አእምሮ መልማት ሲያቆም ፣ ያማሩ ከተሞች በፈራረሱ ሰዎች ሲሞሉ ፣ ሰው ለሰው ተኩላው ሲሆን ፣ ሺህ መልካምነት አወዳሽ አጥቶ አንድ ስህተት እንደ ሰማይ ስባሪ ሲታይ ፣ ከፍቅር ለቂም ዋጋ ሲሰጥ ፣ ዓመት ሙሉ የለፉበትን በሰከንድ ለማፍረስ ጎበዝ ሁሉ ሲጣደፍ ፣ አባት ሰሚ ፣ መምህር ተማሪ ፣ ንጉሡ መሪ ፣ ወላጅ ውላጅ ሲያጡ እኔ እልሃለሁ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ ።
አንድነት እንደ ኮሶ ሲመርር ፣ ባንዲራ ሲወድቅ ፣ መማጸኛዋ ቤት መማጸኛ ስትፈልግ ፣ ካህን ከመንበሩ ፣ ዳኛ ከችሎቱ ፣ ሊቅ ከደቂቅ ሲርቅ ፤ መካከለኛ ጠፍቶ ሁሉ ጽንፍ ይዞ ሲተኩስ፣ ለሚነደው እሳት ውኃ ጠፍቶ ሁሉ እንጨት ሲያቀብል ፣ ድልድዮች ፈራርሰው ግንቦች ሲበዙ፤ እኔ ግን እልሃለሁ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ!
ምእመን ለመካድ ሲከጅል ፣ ወርዶ የሚያወርድ ሲበዛ ፣ ተሳዳቢ ሐቀኛ ሲባል ፣ በደሀ ደረት የሚያለቅስ ሲበዛ ፣ የሰው ሞት ለሰው ሰርጉ ሲሆን ፣ ጅረቱ ሲታገድ ፣ ምንጩ ሲነጥፍ ፣ ደጉ ሲከፋ ፣ ምስኪን ሲደፋ ፣ አስታራቂ ሲጠፋ ፣ እውነት ከዐውደ ምሕረት ሲገፋ ፣ ተመልካች ዓይን ፣ ሰሚ ዶሮ ሲታጣ ፣ የጋራ ልቅሶ አክትሞ ሁሉም በየሰፈሩ ሲያነባ ፣ የሚገዛ የሚገዛም ሲታጣ ፣ ሁሉም ልምራ ብሎ መድረሻው ገደል ሲሆን፤ እኔ ግን እልሃለሁ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ !
ሀገር የማታስቀምጥ የጋለ ነሐስ ስትሆን ፣ የእናት ቤት ሲዘጋ ፣ የወንድም አለኝታ ሲጠፋ ፣ ጓደኛ ትዳርን ሲቀማ ፣ ሰውን በቁሙ ለመውረስ ፣ በሬን እየሄደ ለመጉረስ ፣ ሠረገላን እየበረረ ለመሳፈር ፣ ይሉኝታ የለሽነት ሲነግሥ ፤ ያጎረሰ እጅ ሲነከስ ፣ አውራው ሲገረሰስ ፣ ምልክት ሲጠፋ ፣ የአባት ድንበር ሲደመሰስ ፤ በረሃው ምድረ በዳ፣ ለምለሙ የተቃጠለ ሲሆን ፣ ከሚጠበቅበት የልኩ ሲታጣ ፣ ዝናብ የሌለው ደመና ሲበዛ ፣ ትልቅ ሥራ ተጠልቶ ትልቅ ወንበር ሲወደድ ፣ ሰው ስሙን ወድዶ ሰም ሆኖ ሲቀልጥ ፤ እኔ ግን እልሃለሁ በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ !
በእንተ አብርሃም የ430 ዘመን ባርነት ተሰብሯል፣ በእንተ ዳዊት ኢየሩሳሌም ከመጣው ጦር ተጋርዳለች ፣ በእንተ ማርያም ስንልህ ከራሳችን ምርጫ አድነን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 1 ቀን 2016 ዓ.ም.