የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በነፍስ ለዛላችሁ

“በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ።” ዕብ. 12፡3 ።
“አንቺው ጠሪ አንቺው ቀሪ” ይባላል ። እኛ ያሳመናቸው እያመኑ እኛ ማመን ሲያቅተን ፣ እኛ ጸሎት ያስለመድናቸው እየጸለዩ እኛ መጸለይ ሲከብደን ፣ እኛ ፍቅርን ያስተማርናቸው እያፈቀሩ እኛ ጠብ ሲናፍቀን ፣ እኛ አሥራት ማውጣት ያለማመድናቸው እያወጡ እኛ ንፍገት ሲጫጫነን ፣ እኛ መዝሙር መልካም ነው ያልናቸው እየዘመሩ እኛ አሸሼ ገዳሜ ሲያምረን ፣ እኛ ታገሡ ያልናቸው ሲረጋጉ ፣ እኛ ማበድ ሲጀማምረን ፣ እኛ የስብከት አትሮኖንስ ለቀንላቸው ሲሰብኩ እኛ ፖለቲካ ሲያምረን ፣ … እኛው ጠሪ እኛው ቀሪ መሆናችን ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት ያመጣናቸው ሰዎች ስላሉ ብቻ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ፣ እልህ ስላለብን ብቻ መስበክ ፣ አልጠፉም ላለመባል መዘመር ዝለትን የበለጠ እያፋፋመው ይመጣል ።
“በሰም የተጣበቀ ጥርስ ቢስቁበት አያደምቅ ፣ ቢበሉበት አያደቅ” ይባላል ። ጥርሱ ሲታይ የሚቆርጥ ፣ የሚያደቅ ፣ የሚመነጭቅ ፣ የሚቦጭቅ ይመስላል ።በርቀት ላለ ማስፈራሪያ ነው ። ቢቀርቡት ግን እንደ ነገሩ የተያያዘ ነው ። ለሳቅም ለማኘክም የማይሆን ነው ። ደስታንም መከራንም የማይችል ነው ። ሲስቅም ተጨንቆ ፣ ሲያኝክም ፈርቶ ነው ። የተጣበቀው በደካማው በሰም ነውና ። ሐሰተኛ ሳቆች ፣ የፉከራ ድምፆች ፣ ጌታን የያዘ ምን ይሆናል ? የሚሉ መግደርደሮች ፣ በትንሽ ፈተና የሚደነብሩ ማንነቶች እያንዣበቡን ይመስላል ። ለሳቅም ለኀዘንም ስሜት አልባ መሆን ከባድ ነው ። ይህ የነፍስ ዝለት ይባላል ። ስለ ባል ስለ ሚስት ብቻ አማኝ መምሰል በሰም የተጣበቀ ጥርስ ነው ። ስለ አባቶች ቊጣና ተግሣጽ ብቻ ወደ እግዚአብሔር ቤት መገስገስ ይህ በሰም የተጣበቀ ጥርስ ነው ። ተቃዋሚዎች ስላሉ ብቻ ለአገልግሎት ተፍ ተፍ ማለት ይህ በሰም የተጣበቀ ጥርስ ነው ። እውነተኛ መከፋትን ደብቆ የሌለንን ደስታ ማውራት ይህ በሰም የተጣበቀ ጥርስ ነው ። መግደርደር የበዛበት ኑሮ ፣ ለመስጠትም ለመቀበልም የማይመች ሐሰተኛ አኗኗር በሰም የተቀባ ጥርስ ነው ።
ዝለት በአንድ ጊዜ የሚመጣ አይደለም ። ዝለት የብዙ ድካሞች ጥርቅም ነው ። አንድ ነገርን ያለ ታዳሽ ኃይል የያዙ ሰዎች ዝለት ውስጥ ይገባሉ ። በነፍስ ዝለት የተያዘ ሰው ራሱን እየፈራ የሚኖር ሰው ነው ። የያዘውን ኃላፊነት በሙሉ ድንገት የሚጥለው እየመሰለው የሚበረግግ ነው ። ዝለት በድንገት ፀሐይ ስትጨልም የሚፈጠር ስሜት ነው ። ዝለት የያዝነውንና የያዘንን መልቀቅ ነው ። እግር ድንገት ሽብርክ ሲል ፣ እጅም ዛል ብሎ የያዘውን ሁሉ ሲዘረግፍ ዝለት ይባላል ። ድንገት እንደ ብራቅ ብልጭ ብሎ መናገር ፣ እንኳን ዝናብ እሳት ለምን አይዘንብም ብሎ ደፋር መሆን ፣ ለሰው ሁሉ ያለንን በጎ አመለካከት መጣል ፣ የሠራነውን ሁሉ ተግተን ስናፈርስ ፣ ቀትሩ ሲጨልምብን ፣ ሁሉም ነገር ድግግሞሽ ሲሆንብን ይህ የነፍስ ዝለት ነው ። ጠዋት ስንነሣ ተኝቶ ያደረ ሰው ሳይሆን ሲሠራ ያደረ ሰው ያህል ስብርብር ስንል ፣ ደስ ብሎን እናደርገው የነበረውን እንደ ተጋዘ እስረኛ በግዳጅ ስንፈጽም ፣ ሊመጣ የሚችለውን ማንኛውንም አደጋ መድፈር ስንጀምር ይህ የነፍስ ዝለት ነው ። ዝለት ውስጥ ስንሆን በጣም ልንመገብ አሊያም መመገብ ሊያስጠላን ይችላል ። የሚሆነው ባለፈው የሆነው ፣ የሚደረገው ሲደረግ የነበረ ይሆንብንና ድግግሞሽ እንጂ አዲስ ነገር የለም የሚል ስሜት ውስጥ እንገባለን ።
የዕብራውያን መልእክት ፀሐፊ የዝለት መነሻዎችን ይጠቅስልናል ። የቀደሙትን የቅዱሳን ሕይወት ማሰብና ማሰላሰል አለመቻል ዝለት ውስጥ ይከተናል ። ቅዱሳን በተጋድሎ ብቻ ሳይሆን በብዙ ፈተና ወስጥም ያለፉ ናቸው ። ዳዊት በእኔና በሞት መካከል አንድ እርምጃ ብቻ ቀረ እስኪል ተስፋ ቆርጧል ፣ ነቢዩ ኤልያስም ግደለኝ ብሎ ለምኗል ፣ ነቢዩ ዮናስም ከእግዚአብሔር ፊት ኮብልሏል ። የቅዱሳንን ሕይወት ስናስብ እንደገና እንበረታለን ። ገድለ ቅዱሳን እንዳንዝልና ከዛልንም እንድንበረታ ያደርገናል ። እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን” ይላል ። ዕብ. 11፡1 ። ምስክርነታቸው ሃይማኖት የሚፈጸም ሩጫ መሆኑን የሚናገር ነው ። ካዩት ፣ ከሰሙት ፣ ከቀመሱት ፣ ከተሸለሙት ቅዱሳን ይመሰክሩልናል ። እንደ እኛ ያምኑ የነበሩ ፣ በእምነት ግን ብዙ የተጋደሉ እንዳሉ መስማት ከነፍስ ዝለት ያነቃል ። ለልጆች በትምህርት ቤት ስለ አገር ጀግኖች የሚነገራቸው ጎበዝ እንዲሆኑም ነው ። ክርስትና በብዙ ዋጋ የቆመ መሆኑን እንድናውቅና በክብር እንድንይዘው ገድለ ቅዱሳን በጣም ያግዘናል ። “የሰማዕታት ደም የቤተ ክርስቲያን ዘር ነው” ይባላል ።
ወደ ነፍስ ዝለት የሚያደርሰን ሌላው ነገር “ሸክም” ነው ይለናል ። ሸክም ኃጢአት አይደለም ወደ ኃጢአት የሚያደርስ ዋዜማ ነው ። አጉል ባልንጀርነት ፣ የማይገቡ ፊልሞችና ንባቦች ፣ ከንቱ ጨዋታዎች  እነዚህ ሁሉ ለክርስትናችን ሸክም ናቸው ። ሰይጣን በሸክም ካዳከመ በኋላ በኃጢአት ይጥለናል ። ሌላው የዝለት መነሻ ኃጢአት ነው ። ኃጢአት ዛሬ በስሙ ልንጠራው ያልቻልነው ብዙ የዳቦ ስም ያበጀንለት ነው ። ዘመናዊነት ምንድነው ስንል ኃጢአትን የማቆንጀት ባሕል ነው ። የነፍስን ዝለት የሚያመጣው ሌላው ነገር ክርስቶስን አለመመልከት ነው ። አገልጋዮችንም መመልከት ዝለት ያመጣል ። ከአገልጋዮች ጋር ያለን ግንኙነት ከአገልግሎታቸው ጋር እንጂ ከኑሮአቸው ጋር መሆን የለበትም ። ድንበራችንን ካላወቅን እየሳትን እንመጣለን ። መመልከት ያለብን የጥሪውን ባለቤት ነው ። ሰርግ ቤት የሄደ ሰው የሚያየው የሰርግ ወረቀቱን ያመጣለትን ሰው ሳይሆን የጠራውን ሙሽራ ነው ። ፈረንሳዮች፡- “ወደ ቤተ ክርስቲያን በቀረብህ ቊጥር ከአምላክ ትርቃለህ” ይላሉ ። ወደ አስተዳደሩ ፣ ወደ አገልጋዮቹ የግል ሰብእና እየቀረብን ከመጣን እግዚአብሔርን ልናጣ እንችላለን ። ምክንያቱም በቤተ ክርስቲያን የተፈቀደልን መንፈሳዊነታችንን ማጠናከር ነውና ።
መሮጥ አለመቻል የነፍስ ዝለትን ያመጣል ። ወደ ክርስትና ስንመጣ በጀመርነው ትንፋሽ እየሮጥን ካልሆነ ዝለት ይመጣል ። ለመሄድ የተሠራ መኪና ሲቆም መዛግ ይጀምራል ። ሰማይን ወደብ አድርጎ የጀመረ ክርስትናም ካልሮጠ ፣ በትናንሽ ነገር ከቆመ ዝለት ይገጥመዋል ። ሩጫው በግራና ቀኝ ደጋፊ ሳይሆን ተሳዳቢ ያለው ነውና በሰማይ ያደሩትን ቅዱሳን እያሰብን በትዕግሥት መሮጥ ይገባናል ። ሊያባሩ ያልቻሉ መከራና ፈተናዎችም ወደ ነፍስ ዝለት ያደርሱናል ። ሰንሰለታማ የሆኑ ችግሮች ድንገት እንድንሰለች ያደርጉናል ። የዚህን ጊዜ የተሰቀለውን ጌታችንን ማሰብ ያስፈልገናል ። ሌላው የዝለት መነሻ ዘወትር የሚጥለን የግል ድካማችን ነው  ። የሚያበሳጩን ከጎናችን ያሉ ብቻ ሳይሆኑ በውስጣችን ያለው ኃጢአትም ነው ። ከኃጢአት ጋርም ነጻ ትግል ለማድረግ ብናስብም መልሰን እንሸነፋለን ። ሐዋርያው እንደገለጠው እስከ ደም ጠብታ ከኃጢአት ጋር መታገል ያስፈልገናል ። ተራ ትግል ሳይሆን ብርቱ ጦርነት መሆኑን ማሰብ ከነፍስ ዝለት ይታደጋል ።
የነፍስ ዝለት ሲሰማን ልናደርገው የሚገባን ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብና ማጥናት ቀዳሚው ነው ። ሸክም የሆኑብንን ነገሮች ቆርጠን መጣል ወሳኝ ነው ። ይበልጥ ክፉ ባልንጀርነቶችን መበጠስ ያስፈልገናል ። በኃጢአታችንም ንስሐ ገብተን ከእግዚአብሔርና ከራሳችን ጋር ሰላም መፍጠር ግድ ይለናል ።ዘወትርም የጠራንን ጌታ እንጂ ማንንም ማየት አይገባንም ። ገና በፈተና ላይ ያሉት ሰዎች ሳይሆን በሰማይ ያደሩትን ፣ ተጋድሎአቸውን የፈጸሙትን ቅዱሳን ማየት ይገባናል ። ሩጫው መልካም ቢሆንም ደጋፊ ሳይሆን ተቃዋሚ ያለበት መሆኑን በማሰብ በትዕግሥት መሮጥ ይገባናል ። ሯጩ የሚሮጠው የሚሸልመው ዳኛ እስካለበት ድረስ ነው ። እውነተኛው ዳኛ ፣ በጽዮን የነገሠው ክርስቶስ ጋ እስክንደርስ መሮጥ አለብን ። ያለነውም ጦር ሜዳ እንጂ ኳስ ሜዳ አለመሆኑን ማሰብ ያስፈልገናል ። ከነፍስ ዝለት ክርስቶስ ያተርፈናል ።
በላይ በሰማይ በዙፋንህ ላይ ፣ በታች በምድር በትንሿ ልቤ ላይ ላለኸው ፣ ሰጠ እንጂ አጣ ለማትባለው ለአንተ ለአምላኬ ክብርና ምስጋና አቀርባለሁ ። ሰማይን ወደብ አድርጌ እንድሮጥ ፣ አንተን ብቻ እያየሁ እንድበረታ ጸጋህ ያግዘኝ ። ያደከሙኝን ነገሮች አድክማቸው ። የበረቱብኝን ድል ንሣቸው ። በዘላለም ክብርህ አሜን ።
የዕለቱ መና 30
ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ