የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በክርስቶስ መረጠን

“ዓለም ሳይፈጠር ፥ በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን ።” ኤፌ. 1 ፡ 4 ።

ይህ ዓለም የተፈጠረ ዓለም ነው ። መነሻ ያለው ዓለም ነውና መድረሻ አለው ። ይህ ዓለም የተፈጠረ ዓለም ነውና ፈጣሪ አለው ። ዓለም ግኝት ነውና አስገኚ አላት ። በዘፈቀደ የተገኘ ፣ ራሱንም ያስገኘ ፍጥረት የለም ። ከፍጥረት በፊት የፈጣሪ ዕቅድ ነበረ ። ከመወለዱ በፊት የነበረ ሰው የለም ። ራሱንም ያስገኘ የሰው ልጅ የለም ። ከሰው ያነሰው ፍጥረትም ራሱን አላስገኘም ። ዓለም ሳይፈጠር ያቀደ እግዚአብሔር ነው ። ያቀደውም በፍቅር ነው ። በእውቀት ፣ በችሎታ ፣ በሀብት የሚያቅዱ ይኖራሉ ፣ እርሱ ግን በፍቅር አቀደ ። የሰውና የመላእክት ተፈጥሮ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ፍቅር ብቻ ነው ። በፍቅሩ የተፈጠረው ዓለም በፍቅሩ ዳነ ። ዓለም ሳይፈጠር የወደደን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዓለም ሲያልፍም የሚወደን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዓለም ሳይፈጠር ወዶናልና ዓለም የማይለውጠው ፣ ዘመን ሳይቆጠር ወዶናልና ዘመን የማይቀይረው ፍቅር አለው ። ዓለም ቁሳዊነት ነው ፣ ዘመንም ተለዋዋጭነት ነው ። ወዳጆችን ቁሳዊ ነገር በማግኘትና በማጣት እንከስራቸዋለን ። በማግኘታችን ቀናተኞች ይጠሉናል ፣ በማጣታችን ከዳተኞች ይርቁናል ። ዘመን ፍቅርን የሚሸረሽር ወንዝ የሆነባቸው አያሌ ናቸው ። ሕፃን ሁነው የሚወዱን አሁን ላይወዱን ይችላሉ ። የሰው ፍቅር በጊዜ ውስጥ የጀመረ ነውና በጊዜ ውስጥ ያልቃል ።

ዓለም ሳይፈጠር ፣ ዘመን ሳይቆጠር በእኛ ላይ ዓላማ የነበረው እግዚአብሔር ነው ። ወላጆቻችን ሳንወለድ ዓላማ ይኖራቸው ይሆናል ። ዓላማው ግን ስሜን ያስጠሩልኛል የሚል ይሆናል ። እግዚአብሔር ህልውናና ስም ሳይጀምር ወደደን ። እርሱ የህልውናና የስም መገኛ ነውና እጠፋለሁ ብሎ ስሙን እናስጠራ ዘንድ አልፈጠረንም ። ከመገኘታችን በፊት የመረጠን ፣ ግቡ እኔ ልሁንለት ያለን እግዚአብሔር ብቻ ነው ። እኛ ፅንስን ለማየትም ለመውደድም ይዘገንነናል ። እርሱ ግን ምንም የሆነውን ነገራችንን ወደደው ። ወላጆቻችን ሳያውቁን ያወቀን ፣ ወላጆቻችን ሳይወለዱ የወደደን ድንቅ አምላክ ነው ። ትላንትን ማሰብ ቢያስፈራን እርሱ ቀዳማዊ ነውና ትዝታችንን ይቀድሰዋል ፣ ነገ ቢያስጨንቀን እርሱ ደኃራዊ ነውና ተስፋችንን ያለመልማል ። የሰው ልጅ ኑሮ በኖረውና ባልኖረው ዘመን ውስጥ ነው ። የኖረው ትላንት ፣ የሚኖረው ነገ ያውከዋል ። እምነት ግን አሁን ነው ። አሁን በንስሐ ትላንትን መቀደስ ፣ አሁን በተስፋ ነገን መውረስ ይቻላል ።

ዓለም ሳይፈጠር ከወደደኝ ፣ ፍቅሩ ቁሳዊ አይደለም ፣ ምክንያቱም ቁሳዊው ዓለም ሳይፈጠር የነበረ ፍቅር ነውና ። ዓለም ሳይፈጠር ከወደደን ዓለም ሳይፈጠር የራሱ አድርጎ ወሰነን ። ፍቅር በልቡ ስፍራ ይሰጣልና ። የመንግሥተ ሰማያት መኖሪያ ሳይሠራ ፣ የምድር ቤት ሳይበጅ ፣ የገነት አጸድ ሳይበቅል እርሱ ግን በልቡ ላይ አሳፈረን ።

እግዚአብሔር ዓይኖቹ ንጹሕ ናቸውና በንጹሕ ዓይኖቹ አየን ። በረከሰ ዓይናቸው የሚያዩን ርኵስ ሁነን እንታያቸዋለን ። አዳም እንደሚበድል ቢያውቅም ማወቁ ግን እንዳይፈጥረው አላደረገውም ። ራሱን አስቀድሞ ቤዛ አድርጎ በምክሩ ሰጠ ። በኋለኛው ዘመን ሰው ሁኖ አዳነው ። በመፍጠሩ ፈጣሪ ፣ በማዳኑም አዳኝ ተባለ ። እርሱ የሚያየን ንጹሕ አድርጎ ነው ። የፍቅር ዓይኖቹ እንከን አይፈልጉም ፣ ተራራ ስህተት ቢያዩም ነጥብ መልካምነትን ያጎላሉ ። የፍቅር ዓይኖቹ እያፈቀሩ ያድናሉ ። ወላጆቻችን ተወልደን ቢያዩን ሳሱ ፣ እርሱ ግን ደም ሳይረጋ ፣ አጥነት ሳይሰካ ፣ በማኅፀን ህልውናችን ሳይጀምር ወደደን ። ወዳጆች አድገን ቁም ነገራችንን መዝነው ወደዱን ። እርሱ ግን ገና ደግና ክፉ ሳንሠራ ዓለም ሳይፈጠር ፣ ዘመን ሳይቆጠር አፈቀረን ። ወዳጆቻችን ፍቅራቸውን ይሸሽጋሉ ፣ እርሱ ግን እንደሚወደን ይነግረናል ። ሊጎድልብኝ ይችላል ብለን የምንወዳቸውን ወደድን ። እርሱ ግን ጉድለት ሳይኖርበት ፍጹም ሳለ ዓለም ሳይፈጠር ወደደን ። ከዓለም በፊት ወዶናልና ዓለም ሲያልፍም ይወደናል ። ከዘመን በፊት ወዶናልና ዘመን ሲታጠፍም ይወደናል ። ከዓለም በፊት ጊዜ አልነበረም ። ከጊዜ ውጭ ወዶናልና ፍቅሩ በጊዜ የማያበቃ ዘላለማዊ ነው ።

እርሱ የሚያየን ነውር የሌለን ቅዱሳን አድርጎ ነው ። ፍቅር አሟቶ ያያል እንጂ ጉድለትን አይፈልግም ። የተጠራን ብቻ ሳይሆን የተመረጥን ነን ። ሰዎች ለሰርጋቸው ከዓመት በፊት ጠርተውን ይሆናል ። እርሱ ግን ዓለም ሳይፈጠር የጠራን ነውና በጥሪው ተካካይ የለበትም ። የጠሩን ሁሉ የሚመርጡን አይደሉም ፣ እርሱ ግን በቤቴ ኑሩ ብሎ መረጠን ። የእግዚአብሔር ምርጦች ከመሆን በላይ ምንም የሚያስደስት ነገር የለም ። ምርጥነታችን የፍቅሩ መገለጫ እንጂ ሌሎችን አልተመረጣችሁም የምንልበት የልጅ መጫወቻ አይደለም ። በክርስቶስ መመረጥ በሴት ወይም በወንድ ከመመረጥ በላይ ነው ። ለዘላለም ዓላማ መመረጥ የሚገኘው ከዘላለሙ ክርስቶስ ነው ። ለመመረጣችን ደግሞ መስፈርቱ ራሱ ክርስቶስ ነው ። መራጩም መስፈርቱም ራሱ የሆነ ፣ በእኔ ይክበሩ ያለ ፣ የአብ ልጅ ቡሩክ ነው !

ያልተመረጡ ወደ ውጭ ይጣላሉ ፣ ከውድድር ውጭ ይሆናሉ ። ጊዜ አልፎባችኋል ሌላ ዕድል ጠብቁ ይባላሉ ። መመረጥ ግን ማረፍ ነው መመረጥ ግን መክበር ነው ። መመረጥ ግን የክርስቶስ ቤተሰብ የቤተ ክርስቲያን አካል ለመሆን ነው ። ተመርጫለሁ ብለን የሥነ ልቡና መነቃቃትና ፉከራ እንድናሰማ ሳይሆን የአካልነት ስሜት ተሰምቶን ለወንድማችን እንራራ ዘንድ በክርስቶስ ተመረጥን ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /6

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 5 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ