የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ ብርሃን ወጣላቸው”(ማቴ. 4÷16)

                                             ሐሙስ ሐምሌ 30 / 2007 ዓ.ም.
ብርሃን ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ለሰው ልጆች፣ ለእንስሳት፣ ለእጽዋት ሁሉ ብርሃን ከህልውና ጋር ተያያዥ ነው፡፡ ትልልቅ ግድቦች የሚገነቡት፣ የኒውክለር ተቋማት የሚታነጹት የመጀመሪያው የብርሃን ጥያቄን ለመመለስ ነው፡፡ ዘመናዊው ዓለም እንዲመልሰው ከሚፈለገው ጥያቄ አንዱ በቂ የኃይልና የብርሃን አቅርቦትን ማፍጠን ነው፡፡ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ይህች ዓለም የብርሃን ጥገኛ ሆናለች፡፡ በመቅረዝ፣ በኩራዝ የማይጠቁ ጨለማዎች በዓለም ላይ ተከስተዋል፡፡ ያማሩ ሕንጻዎች ቢገነቡ በመጨረሻ ብርሃን ካላገኙ ዋጋቸው የወደቀ ነው፡፡ ስለዚህ ለውድ ነገሮች እንኳ ዋጋ የሚሆናቸው የኤሌክትሪክ ብርሃን ማግኘት ነው፡፡ የብርሃን መገኛው ኃይል ነው፡፡ ኃይል በሌለበት ብርሃን ሊኖር አይችልም፡፡
በዚህ ዓለም ላይ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ብርሃናት አሉ፡፡ የተፈጥሮ ብርሃናት የማይከፈልባቸው ሲሆኑ ሰው ሠራሽ ብርሃናት ግን ብዙ ክፍያ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ በአሁን ዘመን ያሉ ነገሥታት እያንዳንዱን ሰው ቢያንስ የአንድ አምፑል ባለቤት ማድረግ እንደ ሰብአዊ መብት፣ እንደ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እያዩት በመሆኑ ደስ ይላል፡፡ ብርሃን ማግኘት ከሰብአዊ ጥያቄና መብት አንዱ ተደርጎ መታሰቡ ይደንቃል፡፡

ብርሃን የተለያዩ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ብርሃን የዘመን መስፈሪያ ነው፡፡ ዘመን የሚቆጠረው በፀሐይና በጨረቃ ዑደት ነው፡፡ ያለ ብርሃን ዘመን ሊቆጠር፣ ታሪክ ሊነገር አይችልም (ዘፍ. 1÷14)፡፡ ብርሃን ለተሟላ አካላዊ ዕድገት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕጻናት ፀሐይ መሞቅ አለባቸው፣ እስረኞች የፀሐይ ብርሃን ማግኘታቸው አንዱ የሰብአዊ አያያዝ መለኪያ ነው፡፡ ዕጽዋት ያለ ፀሐይ ብርሃን የተሟላ ዕድገት አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ዕጽዋት የፀሐይ ብርሃን ወዳለበት ይዞራል፡፡ በቂ የፀሐይ ብርሃን በማይገኝባቸው በረዷማ አገሮች ላይ ከፀሐይ ብርሃን የሚገኘውን ጥቅም የሚተካ ኪኒን መዋጥ ግዴታቸው ነው፡፡ አሊያ የተስተካከለና የጠነከረ አጥንት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ዓይን የራሷ ብርሃን የላትም፣ ይህች ዓይናችንም የፀሐይ ብርሃን ካላገኘች ልትጨልም ትችላለች፡፡ ብዙ እስረኞች የፀሐይ ብርሃን በሌለበት ስፍራ በመታሠር ዕውር እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ብርሃን ሥራ ለመሥራት ወሳኝ ነው፡፡ ምንም ታላላቅ ዕቅዶች ቢኖሩን ፀሐይና ጨረቃ ከጨለሙ ልናከናውነው አንችልም፡፡ ራሳችንን እንኳ የምናየው በብርሃን ነው፡፡ ብርሃን ደስታ ነው፧ ክረምቱ አልፎ በጋው ሲመጣ የታመሙት እንኳ ከአሁን በኋላስ አልሞትም ይላሉ፡፡ በብርሃን ውስጥ የሕይወት ተስፋ አለ ማለት ነው፡፡

 
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ውድ በመሆኑ በነጻ የሰጠን ስጦታ ብርሃን ነው፡፡ የፀሐይ ብርሃን ቢከፈልበት ኖሮ እንኳን ድሆች ባለጠጎችም በዕዳ ተይዘው ወኅኒ  በወረዱ ነበር፡፡ የፀሐይ ብርሃን ለሥራ፣ የጨረቃ ብርሃን ለዕረፍት ተዘጋጅተዋል፡፡ ፀሐይ ባትጠልቅ ማን ያርፍ ነበር፣ ፀሐይ ባትወጣ ማን ይሠራ ነበር; ቀኑ በሚረዝምበት ወቅት በአንዳንድ አገሮች ላይ ከሌሊቱ አራት ሰዓት ወጣቶች ኳስ ይጫወታሉ እንጂ ወደ ቤታቸው አይገቡም፡፡ ቀኑ በሚረዝምበት ከቀኑ እስከ ስድስት ሰዓት  ጨለማ በሚሆንበት ወቅት ደግሞ ብዙዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ ብርሃን ለዕረፍትና ለተስፋ መዋቀሩን እንረዳለን፡፡ ተፈጥሮኣዊው ብርሃን እንኳ ለመኖር ተስፋ ይሰጣል።
ይህ ዓለም ሲፈጠር የተሰማው የመጀመሪያው አዋጅ፡- “ብርሃን ይሁን” የሚል ነው (ዘፍ. 1÷3)፡፡ ጨለማ መንግሥት ነው፡፡ የጨለማው መንግሥት የሚሻረው በብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ ብርሃን የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫ፣ የእግዚአብሔርም የመጀመሪያ አዋጅ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ዓለም  ሲፈጥር ሥራውን የጀመረው “ብርሃን ይሁን” በማለት እንደሆነ ሁሉ በእያንዳንዳችን ሕይወትም ሥራውን ሲጀምር “ብርሃን ይሁን” በማለት ነው/2ቆሮ. 4፡6/፡፡ ብርሃን ካልበራልን፣ የጽድቅ ፀሐይ በሕይወታችን ካልወጣ የእግዚአብሔር ሰው መሆን የእግዚአብሔርን ሥራም መሥራት አይቻልም፡፡ ብርሃን ቀዳሚ ነገር ነው፡፡
ብርሃን መንፈሳዊ ትርጓሜ አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የገለጠባቸው ሰባት “እኔ ነኝ” የሚሉ መገለጫዎች አሉ፡፡ ከሰባቱ መገለጫዎች አንዱ፡- “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” የሚል ነው (ዮሐ. 8÷12)፡፡ ጌታችን እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ ሲል የሰው ልጆች ብርሃን ነኝ ማለቱ ነው፡፡ እኔ ብርሃን ነኝ ሲልም ፀሐይና ጨረቃን እተካለሁ ማለቱ ሳይሆን የሕይወት ብርሃንነቱን እየገለጠ ነው፡፡ ፀሐይና ጨረቃ ለሥጋዊው ኑሮ ሲያበሩ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የመንፈስ መብራት ነው፡፡ ፀሐይና ጨረቃ የተፈጠሩ ብርሃናት ሲሆኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ፈጣሪ ብርሃን ነው፡፡
ብርሃን የዕለት፣ የወር፣ የሳምንት፣ የዘመንና የአዝማናት መቁጠሪያ መነሻ ነው፡፡ እንዲሁም መኖር የምንጀምረው ክርስቶስን ታላቁን ብርሃን ካገኘንበት ጊዜ አንሥቶ ነው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ የማያምነው ዓለም እንኳ ዘመን የሚቆጥረው ከክርስቶስ ልደት በኋላ እያለ ነው፡፡ ለምን? ስንል ያለ ክርስቶስ የኖረበትን ዘመን እንደባከነ ዘመን በመቁጠር ነው፡፡ የእውነተኛው ታሪክ መነሻ ክርስቶስ ነው፡፡ ያለ ክርስቶስ ያሳለፍነው ዘመን የምናፍርበት ከዕድሜአችን ስፍር ውስጥ ገብቶ ሊቆጠር የማይገባው ነው፡፡
ብርሃን ለተሟላ አካላዊ ዕድገት አስፈላጊ ነው፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ለተሟላ ሕይወት፣ ለተሟላ አስተሳሰብ፣ ለተሟላ የሥልጣኔ ጉዞ፣ ለተሟላ ሰብአዊ መብት፣ ለተሟላ የሀብት ክፍፍል፣ ለተሟላ ዕውቀት፣ ለተሟላ ፍልስፍና፣ ለተሟላ በጎ አድራጎት አስፈላጊ ነው፡፡ ክርስቶስ የሌለበት ማንኛውም በጎ ነገር በድን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሕይወት ምንጭ ነው፡፡
ብዙ ዓመት የታሠሩ እስረኞች ከታሠሩበት ዓመታት በላይ የፀሐይ ብርሃን ያላገኙበትን ሦስት ወር አጥብቀው ይናገራሉ፡፡ ብርሃንን መነጠቅ ትልቅ እስራት ነው፡፡ እንዲሁም ከሕመማችን፣ ከእስራታችን፣ ከድህነታችን፣ ከኢኮኖሚ ውድቀታችን፣ ወዳጆቻችንን በሞት ከማጣታችን በላይ የሚከብደው ክርስቶስን አለማግኘት ነው። ጉዳት ሁሉ በክርስቶስ ይካሳል፡፡ ክርስቶስን የከሰረ ግን በየትኛው ስኬት ይካሳል;
ዕጽዋት እንኳ ወደ ብርሃን ሳያቀኑ መኖር አይችሉም፡፡ ክርስቶስም የበረከት ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ሰዎች ወደ እርሱ ሳይመለሱ መኖር አይችሉም፡፡ ብርሃን የሚኮራበት አማራጭ አይደለም፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ አማራጭ ሳይሆን ብቸኛው ምርጫ ነው፡፡
ያለ ብርሃን ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ተፈጥሮ እንኳ የተፈጠረው ከብርሃን አዋጅ በኋላ ነው፡፡ እንዲሁም የክርስቶስ የክብሩ ብርሃን ካልበራልን መሠራትም ሆነ መሥራት አይቻለንም፡፡ ብርሃን ይሠራል፣ ብርሃን ያሠራል፡፡ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ዕቅዶች ሁሉ የብርሃንን አጋዥነት ይፈልጋሉ፡፡ ብርሃን ባይኖር አምሮ መውጣት አይኖርም፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ የዕቅዶቻችን ዖሜጋ (ፍጻሜ)፣ የኑሮአችንም ውበት ነው፡፡ ክርስቶስ ከሌለበት ዕቅድ ሁሉ ከንቱ ቢፈጸምም እርካታው ትንሽ ነው፡፡ ብርሃን መገናኛ ነው፡፡ ብርሃን ሲወጣ የተለያዩ ይገናኛሉ፡፡ እንዲሁም ብርሃናዊው ክርስቶስ ከዘር፣ ከቋንቋ፣ ከነገድ፣ ከወገን እየዋጀ አገናኝቶናል/ራእ. 5፡9-10/፡፡ በየትኛውም የኑሮ ምርጫ የማንገናኝ ሰዎች የተገናኘነው በክርስቶስ የመስቀሉ ጥላ ነው፡፡ ዛሬም ተለያይተው የሚኖሩ የክርስቶስ ፍቅር ስላልገባቸው ነው፡፡ ብርሃኑ ሲበራላቸው ወደ አንድነት መድረክ ይሰበሰባሉ፡፡ ጨለማ መጋረጃ፣ ብርሃን ድልድይ ነውና፡፡ ሕዝብና አሕዛብን ያገናኘው ድልድይ፣ ሰማይና ምድር የታረቁበት መሰላል ክርስቶስ ነው።
ብርሃን የሞትን ፍርሃት የሚንድ ተስፋ ነው፡፡ በሽታው እንኳ ሌሊቱን ሲጠነክር ብርሃን ሲመጣ ግርማው ይገፈፋል፡፡ እንዲሁም ክርስቶስ ተስፋ ሕይወት ነው፡፡ በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ አይሞቱም፡፡ ክርስቶስ የሕይወት ብርሃን ነውና፡፡
ብርሃን ውድ ቢሆንም በነጻ ተሰጥቶናል፡፡ እንዲሁም ውዱ ክርስቶስን በነጻ አግኝተነዋል/ዮሐ. 3፡16/፡፡ በነጻ የተሰጠን ርካሽ ስለሆነ ሳይሆን ዋጋ ስለማይገዛው ነው፡፡ ብርሃን ለዕረፍት፣ ለተስፋ ተበጅቷል፡፡ ክርስቶስም ዕረፍተ ሥጋ፣ ዕረፍተ ነፍስ ሊሆነን መጥቷል፡፡ እርሱን ስናገኝ የመኖር አምሮታችን ይጨምራል፡፡
                            “ብርሃን ወጣላቸው”
                                   ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ