የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

በጥቂቱ ዕድሜ

 
“ማንም በዕድሜው ብዛት አያስጠራም ስሙን ፣
በጥቂቱም ዕድሜው ይሠራል ሐውልቱን ።”
 
               ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ
 
ዕድሜ ሲያንስም ያሳዝናል ፣ ሲበዛም ይታክታል ። በለጋነታቸው የተቆረጡትን ፣ ዕድሜአቸው በዝቶ የጃጁትን ስናስብ ነቢዩ ሙሴ፡- “የዘመኖቻችንም ዕድሜ ሰባ ዓመት ፥ ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው” ያለውን እናስታውሳለን  ። መዝ. 89 ፡ 10 ። ከዚህ በፊት የማናውቀውን ዓለም በልደት አወቅነው ፣ ከዚህ በኋላ ላንመጣ በሞት ተሰናብተነው እንሄዳለን ። ሰባና ሰማንያ ዓመት ጥቂት ቢሆንም ሰውን ያደክመዋል ። ድካሙ ዕቃ ተሸክሞ ሳይሆን ራስን ፣ ፍላጎትን ፣ ሰውን ፣ ኑሮን ፣ አገርን ፣ ግዳጅን ተሸክሞ ነው ። ብዙ ዕድሜ ማግኘት ብዙ የመሥራት ዋስትና አይደለም ። ጥቂት ዕድሜም የሥራ እንቅፋት አይደለም ። ራስን ታሪክን ፣ አገርን ፣ ሕዝብን ለመለወጥ የሚያስፈልገው ትልቅ ዕድሜ ሳይሆን ትልቅ ልብ ነው ። አቤል ለእግዚአብሔር የተመረጠ መሥዋዕት ያቀረበው በወጣትነቱ ነው ። ቃየንም ገዳይ የሆነው በወጣትነቱ ነው ። መክሊት ለሁለት ሰዎች ቢሰጥ አንዱ ይመጸውትበታል ፣ ሌላው ግፍ ይሠራበታል ። መክሊቱ በራሱ ክፉና ደግ አይደለም ። ወጣትነትም እንደ መክሊት ነው ። ደግነትና ክፋት ግን ምርጫ ነው ። በሽምግልናው የሚያመነዝር አለና ወጣት ስለሆንሁ ፍላጎቴን መከልከል የለብኝም ማለት አይገባም ። ኃጢአትን የሚያስጥለን ዕድሜ ሳይሆን ፍቅረ እግዚአብሔር ነው ። ከሰው ልጆች የመጀመሪያው ሰማዕት ወጣቱ አቤል ነው ። በቤተ ክርስቲያን ጉዞም ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ ነው ። ዋናው ብዙ ዘመን መቆየታችን ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መኖራችን ነው ። ለአንዳንድ ሰው መኖር ያመነውን ለመካድ ሲሆንበት በሊቃነ ካህናቱ በሐናና በቀያፋ እናያለን ፣ መኖር በረከት ሲሆንም በፈያታዊ ዘየማን/በቀኙ ወንበዴ እናስተውላለን ። 
 
ስም ከመቃብር በላይ ይውላል ። ሰው ኖሮ ቢያደንቁት ብዙ ይሠራል ። አዝኖና ረግሞም አይሞትም ። ስሙ ቢጠራ የሚያምረው ግን ከሞት በኋላ ነው ። ሞት የዚህ ዓለም ኑሮ መጨረሻ ብቻ ሳይሆን ያ ሰው ከዚህ በኋላ የሠራውን ያበላሻል ተብሎ አይሰጋም ። የቆመ ሰው ግን የራሱን ሥራ ራሱ ሊያፈርሰው ይችላልና ኖሮ ያልጨረሰን ማመስገን ከባድ ነው ። በፍቅር ጀምረው በጥላቻ ፣ በሰላም ጀምረው በሁከት የሚፈጽሙ ፣ እንዳማረባቸው ማለፍ ያቃታቸው ብዙ ወገኖች አሉ ። ስም ማስጠሪያ የሚሆን በጎ ነገር ፣ ከራስ ተርፎ ለአገር የሚሆን ደግነት ያስፈልጋል ። አንድ ነገርን ለአገር ማበርከት አለብኝ ብለው ከልጅነት ጀምሮ የሚያስቡ ሕዝቦች የሥልጣኔ ማማ ላይ ወጥተዋል ። ሰው ያደረገውን የሚደግሙ ሳይሆኑ ያልተሠራውን የሚሠሩ ሕዝቦች አገራቸውን ከፍ አድርገዋል ። እኛ አዲስ ነገር ስለማይታየን ከምግብ ቤት አጠገብ ምግብ ቤት እንከፍታለን ። ሥራን መቀማማት እንጂ አዲስ ነገር አይታየንም ። 
 
ታምመን እንኳ የምንፈራው ሕመሙ የብቻችን ከሆነ ነው ። አገር ሁሉ ታሟል ስንባል እንበረታለን ። ሁሉ ከታመመ ግን አስታማሚ እንደሚጠፋ እንዘነጋለን ። ሁሉ አይቸገር የሚሰጥ እንዳይጠፋ ፣ ሁሉ አይከፋ የሚያጽናና እንዳይታጣ ። ተወለደ ሞተ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ሰዎች በጣም ያሳዝናሉ ። በዚህ ዓለም እንደ ቋጥኝ ተቀምጦ ማለፍን መጸየፍ ያስፈልጋል ። ጨው ይዘን ምድር አልጫ መሆኑ ፣ ብርሃን ይዘን ዓለም ጨለማ መሆኑ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀናል ። ይህን ዓለም ውብ የሚያደርገው ዘላለማዊ ውሳኔ የምናደርግበት በመሆኑ ነው ። በሚያልፈው ዕድሜ የማያልፍ ሥራ መሥራት ይቻላል ። ለሚያልፍ ቀንም የማያልፍ ንግግር እንናገራለን ። አንድ ቀን በዚህ ዓለም ላይ ዋጋ አለው ። አንድ ቀን ተወልደናል ፣ አንድ ቀን እንሞታለንና አንድ ቀን ብዙ ነው ። ሥራቸውን የፈጸሙ ሰዎች መኖርን ስለሚረኩ ብዙ ዕድሜን አይለምኑም ። ሥራቸውን የጨረሱም ፣ ለተፈጠሩበት ነገር የኖሩ በዕድሜአቸው አያፍሩም ። እግዚአብሔር የሰጣቸውን ዕድሜ ቀንሰው አይናገሩም ። ኖሮ አልኖርኩም ከማለት በላይ ክህደት የለም ። 
 
ወጣት ነኝ እንጂ ብዙ መሥራት እፈልግ ነበር አይባልም ። ዕድሜ ገፋ እንጂ ልሠራው የምመኘው ነገር አለ አይባልም ። ባለን ጥቂት ዘመን ለዘመን የሚተርፍ ፣ ለትውልድ የሚፈስስ ነገር መሥራት ይቻላል ። ይህችን ጀንበር ከተጣላነው ታርቀን ፣ የቀማነውን መልሰን ፣ የበደልናቸውን ክሰን አዲስ ማድረግ እንችላለን ። በዚህች ቀን የአርባ ዓመት ቂምን መሻር የምንችል ከሆነ አንድ ቀን ብዙ ነው ። ልንሠራው ለምናስበው ዓላማ የሚረዱ ትምህርቶችን ፣ የአካል ብቃትን ፣ መካሪዎችን ፣ ኅብረቶችን ፣ በጸሎት የሚያግዙንን ዛሬ መፈለግ ይቻላል ። 
 
ብዙ ስለመኖር ሳይሆን ብዙ ስለመሥራት እናስብ ። ብዙ ባንኖር የእኛ ጉዳይ ሳይሆን የአምላክ ፈቃድ ነው ። ብዙ ባንሠራ ግን የእኛ ስንፍና ነው ። ባለጠጋው ቢልጌት፡- “ድሀ ሆነህ መወለድህ የአንተ ጥፋት አይደለም ፣ ድሀ ሆነህ መሞትህ ግን ያንተ ጥፋት ነው” ብሏል ። በጥቂትዋ ዕድሜአችን ብዙ መሥራት እንችላለን ። እስጢፋኖስ ሰማዕት በ17 ዓመቱ ስሙ ተጠራ ፣ ማቱሳላ 965 ዓመት ኖሮ ይህን ሠራ አልተባለን ። 
 
እግዚአብሔር ያግዘን ።
 
የብርሃን ጠብታ 2 
 
 
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
 
 ነሐሴ 24 ቀን 2013 ዓ.ም
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ