October 3, 2021 by ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ባለህ ተደሰት
“የምንወደውን ማግኘት ካልቻልን ፣ የምናገኘውን እንውደድ ።” /ስፓኒሾች/
በዚህ ዓለም ላይ ትልቁ ፍልስፍና ፣ ትልቁ ጥበብ ፣ ትልቁ እምነት “እንደ ፈቃድህ” ማለት ነው ። በእግዚአብሔር ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥተናል ፣ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከዚህ ዓለም እንሄዳለን ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ገዥ ነው ። ፈቃድህ ይሁን ባንልም ፈቃዱ ይሆናል ። ፈቃዱ ይሁን በማለት ግን ሕይወት ጥያቄ ሳይሆን መልስ እንድትሆን ያደርጋል ። ትልቅ ፍልስፍና ራስን መጣል አይደለም ፣ ራስን መጣል ስንፍና ነው ። ፈላስፎች ከምድር ጀምረው በምድር ይጨርሳሉ ። ያለ ክርስቶስም ለዚህ ዓለም ስለሚሞቱ ትንሣኤ የላቸውም ። ዓለም ከንቱ ናት ቢሉም ብርቱ በሆነው በክርስቶስ ግን አልቀየሩአትም ። ትልቅ ፍልስፍና የሕይወቴን መግቢያና መውጫ ለያዘው እግዚአብሔር መንገድ መልቀቅ ነው ። ያለ ፈቃዴ መጥቼ ያለ ፈቃዴ በምሞትበት ዓለም ላይ ፈቃድህ ይሁን ማለት ምቹ ትራስ እንጂ የድንጋይ መደገፊያ አይደለም ። ትልቅ ጥበብም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅና ማክበር ነው ። ጥበብ እውቀትን የምንኖርበት ተግባራዊነት ፣ እሾሁን ሳይሆን ጽጌረዳውን የምናይበት መነጽር ነው ። “የማይጋፉትን ግንብ ዞረው ያልፉታል” እንዲሉ የማንጋፋውን ፈቃድ መቀበል ከመጋጨት ያድናል ። ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ሲጣላ ቀጥሎ ከሰው ጋር ሳይሆን ከራሱ ጋር ይጋጫል ። ከራሱ ጋር የተጋጨም ከሰው ጋር ሰላም የለውም ። ትልቁ እምነትም ተአምራት ማድረግ ሳይሆን “ፈቃድህ ይሁን” ብሎ ማረፍ ነው ። ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ የተሰጠን ነገር እንደሌለ ያለ ፈቃዱም የሚወሰድብን ነገር የለም ።
ይህች ዓለም ጉድለትዋ የጀመረው ዛሬ ሳይሆን አዳም በስደት ከመጣባት ጊዜ አንሥቶ ነው ። ለምለም እንድታበቅል የተፈጠረችው እሾህ አሜኬላ ሲበቅልባት ፣ እየደሙና እያደሙ መኖር ሲበዛባት ፣ አንዱ ላንዱ ዕረፍት መሆን ትቶ ሐፍረት ሲሆንባት ዓለም ከንቱ ነው እንላለን ። ዛሬ የጀመረ የመሰለን ክስተትም ኃጢአትም የለም ። የሚሆነው ሲሆን የነበረ ነው ። “ደንቆሮ የሰማ ቀን ያብዳል” እንዲሉ አላዋቂ ዛሬ ሲሰማ ያ ነገር ዛሬ የጀመረ ይመስለዋል ። ልቅሶ ላልሰማው ሰው ሁልጊዜ አዲስ ነው ። ሰውዬው ሚስቱ በሞተች ባመቱ የሰማ ሰው መጥቶ ሲያለቅስ “እኔ ረስቻታለሁ አንተ እስካሁን ታስባታለህ” አለ ይባላል ። ፍላጎታችንን በውል መረዳት በማንችልበት ዓለም ላይ ነን ። ትላንት የምንፈልገውና ዛሬ የምንፈልገው እርስ በርሱ የሚቃረን ነው ። በምኞት ስንሰጥ ኖረን ስናገኝ ስስታም ነን ። ሁሉም ነገር ቢሟላ ዓለም ዓለም መሆንዋ ይቀር ነበር ። “ብልህ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል” እንዲሉ የመጣውን መቀበል ያልመጣውን ለመጠበቅ ኃይል ነው ።
ብዙ ሰው ከፍላጎቱ ውጭ የተማረ ፣ የሚሠራ ፣ የሚኖር ሊሆን ይችላል ። የሚወደውን ነገር ያገኘ ጥቂት ነው ። ዕለት ዕለት የምንሸከመው መስቀል የማንወደውን ነገር መታገሥ ነው ። ደስታን ማሳደድ በበዛበት በዛሬው ዘመን ፣ ደስታ ላግኝ እንጂ በየትም በኩል ይምጣ በሚባልበት በእኛ ዓለም ፣ በቆሻሻ ውኃም ቢሆን እሳትን ማጥፋት ይቻላል ተብሎ ከእውነት ስሜት በሚከበርበት ምድር የሚወዱትን ማጣት ብርቱ ነገር ነው ። በዚህ ምድር ላይ የምንኖረው ግን የምንወደውን ስላገኘን ብቻ ሳይሆን በማንወደው ነገር ውስጥም ትዕግሥትን ለመለማመድ ነው ። እንደ እኛ አሳብ በዚህ አገር ፣ በዚህ ኑሮ ውስጥ አልነበርንም ። ከመረጥነው የተመረጠልን ይሻላልና ደስ ሊለን ይገባል ። የትም ቢሄዱ ሰማይና አፈር አንድ ነው ። የትም ቢሄዱ ምግብ የሚባል ነገር አናገኘም ፣ የምግብ ልዋጭ እንጂ ። እግዚአብሔር ብቻ እንግዳ ደስታ ነው ።
የምንወደው ወዳጃችን ፣ የመከራችን ጓድ ዛሬ በቅርበትም በሕይወትም ላይኖር ይችላል ። ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት ይሻላልና ያገኘነውን መውደድ ያስፈልጋል ። ሰው የሚኖረው ወዳጁ ያለበት ሳይሆን እንጀራው ያለበት ነው ። እየተዋደድን ከብዙ ወዳጆቻችን ጋር በእንጀራና በሞት ምክንያት ተለያይተናል ። ዛሬ ያሉት ወዳጆቻችን እንደ ቀድሞዎቹ ላይሆኑልን ይችላሉ ። ፍቅር እየቀነሰ ባለበት ዘመን ባለመጥፋቱ ማመስገን ይገባናል ። ከመልካምና ከክፉ ማነጻጸር በድሎት ዘመን ነው ። በክፉ ዘመን ከክፉ የተሻለው ክፉ ይመረጣል ።
የምንወደውን ትምህርት እየተማርን ላይሆን ይችላል ። ሰው ግን የሚኖረው በትምህርቱ ሳይሆን እግዚአብሔር በሚሰጠው ዕድል ነውና መከፋትና ማዘን አይገባም ። የትምህርት አንካሳ የለውምና ሁሉን መማር መልካም ነው ። በምንወደው ሥራ ላይ ላንሆን እንችላለን ፣ የምንወደው ጋ ለመድረስ ያገኘነውን መውደድ መሰላል ነው ።
የምንወደውን ማግኘት አለመቻላችን የሚያናድድ ሳይሆን ሰው መሆናችንን የሚያስረግጥ ነው ። ሰው ማለት አቅሙ የተወሰነ ፍጡር ነውና ። እኛ የምንወደው ባይገኝም እግዚአብሔር ይሁን ያለው ግን አልቀረም ። በገጠመን ዕድል ሳይሆን በመረጥነው ክፉ እንጠየቃለን ። እነዚያ ነገሮች ባይሆኑ መልካም ነበር ። ፈቃዳችን ሳይሆን በሆኑት ነገሮች ግን ጸጸት ሊሰማን አይገባም ። ከንቱ ጸጸት ተመጻቂነት ነውና ።
የዛሬ አለመቻል የነገ መቻል ነው ። አለመቻልን እንደ መቻል ስንቀበለው የምንችልበት ቀን ይመጣል ። ትንሣኤ ያለው ትንሣኤ ውስጥ ሳይሆን ውድቀት ውስጥ ነው ። በጠለቀችው ፀሐይ ሳይሆን በወጡት ጨረቃና በፈኩት ከዋክብት አመስግን ። ጨለማ ባይመጣ ከዋክብት አይታዩም ነበር ፣ ክፉ ቀኖችም ሰዎችን ያሳውቁሃል ።
በእጃችን ያለው ትንሽ ነገር ፣ የማንወደው ቢሆንም ደስ ይበለን ። የምንወደው እየቀረበ ይመጣል ። ምስጋና ጨለማን ብርሃን ፣ መንፈሳዊ ደስታም ጉብኝትን ያመጣል ። ባንወደውም ወደ ሞት የምንጓዝ ነንና የምወደው ቀረብኝ ብለን መከፋት አይገባንም ። የምንወደውን ብናገኝም ሞት አይቀርም ። በሥላሴ ማመን ግን ከሲኦል ሞት ያድናል ። የምትወዱትን ስላላገኛችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ።
የብርሃን ጠብታ 11
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም.