መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ባለሙያው አብ

የትምህርቱ ርዕስ | ባለሙያው አብ

አብ ባለሙያ ነው ድግስ ያውቅበታል ፣
አንድ በግ ሠውቶ ዓለም ጠግቦበታል ።

“በቦታው ማንም የለም ፣ ያለ ቦታው ሁሉም አለ” ይባላል ። በሰለጠነው ምድር በአገር ንብረት የተማሩ ፣ ንጉሡ የደከሙላቸው ተማሪዎች የእጅ ሙያን ፣ የከተማ ሕንፀትን ፣ የእርሻ ዕድገትን ተምረው አልመጡም ። ከአገራቸው ጋር እንዲላኮሱ ፣ መንግሥታቸውን እንዲከስሱ ወሬ ነክ ፖለቲካ ተምረው በአብዛኛው መጥተዋል ። በዚህ ምክንያት ሰላም አጥተው ሰላም ሲያሳጡ ፣ ገራፊውን እንግረፍ ብለው ተጨማሪ ጅራፍ ለሕዝባቸው እያመጡ እዚህ ደርሰናል ። ባልተማሩት የተጠበቀች አገር በተማሩት ፈርሳለች ። የሰው ቄራ እስክትሆን ፣ ለማየት ሲያጓጉ ወጣቶቿን ታንቃለች ። ሁለተኛው ችግራችን በቦታው ላይ ማንም አለመኖሩ ነው ። ቄሱ ፖለቲከኛ ፣ ፖለቲከኛው ቄስ ሁኖ ፣ ባለመስቀሉ ባለመድፍ ፣ ባለመድፉ ባለመስቀል ሁኖ ይታያል ። ጉዳይ ፈጻሚው በቢሮው የለም ፣ አጽናኙም በደብሩ አይገኝም ። ባልም ራስ መሆኑን አቁሟል ፣ ቀጤማ የሆነ መቆም ያቃተው ወንድ በየቤቱ ሞልቷል ። ሚስትም ቤቱን ጥላ ወጥታለች ። ልጆች ወላጆቻቸውን ያዝዛሉ ፣ ያስፈራራሉ ፤ ወላጆችም የልጅ ጩሎ ሁነው አንድ ነገር ቢሆንብኝ እያሉ በመበርገግ ይኖራሉ ። ደካማ እንዳይጠቃ ለመጠበቅ የተቋቋመው አካል ደካማ ያጠቃል ፣ መሣሪያውን ማስፈራሪያ ያደርገዋል ። ሰባኪው ፖለቲካ ያወራል ፣ ሽማግሌዎች የመኳል የመዳር አሳብ ላይ ከገቡ ሰንብተዋል ፣ ዓለም ያመለጣቸው መስሏቸው የማታ ሙሽራ ሁነዋል ።

ያለቦታው ብዙ ሰው አለ ። ነገሮችን ከማቅለል ይልቅ ውስብስብ የሚያደርገው ያለ ቦታው የተቀመጠ ፣ ባወሳሰበው ነገር በልቶ ለመሄድ የተዘጋጀ ነው ። ልክፈልህ ብለውት የሚቀበል ባለሙያ የለም ። ሠርቶ ከሚኖር ሰርቆና አውርቶ መኖር የአገሬ ልጅ ደስታው ሁኗል ። ለአገር የሚገባውን ገቢ በሥርዓት የሚቀበል የለም ፣ እኔ ልቀንስልህ ይህን ያህል ክፈል የሚል ብዙ ነው ። ለመቶ ብር ጉዳይ ሁለት መቶ ብር ጉቦ ይከፈላል ። ሐኪሙ መሐንዲስ ካልሆንሁ ሲል ፣ ቀያሹ ያክማል ። በቦታው ማንም የለም ፣ ያለ ቦታው ግን ሁሉም አለ ። እርሻ ተምሮ ፒያሣ የሚውል ፣ ስለ ማዕድን አጥንቶ ወሬ የሚቆፍር አያሌ ነው ። የወደቀ የኤሌክትሪክ ግንድ ሲተከል የሚሠሩት ሁለት ሰዎች ናቸው ፣ ታጅበው የሚመጡት በሰባት ሰው ነው ። እንደ ሠራ ሰው የዕረፍት ቀን የሚናፍቀው ብዙ ነው ። መሥሪያ ቤቱ ላይ ተኝቶ ፣ “ትኝት ብዬ የምውልበት ቀን ናፈቀኝ” የሚል የሠራ የሚመስለውን ቤት ይቍጠረው ። ጠላት ቢመጣም ይህችን አገር ከእኛ በላይ አይጠላትም ። አገር መውደድ ትርጉሙ መታወቅ አለበት ።

እግዚአብሔር ግን በቦታው ነው ። ጭልም ብሎብን እንደገና የሚበራልን እግዚአብሔር በቦታው መሆኑን ስናስብ ነው ። የሰማነው አንገዳግዶን ልንወድቅ ስንል የሚደግፈን እግዚአብሔር እንደ ሰው አለመሆኑን ባሰብን ጊዜ ነው ። ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ እናለቅሳለን ፣ እግዚአብሔርን ባሰብን ጊዜ ደስ ይለናል ። ሰላማዊት ቤተ ክርስቲያን በነገር ምድጃ ስትጣድ ፣ አገሬ ያሉአት ፍርሃት ስትሆን ፣ የሄደው ሳይመለስ ያለውም ሲኮበልል ሳይጠጡ ያሰክራል ፤ እግዚአብሔርን ባሰቡት ጊዜ ደስ ይላል ። ሁላችንም በቦታችን አይደለንም ። “ኤልያስ ሆይ ፥ በዚህ ምን ታደርጋለህ?” እንደ ተባለው ለእኛም ይባልልናል ። 1ነገሥ. 19 ፡ 9 ። ብዙዎቻችን ሰውን ከምናጽናናበት ፣ የመጣውን ወገን ከምናስተምርበት ማማ ወርደን በቀልድ አዙሪት ውስጥ ነን ። እጅግ ጨካኝ በመሆናችን ሕዝብ ወደ ዘላለም እሳት ሲሄድ አይደንቀንም ። ኪሳችንን ለመሙላት የስንቱን ልብ እናጎድለዋለን ። እግዚአብሔር ግን በቦታው ነው ። እኔ በቦታዬ አይደለሁም ፣ እንደ ተቀበልሁት መጠን አላመሰገንሁም ፣ እንደ ዋለልኝ ልክ ለአምላኬ አልኖርሁም ። በራሴም ሳፍር እግዚአብሔር ሁልጊዜ በቦታው ነው ብዬ እጽናናለሁ ። የሚጠብቀውን አካል ሲሰጋ ፣ ቆሞ ይቀብረኛል የሚለውን ካህን ሲሸሽ ወገን ያሳዝናል ። በሰው የጎደለ ግን በእግዚአብሔር ይሞላልና ደስ ይላል ።

እንግዳ የሚጠራ ፣ በግ አርዶ የሚጠብቅ ወዲህ ቸር ወዲህ ባለሙያ ነው ። እግዚአብሔር አብም ባሙያ ነውና አንድ በግ ሠውቶ ዓለሙን ለግብዣ ጠራ ። በጎች ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ነበር ፣ አንዱ በግ ግን ስለ ሰዎች ተሠዋ ። በጎች ሲሠዉ እንኳን ሕይወቴ ሞቴም ላንተ ነው የሚል መልእክት ነበረው ። አንዱ በግ ሲሠዋልን ሁሉን ሰጥቼ ራሴንም ሰጠኋችሁ የሚል መልእክት አለው ። ከአዳም እስከ ምጽአት ላለ የሰው ዘር አንድ በግ ደግሶ የሚጠራ ባለሙያ የለም ። ለዓለምና ለዘላለም የሚበቃው አንዱ በግ ክርስቶስ ግን ስለ ሁላችን ቤዛ ሁኗል ። እረዱልኝ የሚል ሳይሆን የታረደልን መድኅን ወደ እኛ መጥቷል ። አዎ አንድ ጊዜ የተፈጠረች ፀሐይ ፣ ይሁን በሚል ቃል የተሠራች ብርሃን እስካሁን ታበራለች ፤ አንድ ጊዜ የተሠዋው ሥጋ የለበሰው ቃልም ሲያድን ይኖራል ። ለእርሱ መሞት ከስንት አንዴ የሚገኝ የሰማዕትነት ክብር ነው ። ራስን ሕያው መሥዋዕት ማድረግ ፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር ልብና ጉልበትን ማቅረብ ደጋሹ አብን ፣ የተሠዋውን ወልድን ፣ ጣዕመ ሕይወት መንፈስ ቅዱስን ሲያስደስት ይኖራል ።

አብ ባለሙያ ነው ድግስ ያውቅበታል ፣
አንድ በግ ሠውቶ ዓለም ጠግቦበታል ።

እኔ አመሰግንሃለሁ ! እናንተስ ?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ