የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በኅብረት ተቀመጡ (2)

“ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፥ እነሆ፥ መልካም ነው፥ እነሆም፥ ያማረ ነው።” መዝ. 132 ፡ 1።

አንድነት በአንድ አዳራሽ መቀመጥ ሳይሆን በአንድ አሳብ መስማማት ነው ። በአንድ ላይ ተቀምጠው ኅብረት የሌላቸው አያሌ ናቸው ። የአገራት መሪዎች ፣ የአገር አስተዳዳሪዎች ፣ የቤተ ክርስቲያን አለቆች ፣ የክርስቲያን ማኅበሮች በአንድ አዳራሽ ይቀመጡ ይሆናል ። በዲፕሎማሲ መሸነጋገል ፣ በፖለቲካ ስልት ፣ ባለመተማመን ፣ እንደ ጠላት በመተያየት በአንድ አዳራሽ መቀመጥ ለዛሬ ዘመን ቀላል ተግባር ሁኗል ። ነቢዩ ያለውን እናስተውል “በኅብረት ቢቀመጡ” ይላል ። ውስጥ ልብሱ በተገለጠበት ፣ አንዱ የአንዱን ዕራቁት ለማውራት በሚቸኩልበት ፣ “እገሌን ሲያወራ ቀዳሁት” እየተባለ ወንድም ወንድሙን በሚሰልልበት ፣ በደግ ዘመን ለክፉ ቀን ይሆነኛል ተብሎ ነውር እንደ መረጃ የሚያዝበት በዚህ ዘመን አንድነት የሚናፈቅ ነው ።

ሰዎች ለመገናኘት ሳይሆን ላለመገናኘት በሚመኙበት ፣ “ላለመስማማት እንስማማ” የሚል ፈሊጥ በጠነከረበት ፣ ሰው ጎረቤቱን አኩርፎ ሩቅ አገር ካለ ሰው ጋር በማኅበራዊ መገናኛ በሚያወራበት የሕልም ዘመን አንድነት እየተሸኘ ይመስላል ። በማኅበራዊ መገናኛ 5ሺህ ጓደኛ ሊኖረን ይችላል ። አንዱም ስንጨነቅ አይደርስልንም ። “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” የሚባለው እውነት ነው ። ቤትህ በእሳት ቢነድድ ጎረቤትህ እንጂ ዘመድህ አያጠፋውም ። አካላዊም አሳባዊም መቀራረብ እርሱ ኅብረት ይባላል ። በቅርብ ዘመን የተከሰተው ወረርሽኝ ዓለምን በመከራ አንድ ያደረገ ነበር ። ተራርቆ መቆም ፣ አለመጨባበጥ ፣ “የምንራራቀው ስለምንዋደድ ነው የሚል መፈክር በዝቶ ነበር ። በሽታዎች ባሕል ጥለው ይሄዳሉና ዛሬም መጨባበጥ ፣ መቀራረብ ይረብሸናል ። የሰው ልጅ የጀመረውን ነገር ለመጀመር ይቸገራል ፣ ከጀመረ በኋላ ለማቆም አቅም ያጣል ። ለመጀመር አቅም ያጣው ፣ ለማቆም አቅም ያጣል ። ሰው የተሰጠውን የሚያሳድግ ነው ። ተራርቆ መቆምን ፣ ተራርቆ በመኖር ፣ መዋደድን ባለመጣላት እየተካው ነው ። ከዚህም ከባሰ ለጭንቀት እንዳረጋለንና ኅብረት ያስፈልጋል ።

ሰዎች ተሰብስበው ሲታዩ “እዚያ ጋ ችግር አለ ወይ?” ይላል ። መሰብሰብን የሚፈጥር ችግር ነው ። ኅብረት ካለም ችግር አለ ። ግን ቅዱስ ችግር ነው ። ሰዎች ሲሰባሰቡ የጸጥታ አካላት በንቃት ይከታተላሉ ። ኅብረት ሲኖር አስፈሪ እንሆናለን ። መሣሪያ የያዙ መሣሪያ ያልያዙትን ይሰጋሉ ። ነቢዩ ዳዊት የገዛ ልጆቹን በማሰብ ያስተላለፈው ምክር ሊሆን ይችላል ። ኅብረት በማጣት የገዛ ልጆቹ አንዱ አንዱን አስነውሯል ። አንዱ አንዱን ገድሏል ። በመጨረሻም የልጆች የመለያየት ጦስ ወደ ዳዊት መጥቶ አቤሴሎም አባቱን ከዙፋን አባሯል ። ልጆች ኅብረት ሲያጡ ወላጆች ትልቅ ኀዘንና ስጋት ውስጥ ይገባሉ ። ለውርደትም ይዳረጋሉ ። ደግ ደግ አይወልድምና የዳዊት ልጆች ክፉዎች ነበሩ ።

መልካም የሚለው ቃል የልብ ችሎት የሚሰጠው የመጨረሻው ዳኝነት ነው ። መልካም ለጠባይ የሚጠቀስ ቃል ነው ። ያማረ የሚለው ደግሞ ለውበት የሚጠቀስ አድናቆት ነው ። የመልካም ሰው መገለጫው ኅብረት መውደዱ ነው ። ከአበቦች ፣ በብዙ ምሰሶ ከቆሙ ሕንፃዎች ይልቅ ኅብረት ውበት አለው። ኅብረት እግዚአብሔርን የሚያስደስተውን ያህል ሰይጣንን ያበሳጨዋል ። ሰይጣን ከደከመ ምእመን ይልቅ የተበተነ ኅብረትን ማየት ደስ ይለዋል ። የእያንዳንዱ ምእመን ድካም ሙሉውን ኅብረት ይጎዳዋል ። የምንበረታው ለዚያ ሰው ስንልም ነው ። እኔ የእኔ ብቻ አይደለሁም ማለት ይገባናል ። ዛሬ እግዚአብሔር ወደ አገራችሁ እመጣለሁ ቢለን ምን እናዘጋጅልህ ? ማለታችን አይቀርም። እርሱም፡- “እኔ የምበላው ድግስ ፣ የምቀበለው መልካም ስጦታ ፣ ያማረው አበባ ኅብረታችሁ ነው” ይለናል ። ኅብረት በአንድ ባንዲራ ማጌጥ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ መቀባበል ነው።

ይቀጥላል ዕለተ ብርሃን 13
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ