የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ብርሃን ወጣላቸው”/ክፍል 2/

 ማክሰኞ ነሐሴ 5/2007 ዓ.ም.
 
ማቴዎስ ከሱባዔው በኋላ የጌታችንን እርምጃ ሲዘግብ፡- “ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ፡፡ ናዝሬትንም ትቶ በዛብሎንና በንፍታሌም አገር በባሕር አጠገብ ወደ አለችው ወደ ቅፍርናሆም መጥቶ ኖረ፡፡ በነቢዩ በኢሳይያስ፡-
“የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር÷ የባሕር መንገድ÷ በዮርዳኖስ ማዶ÷ የአሕዛብ ገሊላ÷ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ÷ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሆነ” ይላል (ማቴ. 4÷12-16)፡፡
ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ያጠመቀውና መንገድ የጠረገለት ዮሐንስ በገዢዎች ተላልፎ እንደ ተሰጠ ሰማ፡፡ የወንጌል በሰማዕታት ደም ላይ የምታፈራ ሕያው ዘር ናት፡፡ ወንጌል እዚህ የደረሰችው በዋጋ ነው፣ ወደ ቀጣዩ ትውልድም የምታልፈው በዋጋ ነው፡፡ ሰማዕታት ሊሞቱ ይችላሉ፣ እውነት ግን አትሞትም፡፡ እውነተኞችን የገደሉ እንጂ እውነትን የገደሉ ጨካኞች የሉም። የነፋስን ዙረት፣ የእሳትን ላንቃ መያዝ ይችላል፣ እውነት ግን አትታሠርም፡፡
ሰዎችን ከኃጢአት እስራት ለማስፈታት ንስሐን ይሰብክ የነበረው ዮሐንስ በሥጋ ታሠረ፡፡ በነፍስ አስፈትቶ በሥጋ ቢታሠር ቀላል ነው፡፡ ከመታሠራችን በላይ ያሠሩን ሰዎች እስራት የበለጠ ነው፡፡ በሥጋ የሚያስሩን በነፍሳቸው የታሠሩ፣ ከምኲራብ የሚያባርሩን ገነት የተዘጋባቸው መሆናቸውን ብናውቅ ምንኛ በተደነቅን ነበር፡፡ በርግጥም አንድን ሰው ወደ ክርስቶስ ማምጣት ከሲኦል ማስመለጥ ነው፡፡ ታዲያ ከሲኦል ነፍስ ሲያመላልሱ ወላፈኑ አይንካኝ ማለት አይቻልም፡፡ ሰይጣንን ካደማነው በላይ አላደማንምና ደስ ሊለን ይገባል፡፡ እኛ እየበዘበዝነው እርሱ እየተበቀለ ነው፡፡ ሥጋችንን ለጊዜው ይጎስማል፣ ነፍሳችን ግን የክርስቶስ ናት፡፡ የጌታችንን ወደዚህ ዓለም መምጣት ስናስብ ብዙ ነገሮች ድቅን ይሉብናል፡፡ እርሱ እውነትን ሊመሰክርና እውነት የምታስከፍለውን ዋጋ ሁሉ ሊቀበል ወደ ዓለም መጥቷል፡፡ አገልጋዮቹን እየላከ ያስገድላል እንዳይሉት እርሱ ራሱ ሰማዕተ ጽድቅ (የእውነት ምስክር) ሆኖ ወደ ዓለም መጣ፡፡ ስለ እውነትም ሞተ፡፡
ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ አልተደናገረም፡፡ ዮሐንስ ሲያቆም እርሱ ይጀምራል፡፡ ፍጡር ሲደክመው የማይደክመው ጌታ ይቀጥላል፡፡ ዮሐንስ ሲያቆም ጌታችን አገልግሎቱን ቀጠለ፡፡ እኛ ስንታሠር እኛ ስንገደብ የማይታሠረው ጌታ፣ የማይገደበው ንጉሥ ይቀጥላል፡፡ እኛ ዐረፍተ ዘመን ሲገታን ዘላለማዊ አባት ሥራውን ይፈጽማል፡፡ ሥራው የእኛ አይደለም፣ ሥራው የእግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር በሞት እንኳ የሚያልፉ ልጆቹን ወደ ዕረፍታችሁ ግቡ ይላል እንጂ ሥራዬን ትታችሁ እንዴት መጣችሁ; አይልም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን በዘመናት ሁሉ ይቀጥላል፡፡ እኔ ባልፍ አገልግሎቱ ምን ይሆናል? እኔ ባልኖር ልጆቼ ምን ይሆናሉ? እንላለን፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው የዛሬን ድርሻ መወጣት ነው፡፡ እኛ ስናልፍ የማያልፈው ጌታ ለአገልግሎታችን፣ ለልጆቻችን ይኖርላቸዋል፡፡ እንደውም እግዚአብሔር በሙሉ ድርሻ ያን ቀን ይቆማል፡፡ ዛሬ ግን በሙሉነት እንዳያልፍ የእኛ አለማመንና ጭንቀት መንገዱን ዘግቶበታል፡፡ ዮሐንስ በገዢዎች ቢታሠር አትደንግጡ፤ የማይታሠረው የነገሥታት ንጉሥ ሥራውን ይቀጥላል፡፡


ማቴዎስ ሲዘግብ፡- “ኢየሱስም ዮሐንስ አልፎ እንደ ተሰጠ በሰማ ጊዜ ወደ ገሊላ ፈቀቅ ብሎ ሄደ” ብሏል (ማቴ. 4÷12)፡፡ ጌታችን ፈቀቅ ብሎ የሄደው ግዴለሽ ሆኖ ወይም ፈርቶ አይደለም፡፡ እርሱ ወደዚህ ዓለም የመጣው ሞትን ዓላማ አድርጎ ነው፡፡ ነገር ግን ያለጊዜው ላለመሞት ይጠነቀቅ ነበር፡፡ እንኳን ኑሮው ሞቱም በእግዚአብሔር ፈቃድና ጊዜ እንዲሆን ፈልጓል፡፡ ስለዚህ ሄሮድስ ገና በሕጻንነቱ ሲያሳድደው ወደ ግብጽ ሸሸ፣ ሰይጣን ራስህን ወርውር ቢለው አልታዘዝም፣ ዮሐንስ ሲያዝም ፈቀቅ አለ፡፡ ያለ ጊዜው ሰማዕትነት እንኳ ክብር የለውም፡፡ በግልፍተኝነት የሞቱ ሰማዕታት አይደሉም፡፡ በጊዜው ግን ውብ ነው፡፡
ጌታችን ፈቀቅ ያለው ወደ እስራኤል ሰሜናዊ ግዛት ወደ ገሊላ ነው፡፡ ገሊላ መንፈሳዊ ጨለማ የወረሰው ግዛት ነበር፡፡ ትልቁ ጨለማ፣ ጨለማውን እንደ ብርሃን ተቀብሎ መኖር፣ ካለመዱት መንፈስ ቅዱስ የለመዱት ሰይጣን ይሻላል የሚል የሞት ፍልስፍና ነው፡፡ ገሊላ በጨለማ ተውጣ ነበር፣ በጨለማ መሆኗንና ብርሃን እንደሚያስፈልጋት እንኳ አታውቅም ነበር፡፡ ጌታችን ወደሚፈልጉት ብቻ ሳይሆን እርሱ ወደሚያስፈልጋቸውም ይሄድ ነበር፡፡ የሚፈለገው ክርስቶስ በተቃራኒው ይፈልግ ነበር፡፡ እርሱ የሄደበት አካባቢ ቅፍርናሆም፣ የዛብሎንና የንፍታሌም ምድር፣ የባሕር መንገድ፣ የዮርዳኖስ ማዶ፣ የአሕዛብ ገሊላ ነበር፡፡ እነዚህ አገሮች በመንፈስ ከሞቱ ሰዎች የተነሣ የሞት ከተሞች ሆነው ነበር፡፡ በሰው ኃጢአት የከተማ ስም ይጎሳቆላል፣ በሰው ኃጢአት ከተማ ይደመሰሳል፡፡ ሰው ሲበድል ለሰው የሆነው ሁሉ ይጎዳል፡፡ የገሊላ አውራጃ በተለይ የተጠቀሱት ከተሞች በጨለማ የተቀመጡ፣ በሞት ጥላ የተሸማቀቁ ነበሩ፡፡ ክርስቶስ ወደ እነዚህ ከተሞች በሄደ ጊዜ “ብርሃን ወጣላቸው” ተባለ፡፡ ይህ አስቀድሞ በነቢዩ በኢሳይያስ የተነገረ ትንቢት ነው፡፡
“የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር፥ የባሕር መንገድ፥ በዮርዳኖስ ማዶ፥ የአሕዛብ ገሊላ፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፥ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው”(ማቴ. 4፥13-16፣ ኢሳ. 9፥1-2)፡፡
ጌታችን አገልግሎቱን የጀመረው ከቤተ መቅደስ ሳይሆን ከመንደሮች ነው፡፡ በቤተ መቅደስ ያሉት ሕንጻ የሚጠብቁ፣ ስለ ጣራ ማፍሰስ የሚጨነቁና ስለ ቅርስና ታሪክ የሚያለቅሱ፣ ስለ ፖለቲካው የሚቃትቱ ነበሩ፡፡ ጌታ ግን ራሱ ስለ ሠራው መቅደስ ስለ ሰው ልጅ ግድ የሚለው፣ ፍጻሜው ስለተበላሸበት፣ ዛሬን ማደር እያላቃተው የሚያውል ቃል ስለተራበው ወገን ያስብ ነበር፡፡ ሰው ከፈረሰ ሕንጻውን ማን ያመልክበታል; በዓይናችን የምናየው የሰው ልጅ ፈርሶና ወድቆ ለቅርስና ታሪክ ብዙ ንብረት ሲባክን ስናይ የዛሬውን ትውልድ የማያከብር አገልግሎት አሳዛኝ አገልግሎት ነው፡፡ ቤተ መቅደሱ ትክል ሆስፒታል ነበር፡፡ አገልጋዮችም የመቅደሱ ሐኪሞች ነበሩ፡፡ እዚያው ድረስ መጥቶ ለጠየቀ አገልግሎት የሚሰጡ፣ በክፍያ የሚያገለግሉ ነበሩ፡፡ ጌታችን ግን የበሽተኛ ያለ እያለ የሚፈልግ ተንቀሳቃሽ  ሐኪም ነበረ፡፡ በሽተኞቹ እስኪመጡ የማይጠብቅ ካሉበት ስፍራ፣ ከውድቀታቸው ድረስ በመሄድ ነፍስን የሚያድን ነበር፡፡ ወረርሽኝ በገባባቸው አካባቢዎች ሕዝቡን ሁሉ ወደ ሆስፒታል ማምጣት ስለማይቻል እዚያው ድረስ በመሄድ የሕክምና ቡድኑ ፈውስ ይናኛል፡፡ በመንፈሳዊ ረገድም አንዱ ካንዱ በማይሻል ሁኔታ ሁሉም ጠፍቶ ነበር፡፡ የጠፉ ግለሰቦች ሳይሆን የጠፉ ሕዝቦችና የታወኩ ከተሞች ነበሩ፡፡ ጌታችን የሄደው ወደ እነዚህ ስፍራዎች ነው፡፡
በየመንደሩ እየገባ ያስተምር ነበር፡፡ እርሱ በመቅደስ ያገለገለው እጅግ ጥቂት ቀን ነው፡፡ አድማጭ ባለበት ሁሉ ይናገር ነበር፡፡ አድማጭ ካለ ለስብከት አይመችም የሚባል ስፍራ አልነበረም፡፡ በመንደር፣ በገበያ፣ በልቅሶ ቤት፣ በሠርግ ስፍራ፣ በአርዮስፋጎስ አደባባይ፣ በትምህርት ቤቶች… ወንጌል ይሰበካል፡፡ በየሰው ቤት፣ በመንደር ወንጌል ሲሰበክ የሚቀፋቸው ወገኖች አሉ፡፡ ጌታ ግን እዚህ ቤት በሽተኛ አለ ወይ; እያለ አገልግሏል፡፡ ከጥንት የነበረው የጌታና የሐዋርያት የአበው ልማድ ይህ ነውና ሁሉን ስፍራ ወንጌል አደባባይ ልናደርገው ይገባል። ወንጌል በቦታ አትረክስም፣ ቦታዎች ግን በወንጌል ይቀደሳሉ። ብዙ አብያተ ጣኦታት አብያተ ክርስቲያናት እንደሆኑ ታሪክ ይነግረናል።
ናዝሬትን ትቶ
ጌታ ወደ ገሊላ መንደሮች ሲገባ ናዝሬትን ትቶ ነው፡፡ በዓለም የተጨነቁ ወገኖች አሉ፡፡ የተጨነቁት ወገኖች ግን ቀጥሎ ባለው ቁጥር ይከፈላሉ፡-
1.     የተጨነቁ ግን በክርስቶስ ከሆነ ማረፍን የማይፈልጉ
2.    የተጨነቁ ክርስቶስን አግኝተው ማረፍ የሚፈልጉ
3.    የተጨነቁ አሳራፊውን ክርስቶስን የማያውቁ ወገኖች አሉ፡፡
ስለዚህ በዓለም ላይ ያሉት ወገኖች ሁለት ሦስተኛው ዕረፍትን ቢያገኝ ማረፍ የሚፈልግ ነው፡፡ አንዱ እጅ ግን በጥባጭ ነው፡፡ በነፍሱ እልህ የያዘው፣ ከመድኃኒቱ ያጣላው ነው፡፡ በናዝሬት ይኖሩ የነበሩት የተጨነቁ ግን በክርስቶስ ከሆነ ማረፍን የማይፈልጉ ነበሩ፡፡ ናዝሬት የዓመፅ የዝሙት ከተማ ነበረች፡፡ ከዓመጽዋ በላይ የክርስቶስ ቅድስና የከበዳት ነበረች፡፡ ብዙ ጊዜ ክርስቶስን ገፍታዋለች፡፡ ለመግደልም ሞክራለች፡፡ ጌታ ናዝሬትን ትቶ ሄደ፡፡ የሃይማኖት ቀናያን የሚመስሉ ነገር ግን በብልግና የተሞሉ ሰዎች የነበሩባት ከተማ ስለነበረች በመጀመሪያ አገልግሎት ትልቅ ጉልበት ማባከን ተገቢ ስላልሆነ ናዝሬትን ትቶ ሄደ፡፡ “አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” እንዲሉ፡፡
የዛብሎንና የንፍታሌም አገር
ጌታችን ናዝሬትን ትቶ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም ምድር ሄዷል፡፡ ናዝሬትን የተወበት ምክንያት ናዝሬት ያደገባት ከተማ በመሆኗ ባደጉበት ከተማ ማገልገል ከባድ ስለሆነ ነው፡፡ ራሱ ጌታችን ነቢይ በገዛ አገሩ አይከበርም ብሏል፡፡ በአገራችንም ከአብሮ አደግ አትሰደድ ይባላል፡፡ ምክንያቱም አብሮ አደጐች እውነቱን ከመቀበል እናውቀው የለም ወይ; እውነት በከተማችን ስትገባ እኛን በየት አልፋ እርሱን ነካችው? የሚል አስተሳሰብ ያድርባቸዋል፡፡ ትንሽ ዕውቀት ያሰናክላል፡፡ አብሮ አደግን መልኩን እንጂ ልቡን አናውቀውም፡፡ ራእዩን ማየት አይሆንልንም፡፡ ነጻነታችን ከሌላ መንደር ባለ በባዕድ እንጂ በአብሮ አደጋችን እንዲሆንልን አንፈልግም፡፡ ስለዚህ ጌታችን ትንሽ ዕውቀታቸው መሰናክል እንዳይሆንባቸው ናዝሬትን ትቶ ሄደ፡፡ አብሮ አደጎች ከመስማት ማጣጣል፣ ከመቀበል ሌላውን ማሳደም ይወዳሉ፡፡ ትልቅ ሹመት ላይ ካሉት አንስቶ እስከ ሥር አገልጋዮች በአብሮ አደጎች መጠላትን አስተናግደዋል፡፡
ጌታችን ናዝሬትን የተወበት ሌላው ምክንያት ናዝሬት መልካም አይወጣባትም ተብላ ተስፋ እስኪቆረጥባት በዓመፀኛች የተሞላች ከተማ ነበረች፡፡ ጌታችን ናዝሬትን ትቶ ወደ ዛብሎንና ንፍታሌም ምድር የሄደው አገልግሎቱን ቀለል ካለው ለመጀመር ነው፡፡ አገልግሎት ከኃይለኞች ከተጀመረ ኃይለኞች ጋ ጉልበት ያልቅና ገራሞቹ ጋ ሳይደረስ ይቀራል፡፡ ገራሞቹን አገልግሎ ደቀ መዛሙርት ካተረፉ በኋላ ወደ ኃይለኞቹ ሲሄዱ ብርታት ይጨምራል፡፡
ጌታችን ናዝሬትን ትቶ ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም የሄደበት ሦስተኛው ምክንያት በናዝሬት ይታይ የበረው የሥነ ምግባር ችግር ነው፡፡ በዛብሎንና በንፍታሌም ግን የሥነ ልቡና ችግር አለ፡፡ ከሥነ ምግባር ችግር ለሥነ ልቡና ችግር ቅድሚያ መስጠቱ ነው፡፡ ምክንያቱም የሥነ ምግባር ካለባቸው ሰዎች የሥነ ልቡና ችግር ያለባቸው ሰዎች ሥቃያቸው ከፍ ያለ ነውና፡፡ የዛብሎንና የንፍታሌም ነዋሪዎች ራሳቸውን መቀበል ያቃታቸው መከረኞች ናቸው፡፡ የልብ አምላክ፣ የልብን ስቃይ ያውቃል፡፡
ወደ ዛብሎንና ወደ ንፍታሌም ምድር የሄደው የመጀመሪያው ትንቢትን ሊፈጽም ነው፡፡ ሁለተኛው የተጠቁ ወገን ስለነበሩ ሊታደጋቸው ነው፡፡
ዛብሎንና ንፍታሌም ሰሜናዊ የእስራኤል ግዛቶች ናቸው፡፡ ዛብሎንና ንፍታሌም የያዕቆብ ልጆች የነገድ አባቶች ናቸው፡፡ በስማቸውም የሚጠራ ነገደ ዛብሎንና ነገደ ንፍታሌም የሚባሉ ሁለት ነገዶች አሉ፡፡
ዛብሎን የያዕቆብ ዐሥረኛ ልጅ ነው፡፡ ዛብሎን ከልያ የተወለደ ነው፡፡ ልያ ባሏ ያዕቆብ ያልወደዳት አባቷ አታሎ የዳረለት፣ በጨለማ እንጂ በብርሃን የማትታይ የተጠቃች ሴት ናት፡፡ መጠቃቷን ግን እግዚአብሔር ዓይቶላታል። እግዚአብሔር የተገፉትን ባይቀበል ኖሮ ተገፊዎች ወድቀው በቀሩ ነበር፡፡ ሰው ሲገፋን የምናርፈው እግዚአብሔር ዕቅፍ ላይ ነው፡፡
ልያ ታላቅ ሳለች ያልተከበረች የተናቀችና እንደ ጉድፍ የተጣለች፣ በቀን ዋጋ የማታወጣ በጨለማ የምትሸጥ ነበረች፣፡ ፈላጊ ስለሌላት አባቷ ስለ እርሷ ያስብ ነበር፡፡ ራሔል መልከ መልካም ስለነበረች መኖር ትችላለች፡፡ ልያ ግን ባል ያጫት ዘንድ ተፈላጊ አልነበረችም፡፡ ነገር ግን መኖር የማይችሉ የሚመስሉ በእግዚአብሔር በጀት ይኖራሉ፡፡ እግዚአብሔር የእነዚህም አምላክ ነው፡፡ ስንቱን ብልህ እያደከመላቸው ሞኞች ይኖራሉ፡፡ ስንት ሞኞች እግዚአብሔር የብልህ አሽከር ቀጥሮላቸው ይታያል፡፡
ልያ አባቷ እንጂ ባሏ ያልወደዳት ሴት ነበረች፡፡ ባሏ ስለ እርሷ ዋጋ መክፈል፣ እርሷን ሚስቴ ብሎ መጥራት አይፈልግም ነበር፡፡ ግዱን ያዋዋጣት ሴት ነበረች፡፡ አዎ የቅርብ የተባለ፣ አካል የተባለ ላይወደን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ግን ይወደናል፡፡ በባል ብንጠላ እንኳ በእግዚአብሔር ከተወደድን ይበቃል፡፡ የዓለምን ጥላቻ ሁሉ የሚያስረሳ የእግዚአብሔር ፍቅር ነው፡፡
ዛብሎን ማለት የስሙ ትርጉም መኖሪያ ማለት ነው፡፡ ልያ ለልጇ ዛብሎን ብላ ሰየመችው፡፡ ያዕቆብ ዛብሎንን ይወደዋል፡፡ ዛብሎን እስካለ እኔ እኖራለሁ ብላ ልጇን መኖሪያ ብላ ሰየመችው፡፡ በያዕቆብ ግዛት ለመኖር ዛብሎን የመኖሪያ ፈቃዷ ነበር፡፡
ልያ ውበት የሌላት ሴት ነበረች፡፡ በመጨረሻ ስለ ፍሬዋ በግድ የተወደደች ሚስት ናት፡፡ ዕድሜዋም ከተወደደችው ራሔል በላይ ነው፡፡ ያልተወደዱት እየኖሩ፣ የተወደዱት ቶሎ ያልቃሉ፡፡
ዛብሎን የልያ ልጅ በመሆኑ በእርሷ ላይ ያረፈው በትርና የወደቀባት የሥነ ልቡና ጫና በግድ ያገኘዋል፡፡ ልጆች መልክን ብቻ ሳይሆን ስብራትንም ይወርሳሉና፡፡
ከልያ የተወለዱ የዛብሎን ወገኖች ምንም ብሠራ፣ ምንም ብማር ተቀባይነት የለኝም የሚሉ ናቸው፡፡ ቶሎ የማይወደዱ፣ የሚስብ ውጫዊ ቁመና የሌላቸው በመሆኑ ያላቸውን መልካም ነገር ተስፋ ይቆርጡበታል፡፡ ሌሎች ሳያገሏቸው ራሳቸውን ቀድመው ያገላሉ፡፡ በገጠጠው ጥርሳቸው ያማረውን ያንን ድምፃቸውን ያፍናሉ፤ በተጎረደው አፍንጫቸው ያን የተከማቸ ዕውቀታቸውን ይቀብራሉ፤ በሰለለው አካላቸው ያንን የማይገኘውን ፍልስፍናቸውን አፈር ያለብሱታል፡፡ ጥምጥማቸው ትንሽ፣ ትምህርታቸው ሙሉ የሆኑ፣ ማዕረጋቸው ጥቂት ድርሻቸው አያሌ የሆኑ ዛብሎኖች ዛሬም አሉ፡፡ ጌታችን የሄደው ወደ እነዚህ ወገኖች ነው፡፡ በእርግጥም እንዲህ ካለ ራስን ካሰሩበት እስር ቤት ነጻ የሚያወጣ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ዋጋ የለኝም ለሚሉ ዋጋ ሊሆናቸው ክርስቶስ መጥቷል፡፡ ዋጋችን ሚሊየን ወይም ቢሊየን አይደለም፡፡ ዋጋችን ክርስቶስ ነው፡፡
ዋጋ የለኝም ለምንል፣ ዋጋ የላችሁም ለተባልን ዋጋችን ክርስቶስ ነው፡፡ የሰው ዋጋ ይወድቃል፣ የትላንት ውድ ዛሬ ይረክሳል፡፡ የክርስቶስ ዋጋነት ግን እየጨመረ ይሄዳል፡፡
የዛብሎን ወገኖች ዛሬም አሉ፡፡ ስም የላቸውም ሥራ ግን አላቸው፡፡ መልክ የላቸውም ምግባር ግን አላቸው፡፡ የቅርብ ወገኖቻቸው እንኳ የጠሏቸው ሊሆኑ ይችላሉ። በጎነታቸው ግን መልከ ቀናዎች ጋ የማይገኝ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እንደ ልያ ቆይተው የሚወደዱ፣ በፍሬያቸው የሚከበሩ ናቸው፡፡ መልክ ያላት ራሔል ዕድሜ አልነበራትም፡፡ ፍሬዋም ዘግይቶ የመጣ ነው፡፡ መልክ የሌላት ልያ ግን ከመጀመሪያ ጀምሮ ፍሬ የነበራት፣ ከዕድሜዋም የገፋች ነበረች፡፡ የራሔል ወገኖች ሁሉ ስለሚወዳቸው ሁሉ ስለሚፈልጋቸው ቶሎ ያልቃሉ፡፡ የሚበረክቱት የልያ ወገኖች ናቸው፡፡ የዓለም ጥላቻው ብቻ ሳይሆን ፍቅሩም የሚጨርስ ነው፡፡ የልያ ወገኖች ብዙ ጠላት ባይኖራቸውም ራሳቸውን ግን ያልተወደደ ብለው ይጠሩታል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ያልተወደዱት ዋጋ ነው፡፡ ስለዚህ ጌታችን ወደ ዛብሎን ምድር ሄደ፡፡
የእነዚህ ወገኖች ስቃያቸው ብዙ ነው፡፡ ሰው ካላረጋገጠላቸው መልካም ሥራቸውን መልካም ብለው መጥራት አይሆንላቸውም፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያስፈልጋቸው ከቃል ይልቅ ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ ጌታቸው ሊያበረታቸው አብሯቸው ሊኖር ሄደ፡፡
እነዚህ ዛብሎኖች እንደ ስማቸው ትርጉም መኖሪያ ናቸው፡፡ በክፉ ቀን ያስጠጋሉ፣ ሰው ሁሉ በገፋን ቀን ይቀበላሉ፡፡ የተጠሉ ግን መጠጊያ የሚሆኑ ናቸው፡፡ የተወደዱት መቆያ የተጠሉት መኖሪያ ናቸው፡፡ ብዙ ብልህ ሰዎች የተጠሉና የተነቀፉ ሰዎችን ይፈልጋሉ፡፡ ምክንያቱም ዓለም የሚወደው መሰሉን እንደሆነ ያውቃሉና፡፡
ኢየሱስ የሄደው ይህንን የዝቅተኛነት ጨለማ ሊገፍላቸው ነው፡፡ የዝቅተኛነት ስቃይ የልብ ስቃይ ነው፡፡ የውስጥን ማቃሰት የሚሰማው ጌታ ብርሃን ሆኖ መጣላቸው፡፡ የዛብሎን ምድር እልል በዪ የማትፈለጊውን የሚፈልግ ጌታ መጣልሽ! የዛብሎን ምድር ደስ ይበልሽ ራስሽን ባትቀበይው እንኳ የሚቀበልሽ ክርስቶስ ደረሰልሽ!
የንፍታሌም ምድር፡- ንፍታሌም የተወዳጇ የራሔል ባሪያ የባላ ልጅ ነው፡፡ ራሔል መውለድ ስላልቻለች ባሪያዋን ባላን ሰጥታ ንፍታሌም ተወለደ፡፡ ንፍታሌም ማለት የስሙ ትርጉም የሚታገል ማለት ነው፡፡ ራሔል ተወዳጅ በመሆኗ ባላም ተወዳጅ ነበረች፡፡ ባላ ተወዳጅ ነች፣ ግን ባሪያ ነች፡፡ ወደዱኝ እያለች ቀኑን በሙሉ ስትባክን፣ ያለ ዕረፍት ስትዋትት ትኖራለች፡፡ ብትወልድም ባርነቷ የማይረሳ፣ የራሔል ባሪያ እንጂ የያዕቆብ ሚስት ተብላ የማትጠራ ናት። ባላ ግን ልያ ተጠልታ እኔ ተወደድኩ እያለች ጉልበቷን ያለ ውለታ ትጨርስ ነበር፡፡ ዘመኗን በሙሉ የምትባክነው ሌላውን ለማስደሰት ነው፡፡ የእርሷ ዘሮች የእርሷን ባሕርይ በግድ ይወርሳሉ፡፡
የባላ ዘሮች ተወዳጅ ናቸው፡፡ የሚወደዱት ግን ለባርነት ነው፡፡ የደግ አህያ ውለታዋ ጭነት መጨመር ነው እንደሚባለው ስለደግነታቸው ሁሉ ሲያዛቸው ይኖራሉ፡፡ የሳቀላቸው ሁሉ የወደዳቸው፣ ያቆላመጣቸው ሁሉ ያፈቀራቸው እየመሰላቸው ለድለላ ፍቅር ዕድሜአቸውን ይጨርሳሉ፡፡ ትንሽ ጐሽ ሲሰሙ ብዙ ይለፋሉ፡፡ የተጠቀመባቸው ወገን ግን እንዳታለላቸው ይሰማዋል እንጂ ድካማቸውን ዋጋ አይሰጠውም፡፡
የዛብሎን ወገኖች ተጠልተናል እያሉ ሥራቸውን በዝግታ ይፈጽማሉ፣ የንፍታሌም ወገኖች ደግሞ ተወደናል እያሉ ይባዝናሉ፡፡ ሁለቱም የሥነ ልቡና ችግር ነው፡፡ ጌታ ሁለቱንም ሊረዳ ወደ ዛብሎንና ንፍታሌም ምድር ሄደ፡፡
የንፍታሌም ወገኖች ተወዳጅ ናቸው፡፡ ሁሉ ስለሚፈልጋቸው ቶሎ ያልቃሉ፡፡ ሁሉን ለማስደሰት ይፈልጋሉ። ስለዚህ ሕይወታቸው ያለ ዕረፍት ያልቃል፡፡ ኑሮአቸው ትግል የበዛበት ነው፡፡ ንፍታሌም ማለት የሚታገል ማለት ነው፡፡ እንደ ስማቸው ይታገላሉ፡፡ ሌላውን ለማስደሰት ይታገላሉ፡፡ ራሳቸውን ጥለው እየሮጡ እንኳ እንደ ሞኝ እንጂ እንደ አፍቃሪ አይታዩም፡፡
ሁሉን ማስደሰት አይቻልም፡፡ እግዚአብሔርን ለማስደሰት ስንኖር ግን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ሁሉ ይደሰትብናል፡፡ ሁሉን ለማስደሰት ዕረፍት የለሽ ብኩን ኑሮ መኖር ፍጻሜው ያማረ አይሆንም፡፡ ራእይ የለሽ መሆንም ነው፡፡
እነዚህን ወገኖች በቃል ማገልገል ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ጌታ አብሯቸው ኖረ፡፡ እኛስ እንደ ዛብሎን ራሳችንን መቀበል ያቃተን፣ እንደ ንፍታሌም በሰው ፍቅር የሰከርን እንሆን ይሆን; ያለንበትን ቦታ ለማወቅ ብርሃን ያስፈልጋልና ክርስቶስን በግዛቴ ላይ አብራ እንበለው፡፡ እነዚያ የዛብሎንና የንፍታሌም ወገኖች ክርስቶስ በሄደላቸው ጊዜ ብርሃን ወጣላቸው ተባለ፡፡ እኛስ ብርሃን ወጣላቸው እንዲባልልን ክርስቶስን በልባችን ሾመነዋል?
-ይቀጥላል-
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ