳንነው በጸጋው ነው ። በሥራችን ሞተን ፣ በሥራችን አልዳንም ። አዳም ለማስኰነን በቂ ነበረ ። ክርስቶስም ሊያጸድቀን ተቻለው ። በጸጋ ድናችኋል ማለትም በቸርነቱ ድናችኋል ማለት ነው ። ኦርቶዶክሳዊነት ቤተ ክርስቲያን ድኅነተ ዓለምን ትመሰክራለች ። በድናችኋል ስም ግን እምነትና ምግባርን ፣ ሃይማኖትና ምሥጢራትን አትለያይም ። ድናችኋል ኃጢአትን የምንጥልበት እንጂ ምግባርንና ምሥጢራትን እንዲሁም አገልጋይ ካህናትን የምንገፋበት አይደለም ። ድነሃል የሥጋ አርነት መስደጃ ፣ የራሱ ጉዳይ ተብሎ ሁሉን ነገር ማስጣያ አይደለም ። ሰው የዳነበትን መንገድና የዳነበትን ዓላማ በቅጡ መማርና ማወቅ አለበት ። ከነገረ ሥጋዌ የተነጠለ የድኅነት ትምህርት የማያድን ትምህርት ነው ። ይህን የምንለው የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት የተፈጸመውን መዳንና ሁለት ሺህ ዓመታት የተሰበከውን ወንጌል ሰበር ዜና አድርገው የሚያቀርቡና ለእናታቸው ምጥ የሚያስተምሩ ወገኖች ስለፈሉ ነው ። ክርስቶስ ያዳነን የዳነ ማንነት እንዲኖረን እንጂ እገሌ የዳነ ነው ፣ እገሌ ያልዳነ ነው የሚል ሰንጠረዥ እንድንሠራ አይደለም ።

ድኅነትን ስናስብ ፍቅሩን ፣ ምሕረቱንና ቸርነቱን የሚያዘክር ሕሊና ያብዛልን !

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /31

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 10 ቀን 2014 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ