የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብልህ ሁኑ

“ማንም ብልህ ሁኖ አልተወለደም።” /ታንዛናውያን/

አፍሪካውያን በምድራቸው ላይ ለረጅም ዘመን የተቀመጡ ፣ ታሪካቸውን ፣ የትውልድ ሐረጋቸውን ፣ የመድኃኒት ጥበባቸውን ፣ የሥነ ቅርስና የሥነ ልሳን እውቀታቸውን በቃል እያስተላለፉ የኖሩ ሕዝቦች ናቸው ። አፍሪካ ሀብት ያለባት ምድር ብቻ ሳትሆን እውቀትም ያላቸው ሕዝቦች መቀመጫ ናት ። ሀብትዋ በዘረፋ ፣ ልጆችዋ በባርነት ለዘመናት ሲጋዙ ኑረዋል ። አፍሪካዊ አፍሪካዊነቱን እንዲረግመው ብዙ ተሠርቶበታል ። ቅኝ ገዥዎቹ ከእነርሱ የሚከፉ ጨካኝ አፍሪካውያንን እየተኩ በመውጣታቸው ፣ የአፍሪካ ዕንቈ ልጆችም የሞት ሰለባ መሆናቸው ፣ ያልተረጋጋው ሰላም አፍሪካን ዛሬም እየናጣት ይገኛል ። በዚሁ ከቀጠልን አንድ ቀን ለእናንተው ሰላም ስንል እንደ ገና በባርነት እንይዛችኋለን ብለው የሄዱት መምጣታቸው አይቀርም ። አፍሪካ ደሀ አይደለችም ፣ ልጆችዋም በባርነት ያን የመሰለ ሕንጻና መንገድ ከሠሩ አዋቂዎች ናቸው ። አፍሪካ ደንዋ ተመንጥሮ ከተወሰደ በኋላ የሰሐራ በረሃ ተብሎ ስም ወጣለት ። መሣሪያ ተሰጥቶ ልጆችዋ ከተጋደሉ በኋላ ሰላም የሌላቸው ያልሰለጡ ሕዝቦች ተብለው ተወገዙ ። አፍሪካ በታላቁ እስክንድር ስም በተሰየመችው እስክንድሪያ ታላቅ ቤተ መጻሕፍት የነበራት የመጽሐፍ ምድር ናት ። ይህም ከዛሬ 2300 ዓመታት በፊት ነው ። ብሉይ ኪዳን ለመጀመሪያ ጊዜ ከዕብራይስጥ ወደ ፅርዕ የተተረጎመው በምድረ አፍሪካ ነው ። ክርስትና ኢየሩሳሌም ተመሥርቶ ስድሳ ኪሎ ሜትር ሰማርያ ሳይደርስ በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካይነት ክርስትና ወደ አፍሪካ ገብቷል ። የሰሎሞንን ጥበብ ለማየት ኢየሩሳሌም ድረስ ሂዳ ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥትን ይዛ የመጣቸው አኵሱማዊት ሳባ የአፍሪካ ልጅ ናት ። የመጽሐፍ ቅዱስ ቀኖናዎች ፣ ታላላቅ ጉባዔዎች የተደረጉት ፣ ምንኵስናና ምናኔ የተጀመረው ፣ እነ ቅዱስ ቄርሎስ ፣ እነ ቅዱስ አትናቴዎስ ፣ እነ ቅዱስ እንጦንስ ፣ እነ ቅዱስ አውግስጢኖስ ፣ እነ ጠርጡሊያን የወጡት ከአፍሪካ ምድር ነው ። ሦስቱን ዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔ የመሩት አፍሪካውያን አባቶች ናቸው ። ጸሎተ ሃይማኖት የተረቀቀው በአፍሪካውያን አባቶች ነው ። አፍሪካ የብዙ ሥነ ቃል ፣ መድኃኒት ፣ ጥበብ መገኛ ናት ።

አፍሪካዊ የሆኑት ታንዛናውያን፡- “ማንም ብልህ ሁኖ አልተወለደም” ይላሉ ። የአፍሪካ ጥበቦች ፣ ሥነ ቃሎች ፣ ፍልስፍናዎች በቂ ዳሰሳ አላገኙም ። ብልህነት የተፈጥሮ ጸጋ ብቻ ሳይሆን በአብዛኛው የኑሮና የትምህርት ውጤት ነው ። ብልህነት መግቢያውን ብቻ ሳይሆን መውጫውን ማወቅም ነው ። መግቢያውን ብቻ ያወቀ መውጫውን ግን ያላገናዘበ አወዳደቁ የከፋ ነው ። ወደ ወጥመድ መግባት አለና መግባት ብቻ ውጤት አይደለም ። መግባቱን ችለው መውጫውን ያላወቁ ይጋደላሉ ። በፍቅር የጀመሩ በመጨራረስ ያከትማሉ ። ብልህነት ግን ሲገባ መውጫውንም ያስባል ። ኑሮ ከጉልበት ይልቅ በብልሃት ይመራል ። ብልህነት በሌላው ሰው አእምሮ ውስጥ ገብቶ የመጣበትን ክፉ አመጣጥ በደግ የሚለውጥና አደጋን የሚቀንስ ነው ። ብልህነት የነገርን አካሄድ ፣ የሰውን የተፈጥሮ ጠባይ ማወቅ ነውና ለዳኝነት በጣም አስፈላጊ ነው ። ብልህነት ከትርፉና ከኪሣራው ለክቶ የተሻለውን የሚመርጥ ነው ። ብልህነት ትላንትን ሳይረሳ ዛሬን ይኖራል ። ብልህነት ለነገ የሚተርፍ ነገር ዛሬ ይከውናል ። ብልህነት እሳት ሁነው ሲመጡ ውኃ ሁኖ ይጠብቃል ። ተደጋጋሚ ችግሮች ብሶተኛ እንዲያደርጉት አይፈቅድም ። በችግር ላይ ስንስቅ ችግሩ ያለቅሳል ፣ እኛ ስናለቅስ ችግራችን ይስቃል ። ብልህነት ከትላንቱ ችግር ምክሩን እየወሰደ ፣ ከመሞት መሰንበት ይሻላል እያለ ፣ ከክፉው ደጉን እያወጣ ፣ ኀዘን ኀዘንን ይወልዳል ላብርደው እያለ ቀኑን የሚያፈካ ነው ። ብልህነት ሞኝ ከሁሉ ይጣላል በማለት ጠብንና ጠላትን የሚቀንስ ፣ ጠላት ቢበዛበትም መውጫ መንገዱን የሚያስብ ፣ ይህም ሊሆን ይችላል በማለት በገጠመኙ የማይደነቅ ነው ። ብልህነት ሁልጊዜ ለመጀመር ዝግጁ የሆነ ፣ የዛሬ አለመቻል የሁልጊዜ አለመቻል አይደለም ብሎ የሚያምን ነው ። ብልህነት ለጠላቱ የውጊያውን ስልት የማያወራ ፣ በአፍ ሳይሆን በተግባር የሚረታ ፣ ተወደድሁ ብሎ መጠላት እንዳለ የማይረሳ ነው ።

ብልህነት ራሱን ከአገር ከሰው ለይቶ በድሀ መሐል ወርቅ የማያበዛ ፣ ተደመጥሁ ብሎ ንግግርን በኩንታል ጭኖ የማይመጣ ፣ ተጠላሁ ብሎ አገር ለቅቄ ልጥፋ የማይል ፣ የወሰዳቸው መንገድ መልሶ ያመጣቸዋል ብሎ በቅንነት የከዱትን የሚጠብቅ ፣ ለሁሉም ዋጋ ከፋይ እግዚአብሔር በዙፋኑ አለ ብሎ የሚያምን ነው ። ብልህነት ብልጥነት አይደለም ። ብልጠት የጦጣ ማኅበርተኞች ተግባር ፣ የሚያስንቅ አመል ነው ። ብልጥ ሁሉን አሞኛለሁ ብሎ ሲነሣ ሁሉም ብልጠቱን ያውቅበትና ሞኝ ይሆናል ።

ብልህ ሁኖ የተወለደ የለም ። ብልህ ለመሆን ልባምነትን ከእግዚአብሔር ቃል መያዝ ፣ የሽማግሌዎችን ምክር መስማት ፣ ዕለት በዕለት አንድ በጎ ነገር በማድረግ ማደግ ፣ ባልንጀራ አለማብዛት ፣ ንዴትን መጠየፍ ፣ ለውሳኔ አለመቸኮል ፣ ስሜትን መግዛት ፣ ታይታን መጥላት ፣ ሰወር ብሎ መኖር ፣ እውነተኛነትን እንጂ ገታራነትን ማራቅ ፣ ከመናገር ማዳመጥ ፣ የምክር መጻሕፍትን ማንበብ ፣ አንገት ደፍቶ የችግር ቀንን ማሳለፍ ፣ የሚቆጠበው ካለው ነገር እንጂ ከሌለ ነገር አይደለምና በታኝ አለመሆን ይገባል ።

ከሁሉ በላይ ራስ የሆነውን ክርስቶስን አለማስነካት ብልህነት ነው ። ራስ ከተቆረጠ ሕይወት የለም ። እባብ ራሱን አያስነካም ። “ስለዚህ እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ ።” ማቴ. 10፡16።

የብርሃን ጠብታ 29

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 29 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ