መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » “በጌታ እስር የሆንሁ”

የትምህርቱ ርዕስ | “በጌታ እስር የሆንሁ”

 ክፍል 2

“በጌታ እስር የሆንሁ”

 

መከራን ማጥራት የክርስትና ትምህርት ነው ። ነቢያት ስለ ክርስቶስ መከራ ተቀበሉ ፣ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ቤዛ ሆነ ፣ ፈያታዊ ዘየማን ስለ ኃጢአቱ ተሰቀለ ። መከራን አሳዛኝና አስደሳች የሚያደርገው የምንቀበልበት ምክንያቱ ነው ። ክርስቲያን የቤዛነት መከራን እንደ ክርስቶስ መቀበል አይችልም ፣ በአንዱ አዳም እንደሞትን በአንዱ ክርስቶስ መዳናችን ግድ ነው ። አንዱ አዳም ለኵነኔ በቂ ሆኖ ራሱንና ልጆቹን ካስኮነነ ፣ አንዱ ክርስቶስ በቂ ሆኖ የሚምኑበትን ያድናል ።

ክርስቲያን እንደ ፈያታዊ ዘየማን ገንዘብና ነፍስን በመስረቅ መከራ ሊቀበል አይገባውም ። ወንጀለኛና ሰማዕት እኩል መከራ ቢቀበሉም እኩል ክብር ግን የላቸውም ። ክርስቲያን እንደ አባቶቹ ስለ እውነት መከራ መቀበል ይገባዋል ። ክርስትና እዚህ የደረሰው በዋጋ ነው ። ነገ ላይ የሚደርሰውም እኛ በምንከፍለው ዋጋ ነው ። 

ሐዋርያው ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክታት የኤፌሶንና የፊልጵስዩስ መልእክታት አስደናቂና መንፈስን ማራኪ ናቸው ። ሁለቱም የተጻፉት በሮም ነው ። ሐዋርያው በሮም የተገኘው ሰባኪ ወይም አገር ጎብኚ ሆኖ ሳይሆን እስረኛ ሆኖ ነው ።

እስረኝነት ያልጋረደው የክርስትና እውነትና ደስታ በእነዚህ መልእክታት ውስጥ ይታያል ። እግዚአብሔር ከሦስት ነገሮች በላይ ነው ። ከጊዜ ፣ ከቦታና ከሁኔታ በላይ ነው ። የኤፌሶንና የፊልጵስዩስ መልእክታት ምእመን እግዚአብሔርን ይዞ ከጊዜ ፣ ከቦታና ከሁኔታ በላይ እንደሚሆን የሚናገሩ ናቸው ። ከቦታ በላይ መሆን እንደሚገባን ሲገልጥ በሰማያዊና በመንፈሳዊ በረከት የባረከን ይላል ። ከጊዜ በላይ መሆናችንን ሲያስረዳ ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ ይላል ። ከሁኔታ በላይ መሆኑን ሲገልጥ እስረኛ ሳላ ነጻ ነን የሚሉትን ያጽናና ነበር ።

  የኤፌሶን መልእክት ምዕራፍ አንድ በሰማያዊና በመንፈሳዊ ስፍራ ስለ መቀመጥ ይናገራል ። ሐዋርያው ሥጋዊ አካሉ በሮም ጠባብ እስር ቤት ቢሆንም እርሱ ግን በሰማይ እንዳለ ይሰማዋል ። ምዕራፍ ሁለት ሞት ነበር ሆኖልኛል ብሎ ሲጽፍ ፣ ጊዜያዊ እስራቱ የዘላለም ሞት ምትክ መሆኑን ተረድቷል ። በምዕራፍ ሦስት ከለመነው በላይ አትርፎ የሚሰጠን ሲል ደግሞ ኢየሩሳሌም በሰላም ለመድረስ ጸልዩልኝ ብሎ ፣ እግዚአብሔር አትርፎ ሰማውና እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም ተወሰደ ፤ ይህም ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለቄሣር ወንጌልን ለመስበክ ዕድል የሰጠው ነው ። ምዕራፍ አራት በጌታ እስር የሆንሁ እኔ ሲል ያሳሰሩትን  አይሁዳውያንና ያሰሩትን ሮማውያን ረስቶ በእግዚአብሔር ፈቃድ እዚህ አለሁ እያለ ነው ። በምዕራፍ አምስት ስለ አጋፔ ፍቅር ሲናገር ያለምክንያት የወደደንን አምላክ በምክንያት እንኳ እንውደደው እያለን ነው ። በምዕራፍ ስድስት የሚጠብቀውን ወታደር የደንብ ልብስ እያየ ስለመንፈሳዊ ውጊያ ሲጽፍልን ፣ አስጨናቂዎቻችንም አስተማሪዎቻችን ናቸው ማለቱ ነው ።

ይልቁንም በኤፌ 6 ፡19 -20 “ደግሞ የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆንሁ፥ መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ” በማለቱ ሐዋርያው የእስር ቤት በሮች እንዲከፈቱለት ሳይሆን አፉ ለጸድቅ ቃል እንዲከፈት ፣ ሰንሰለት እንዲወድቅለት ሳይሆን ብዙዎች ነጻ እንዲወጡ ጸልዩልኝ ይላል ።

 ሐዋርያው “በጌታ እስር የሆንሁ እኔ” ይላል። ሐዋርያው በዚህ ሰዓት የቄሣር እስረኛ ነው ። እርሱ ግን  የክርስቶስ እስረኛ ነኝ እያለ ነው ። እንደ እግዚአብሔር አሳብ ስለተጓዘ የፍርድ መዛባትና እስራት እንኳ ለአእምሮው ጥያቄ አልሆነበትም ። እግዚአብሔር  ከዮሴፍ ጋር በእስር ቤት እንደነበረ ፣ ከጳውሎስም ጋር በሮም ወኅኒ ቤት ውስጥ ነበር ። ሐዋርያው ሰዎችን ካሳሰረበት ሳውልነቱ  ፣ ለክርስቶስ የታሰረበት ጳውሎስነቱ ደስታ ሰጥቶታል ። “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ቢል ኖሮ እስጢፋኖስን አስገድሎ የእስጢፋኖስ ፍሬ አይሆንም ነበር ። እስጢፋኖስ ከኢየሩሳሌም አልዘለለም ፣ የደሙ ነጠብጣብ ግን ዓለምን የሚዞር ጳውሎስን ወለደ ።

ሐዋርያው “በጌታ እስር የሆንሁ እኔ” ብሎ ሲናገር ምክንያቱ የታወቀ መከራ የሙሽርነት ያህል እንደሚያስደስት እየተናገረ ነው ። ነጻ ሰውና ነጻነት ያለው ሰው ልዩነት አለው ። ሐዋርያው ነጻነት አለው ፣ እስረኛ በመሆኑ ግን ነጻ አይደለም ። ራሳችንን በሕመም አልጋ ብናገኘው “በክርስቶስ እስር የሆንሁ” ማለት እንችል ይሆን? እግዚአብሔር በሚያውቀው ሁኔታ ውስጥ እያለፍን ነውና ከሳሽ አይሁዶችን ፣ ፈራጅ ቄሣርን ትተን በጌታ እስር የሆንኩ ማለት ይገባናል ።

በእስር ቤት ውስጥ ብንሆን እንኳ ፣ መንፈሳችን ግን ያለው በሰማያዊና በመንፈሳዊ ስፍራ ነው ። የተገፋን ብንሆን እንኳ ፣ የዘላለም ሞት በነበር የቀረልን ሰዎች ነን ። ጥሩ ሠርተን ክፉ ቢገጥመን ከለመነው በላይ አትርፎ ሊሰጠን እግዚአብሔር ዕቅድ አለው ። የሐሰት ምስክርና የሸፍጥ ዳኛ ወህኒ ቢጥሉን እንኳ ያለነው በጌታ እይታ ውስጥ ነው ።

የማንወደደውን እኛን ጌታ ከወደደን፣ የሚወደደውን ጌታ መውደድ  እግዚአብሔርን ባንፈራ ፣ ሰውን አፍረን እንኳ ልናደርገው የሚገባ ነው ። አላስወጣ ያለን የችግር ዘብ ካወቅንበት የመማሪያ ደብተራችን ነው ።

 ከእስራታችን እስራታቸው ይብሳልና ስለራሳችን ሳይሆን ስለሌሎች እንጸልይ ። እኛስ የይሉኝታ እስረኞች ነን? አንዳንዶቻችን እንደ ዘመኑ ለመዝፈን ወረት እስረኛ አድርጎናል ። ሳይጠሩን አቤት ፣ ሳይልኩን ወዴት እያልን ትዝብት ላይ ወድቀናል ። ሰውየው እንደ ተናገረው 

 

በስምንተኛው ሺህ ያገኘሁት ጥቅም ፣

 ሰማሁ አልሰማሁም አየሁ አላየሁም ።

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ነሐሴ 8 ቀን 2013 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም