የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ባዶነት ሲሰማን 

ብርሃን አንድ ቢሆንም ጨለማዎች ግን ብዙ ናቸው ። ይህን ዓለም ለማበጀት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው የአዋጅ ድምፅ “ብርሃን ይሁን” የሚለው ትእዛዝ ነው ። “ብርሃን ይሁን” የሚለው አዋጅ የተሰማው በሦስት ምክንያት ነው፡- “ምድርም ባዶ ነበረች፥ አንዳችም አልነበረባትም ጨለማም በጥልቁ ላይ ነበረ የእግዚአብሔርም መንፈስ በውኃ ላይ ሰፍፎ ነበር” ይላል ። ዘፍ. 1፡2። ምድር ባዶ መሆንዋ ፣ ጨለማ በጥልቁ ላይ መሆኑ ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ነበር ። ምድር ታላቅ ባዶነት ገጥሟት ነበር ። ይህ ባዶነት ያለ እጽዋት ፣ ያለ ፍጥረታት ፣ ያለ እንስሳት ፣ ያለ አፍላጋት ፣ ያለ ሰዎች ባዶና መላጣ ፣ ጉበት መሳይ ነበረች ። ባዶነትዋ አንዳች ያልነበረው ዕራቁትነት ነበር ። የሚኖርባት ምንም ነገር ፣ የሚያኖርም ምንም ነገር አልነበረባትም ። ይህንን ባዶነት ለማራቅ የተሰማው ቃል “ብርሃን ይሁን” የሚል ነው ። ይህ ባዶነት እንደገና የብርሃን ጸጋ ያልነበረው ጽኑ ጨለማ የዋጠው ነበር ። “ብርሃን ይሁን” የሚለው አዋጅ ባዶነትን የሚሞላ ነው ። ብርሃን ባዶነትን ያጋልጣል እንጂ እንዴት ባዶነትን ይሞላል ብንል በቃል አዋጅ የተሰማው ብርሃን ባዶነትን የሚሞላ ነበር ። እግዚአብሔር የነቢብ ፍጥረታትን በብርሃን አዋጅ መግለጥ ጀመረ ።

ምድር ያኔ ስትፈጠር እንደ ነበረው ዛሬም የሚታይ በጎ ፣ የሚሰማ ብሥራት አጥታ ባዶነት ውስጥ ተቀምጣለች ። ዓይንና ጆሮን የሚይዙት ዘመናዊ መገናኛዎች የሚያሳዩንና የሚያሰሙን ክፉ ዜና ነው ። ጆሮ ደግ ነገርን ተርቧል ። ዓይንም ማረፊያ አጥቷል ። ስለ ደኖች ይወራል ፣ ሰው ግን ይጨፈጨፋል ። ብርሃን ክርስቶስ ነው ። ያለ እርሱ ምድር ምንም የሌላት ናት ። የእሳት እራት ለመሆንም የተዘጋጀች ናት ። ብርሃን ክርስቶስ ሥራውን ሲጀምር ባዶነታችንን ይሸፍናል እንጂ አያጋልጥም ። ሁሉ በእርሱ ሆነ የተባለለት ክርስቶስ በሥልጣን ቃሉ “ብርሃን ይሁን” እንዳለና ባዶነትን እንዳሸነፈ ዛሬም “ብርሃን ይሁን” ብሎ የነፍሳችንን ባዶነት ሊሞላው ይችላል ። ምድር ባዶነትዋን ለመሙላት ቃሉን ተቀብላለች ። ብርሃን በራሱ ስጦታ ነው ፣ የተሰጠንንም የምናየው በብርሃን ነው ።

ባዶነት ትልቅ ጩኸት ነው ። ባዶ ነገር ሁሉ ድምፅ ያስታጋባል ። ባዶነት ጸጥታ አይደለም ፣ ባዶነት ድምፅን ማጉላት ነው ። ባዶነት ያጠቃቸው ሰዎች ብዙ በመናገር ምንም አለማወቃቸውን ለመሸፈን ይሞክራሉ ። በምድር ላይ ታውቆ የሚነገር አለ ፣ እርሱም አዋቂ ያሰኛል ። ታውቆ የማይነገር አለ ፣ እርሱ ጨዋና ልከኛ ሰው ያሰኛል ። ታውቆ የሚነገረውን ያወቀም የሚሰማም እየጠፋ ነው ፣ ታውቆ የማይነገረውን የሚናገረውም የሚሰማውም እየፈላ ነው ። እውቀት ሲያንስ አፍ ሥራ ይበዛበታል ። ውኃ የሞላ እንስራ ጸጥ ይላል ፣ ጎዶሎው ይንቦጫቦጫል ። እሸት ፍሬ ያለው አገዳ ዘንበል ይላል ፣ ባዶ አገዳ ቀጥ ይላል ። በፍርድ ቤት ሰው ሰውን ሲገድል ያዩ ምስክሮች ይህን ስላወቁ በሊቅ መዝገብ አይጻፉም ። የመረጃ እውቀትም አዋቂ አያሰኝም ። ሰዎች የመረጃ እውቀትን ከሕይወት እውቀት መለየት አለባቸው ። ዜና ቶሎ ድርቆሽ የሚሆን ሲሆን ደግመው ቢያወሩት የሚሰለች የዕለት ድምፅ ነው ። ሕይወት ግን የዘመናት ርእስ ነው ። ምድር ባዶ ስለነበረች ታስተጋባ ነበር ። በመጀመሪያው የምድር ጉዞ የነበረው ሁነት በመጨረሻው የምድር ዘመን ይደገማል ። ሩጫ የጀመረበት ጋ ይጠናቀቃል ። ስለዚህም ባዶነት ፣ ማስተጋባት የመጨረሻ ዘመን ጠባይ ነው ። የመጨረሻው ዘመን ገዥ ሐሰተኛው መሢሕ የስድብ አፍ ተሰጠው ይላል ። ተሳዳቢነት ፣ ቅለት ፣ ሌላውን ማሳነስ የአውሬው ጠባይ ነው ። “ታላቅንም ነገርና ስድብን የሚናገርበት አፍ ተሰጠው” ይላል (ራእ. 13፡5)። ባዶነት የምድር ትልቅ ፈተና እየሆነ ስለመጣ አዋቂዎች ዱዳ አላዋቂዎች ደግሞ ተናጋሪ ሆነዋል ። ያልተጣሩ እውቀቶች በድፍረት ይነገራሉ ። ነጻነት ተብሎ የሚጠራው አንዱ አንዱን ማዋረድ ፣ ገዥዎችን መሳደብ ነው ።

በሰለጠነው ምድር የአእምሮ ሕመም የብዙዎች ፈተና ነው ። እጆች ሥራ ሲቀልላቸው አእምሮ ሥራ በዝቶበታል ። የባዶነት ስሜት የአእምሮ ሕመምን እያመጣ ነው ። ማኅበራዊ ኑሮ መፍረሱ የሰው ልጆችን ዕድሜ አጭር እያደረገው ነው ። ሰዎች ላለመነካካት ፣ ላለመቀራረብ የሚያደርጉት ጥረት ፣ የተፈጠረው ግለኝነት ከፍተኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜትን ወልዷል ። ለሌላው ዋጋ ላለመክፈል የሒሳብ ኑሮን እንደ ትልቅነት መቍጠር ደስተኛነትን አርቋል ። ምን አገባኝ ፣ እርሱም የራሱን ፣ እኔም የራሴን የሚለው የድንበር ኑሮ ሰዎች በባዶነት እንዲሰቃዩ አድርጓል ። ብዙዎች ሀብትን ሰብስበዋል ፣ ለእርካታ የሚሆን በጎነትን ግን አልሠሩም ። ደግነት የሌለበት ሀብት የባዶነት መነሻ ነው ። ብዙ ቢሊየነሮች ሁሉን ጨብጠው እርካታ ሲያጡ ወደ እርዳታ ፊታቸውን በማዞር እፎይ ማለት ይጀምራሉ ። በመስጠት ውስጥ ደስታ ተቀብሯል ። ድሆች ደስታ ፣ ባለጠጎች ገንዘብ አላቸው ። ገንዘባችንን ለድሆች ስንሰጥ ድሆች ደግሞ ደስታን ይለቁልናል ። ምነው የሰው ሁሉ አንገት አንድ በሆነልኝ እስኪሉ የመግደል ጥማት ያለባቸው ገዥዎች በባዶነት ይመታሉ ። ምድርን ባዶ ካደረጉ ባዶነት በግድ ይመጣል ። ዛሬ የሰው ልጆች ቍጥር አሳስቦናል የሚሉ ሰውን እንደ ጉድፍ እየጠረጉት ነው ። የወደፊት ትልቅ እቅድም ይኸው ሰውን እንደ ቆሻሻ ማጽዳት ነው ። ምድር ያለ ሰው ባዶ ናት ። ስለዚህም ለባዶነት ስቃይ ራሳችንን እያዘጋጀን ነው ። ብርሃን ሲበራልን ግን ሰው አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን ። አዎ ሰው ከነ ክፋቱ ጥሩ ነው ።

ብርሃን የበራላቸው ቃለ እግዚአብሔርን ዕለታዊ ምግባቸው ያደርጋሉ ፣ ከሰዎች ጋር መገናኘት ፣ ደግሶ ሰዎችን ማብላት ፣ ከወዳጆች ጋር መጫወት ፣ በጎ አድራጎት ማድረግ ይፈልጋሉ ። ይህን ብርሃን ያጡ ሰዎች ከቃለ እግዚአብሔር ዜናን ያስቀድማሉ ። የሚገርመው የመረጡትን መርጠው ጨነቀኝ ማለታቸው ነው ። የሚያስጨንቅ ነገር ሰምቶ መጨነቅ ግድ ነው ። ለአማኝ ዜናው ትንቢቱን የሚያስተውልበት ፣ የጸሎት ርእስ ነው ። በንፍገት የተሞሉ ፣ ብቻዬን ልብላ የሚሉ ሰዎች በባዶነትና በጨለማ ውስጥ የሚኖሩ ናቸው ። የክርስቶስ አዋጅ ዛሬም ብርሃን ይሁን የሚል ነው ። መብራት የገባለት አካባቢ ቶሎ ያድጋል ፣ ብርሃን ክርስቶስን ያገኘ አእምሮ ይለማል ።

ባዶነት ሲሰማን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑን ማመን ይገባል ። ትልቁ ባዶነት ያለ ሰው ሳይሆን ያለ እግዚአብሔር መሆን ነው ። የቀጠልነውን ኃጢአት ማቆም ፣ ያቆምነውን ጽድቅ መጀመር የባዶነት መድኃኒት ነው ። ማኅበራዊነት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ። የምንሰጠውም የምንቀበለውም አለ ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 6 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ