የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብርሃን ወጣላቸው (ክፍል 4)

                                                
                                                        ዓርብ ነሐሴ 15/2007 ዓ.ም.
በዛሬው ዘመን ታላላቅ ከሆኑት የምሥራቾች አንዱ መብራት ያልነበራቸው ከተሞች ባለመብራት መሆናቸው ነው፡፡ መብራትን ጨርሶ ማጣት አይደለም በፈረቃ ማግኘት እንኳ ምን ያህል ሕመም እንዳለው ያለፉበት ያውቁታል፡፡ እገሌ የሚባሉ ከተሞች የሃያ አራት ሰዓት መብራት ተጠቃሚ ሆኑ ተብሎ በዜና ሲነገር በቴሌቪዥኑ መስኮት ላይ ደስታቸውን በጭፈራ የሚገልጡ ሰልፈኞች ይታያሉ፡፡ የሰው ልጅ ብርሃንን እንደ ሰብአዊ መብቱ ያየዋል፡፡ ቶማስ ኤድሰን ከሠራው ሥራ ሁሉ የረካው መብራትን፣ ብርሃን ሰጪ አምፑልን በሁሉም ቤት ማስገባት በመቻሉ ነበር። በእውነትም ከድሃዋ ቤት ጀምሮ እስከ ቤተ መንግሥት ሁሉም በእኩልነት የሚጠቀሙበትን ብርሃን በመሥራቱ ሊደሰት ይገባዋል።
የሰው ልጅ የብርሃን አፍቃሪ ነው፡፡ የሰው ልጅ የብርሃን ተጠቃሚ ነው፡፡ ያለ ብርሃን ማቀድና ሥራ መሥራት የማይቻል ነገር ነው፡፡ የሰውን ተፈጥሮ ስንመለከት ከጨለማ ጋር ተገናዝቦ መኖር የማይችል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ጨለማ ራስን አያሳይም፣ ወንድምን አያሳይም፣ አካባቢውን አያሳይም፣ ሥራ አያሠራም፣ ለመነጋገር እንቅፋት ነው፣ ለመለካት አይመችም፣ ፍርሃትን ይወልዳል፣ ጥርጣሬን ይነዛል፣ ሌባ ያመጣል፣ አጋንንትን ያሰለጥናል፡፡ ስለዚህ ብርሃን ማግኘት ትልቅ ድል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ የኖረባቸው ከተሞች ብርሃን ወጣላቸው ተብሎላቸዋል፡፡ የወጣላቸው ተፈጥሮአዊ ብርሃን ሳይሆን መንፈሳዊ ብርሃን ነበር፡፡ ተፈጥሮአዊው ጨለማ ይህን ያህል ጉዳት ካለው መንፈሳዊው ጨለማ ደግሞ የበለጠ አስጨናቂ ነው፡፡ ጨለማን ተላምዶ መኖር አይቻልም፡፡ ጌታችን የኖረባቸውና ብርሃን ወጣላቸው የተባሉት ከተሞችን እስቲ በጥቂቱ እንመልከት፡፡
የባሕር መንገድ
የባሕር መንገድ ስጋት ያለበት፣ ሳት ካሉ የሚያሰጥም ነው፡፡ ይህች ከተማ ብርሃን ወጣላት ተብሎ ተጽፎላታል፡፡ የወጣላት ብርሃን ሲመሽ የማይጠልቀው ፀሐየ ጽድቅ ክርስቶስ ነው፤ የወጣላት ብርሃን ዘይቱ ሲያልቅ የማይጠፋው የሃይማኖት መቅረዝ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እንደ ባሕር መንገድ ስጋት ያለበት ሕይወት የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ የስጋት ኑሮ የቁም ኩነኔ ነው፡፡ የሚሰጋው ሰው የሚሰጋው ነገር ከመምጣቱ በፊት ጉዳቱን እየተቀበለ ነው፡፡ ስጉ ከቀኑ በፊት የሚጎዳ ነው፡፡ በቀኑ የሚመጣው መከራ መቻያ አለው፡፡ ስጉ ሰው ግን ከቀኑ በፊት ያለ ረድኤት መከራን የሚቀበል ነው፡፡ መከራው ወይም የሚሰጋበት ነገር ቢመጣም ከዚህ በላይ የሚያሰቃይ አይደለም፡፡ በስጋት የሚኖሩ እንስሳት እነ ሚዳቋ አይሰቡም፡፡ ሕይወታቸው መባረር ያለበት፣ ፍርሃት ያጠላበት፣ አንድ ጊዜ ሣር ግጠው ቀና የሚሉበት፣ አንድ ጊዜ ውኃ ተጐንጭተው ጠላትን የሚያዩበት በመሆኑ አይሰቡም፡፡ በስጋት የሚኖርም ሰው ጠላት ባይኖር እንኳ ጠላትን እየሳለ የሚጨነቅ፣ እየበላ የሚርበው፣ እየጠጣ የሚጠማው፣ እየለበሰ የተራቆተ ያህል የሚሰማውና ሳይኖር የሚሞት ነው፡፡ ስጋት ሁልጊዜ ተጨባጭ አይደለም፡፡ እንዲሁ እየፈጠሩ የሚጨነቁ ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡ ልጆች ሳሉ ለወላጆቻቸውና ወላጅ ሆነው ደግሞ ለልጆቻቸው እየሰጉ ለአንድ ቀን እንኳ ዕረፍትን ሳያዩ የሚኖሩ፣ ከበረሃ ሚዳቋ፣ ከምድረ በዳ ዋላ ያልተሻለ ሕይወትን የሚገፉ ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹም ስጉነትን እንደ ጠንቃቃነት ቢያዩትም ስጉነት ግን ራስን የማወክ ሥርዓት መሆኑን ልንነግራቸው እንወዳለን፡፡ ነቢዩ ዳዊት ነፍሱን እንደ ጠየቃት፡- “ነፍሴ ሆይ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ?” ልንላት ይገባል/መዝ.42፡5/፡፡ 

 


እነዚህ ሰዎች በምክር የሚለወጡ አይደሉም፡፡ ይህ ጠባያቸው ስለጐዳቸው መቼ ነው የምላቀቀው; እያሉ ነጻነትን ይናፍቃሉ፡፡ ነገር ግን ሕያው የሆነው ጌታ በልባቸው ሲኖር ያን ጊዜ ነፍሳቸው በሰላም ታድራለች፡፡ የማዕበሉ አዛዥ እርሱ ነውና፡፡
አንዲት መንፈሳዊ እህቴ እግዚአብሔር ሁሉን ሰጥቷት በስጋት ከመኖሯ የተነሣ እጅግ ተጐሳቁላ አገኘኋት፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት አንድ ቀን ቢወድምስ እያለች ትጨነቃለች፣ ያ ደግ ባሏ ተኝቶ ሳለ ከእንቅልፍ ነቅታ ቢሞትስ ልጆቹን ምን አደርጋቸዋለሁ? ትላለች፡፡ በዚህች እህት በረከት የሚኖሩ ቢያንስ ከ500 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞች አሉ፡፡ እነርሱ ተኝተው ያድራሉ፣ እርሷ ግን ስትናጥ፣ ጦርነት ፈጥራ ስትታኰስ በሀሳብ ስትፋለም ታድራለች፡፡ ስጋት በሚኖረን ነገር የሚለቀን፣ በድህነትም የሚመጣብን አይደለም፡፡ ስጋት ያለማመን ውጤት ነው፡፡ ጴጥሮስ ነገ የሞት ፍርድ ሊቀበል በወኅኒ ቤት በሰላም ተኝቶ ነበር/የሐዋ.12/፡፡ እግዚአብሔር ግን መልአኩን ልኮ አዳነው፡፡ ያመነ ሰው በሞት ፍርድ ውስጥ እንኳ በሰላም ይተኛል፣ ያላመነ ግን በሰላማዊ ስፍራ እንቅልፍ ያጣል፡፡ በዕውቀት፣ በሀብት በማይኖርበት ዓለም ላይ እምነት የልብ ሰላም ነው፡፡
የባሕር መንገድ ሳት ካሉ ቀጥሎ መስጠም ያለበት ነው፡፡ ዳሩ ረግረግ ያለበት፣ የሚረገጥ መስሎ የሚያጠልቅ ቀጥሎ ለትልቁ ባሕር አሳልፎ የሚሰጥ፣ ቆሞ ከመሄድ በደረት መሳብን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከስህተት ቅርብ ሆነው የሚኖሩ ሰዎች አሉ፡፡ ባልንጀሮቻቸው እግዚአብሔርን የማይፈሩ፣ በሱስ የተዘፈቁ ናቸው፡፡ ጊዜያቸውን የሚያባክኑት በኢንተርኔት፣ በፌስ ቡክ፣ ነውረኛ ጽሑፎችን በማንበብ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከተመልካችነት ወደ አባልነት መሸጋገራቸው የማይቀር ነው፡፡ ለስህተት ቅርብ፣ ለሞት ጎረቤት ሆነው ይኖራሉ፡፡ ትንሹን ስህተት ስላልፈሩት ለትልቅ ስህተት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ቤታቸውን የሠሩት የባሕሩ መንገድ ላይ ነው፡፡ ጌታችን መጥቶ የኖረው በባሕር መንገድ ላይ ወደሚኖሩ ሕዝቦች ነው፡፡
ክፉ ባልንጀርነት፣ ጊዜያችንን የሚበሉ ፊልሞችና የነውር ጽሑፎች እንዲሁም ኢንተርኔት ሱስ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ለመላቀቅና ለመንፈሳዊው ነገር ጊዜ ለመስጠት ብዙዎች ይፈተናሉ፡፡ ፍቅር ግን የሚሻረው በፍቅር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን በፍጹም ልባችን መውደድ ስንጀምር ከኃጢአትና ከዓለም ፍቅር እንለያለን። ዛሬ ስለጠፉት ብቻ ሳይሆን ሊጠፉ ስላላቸውም በባሕሩ ዳርቻ እየተጓዙ ስላሉትም ክርስቶስን ልንሰጣቸው ይገባል፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶስ የተሸነፈ መስሎት ከገዳዮች ጋር እሳት መሞቅ ጀምሮ ነበር፡፡ እነርሱ ግን ክርስቶስን ቢክደውም አይሁድ ጴጥሮስን አላመኑትም፡፡ እንዲሁም መከራ ፈተና ሲበዛ እውነትን በመጣል ከገዳይ ጋር ለማበር እያመነቱ ላሉት ልንደርስላቸው ይገባል፡፡ የጠላት ኃይሉ ለጊዜው ነው፡፡ እግዚአብሔር ግን በድል ብርታቱ ለዘላለም ይኖራል፡፡ የባሕሩ መንገድ ግፊያ በዝቶበታል፡፡ ብዙዎች ሳት ቢሉ በሚወድቁበት ዳርቻ ላይ እየተጓዙ ነው፡፡ ክርስትና ግን ማስተዋልና ጥንቃቄ ያለበት ነው፡፡ ሕይወት በነፋስ ውስጥ የተለኰሰች ሻማ ናት፡፡ ስለዚህ ልዩ ጥንቃቄ ትፈልጋለች፡፡
የዮርዳኖስ ማዶ
ጌታችን ከኖረባቸው ከተሞች አንዷ የዮርዳኖስ ማዶ ናት፡፡ ዮርዳኖስ ብዙ ተአምራቶች የተደረገበት ወንዝ ነው፡፡ እስራኤል ዮርዳኖስ ተከፍሎ ምድረ በረከትን ወረሱ፣ ንዕማን ከለምፁ የነጻው በዮርዳኖስ የተቀደሰ ውኃ ነው፣ ጌታችን የተጠመቀው በዮርዳኖስ ወንዝ ነው፡፡ ከዮርዳኖስ ማዶ ከተማ ሠርተው የሚኖሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ወንዙ ተከፍሎ እስራኤል በረከታቸውን ሲወርሱ የሚያዩ፣ ንዕማን ከለምፁ ሲነጻ፣ ጌታችን ሲጠመቅ እያዩ ማዶ ሆነው የሚኖሩ በዮርዳኖስ ላይ የተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር የማይስባቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ጌታችን ሄዶ የኖረው በእነዚህ ሕዝቦች መካከል ነው፡፡
ዛሬም ከዮርዳኖስ ማዶ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በአገራቸው፣ በቤተሰባቸው፣ በወዳጆቻቸው እግዚአብሔር ክብሩን ሲገልጥ እያዩ ክብሩን ለእኔ ብለው የማይናፍቁ ዛሬም አሉ፡፡ የእግዚአብሔር የፍቅር ኃይል፣ የተአምራቱ ድንቅነት የማይማርካቸው ለዘመናት የእግዚአብሔርን ሥራ እያዩ የማይማረኩ ሰዎች እጅግ ያሳዝናሉ፡፡
ከመንፈሳዊ ዓለም ማዶ ሆኖ መኖር፣ ከክርስትና ማዶ ሆኖ መኖር ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ሰዎች እንጀራ እያለላቸው ረሀብተኞች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ኃያላንን ሲጥል፣ የማይቻለውን ሲችል፣ ሕዝቡን ሲረዳ፣ በረከቱን ሲያዘንብ ያያሉ ነገር ግን የበዪ ተመልካች እንጂ ተሳታፊዎች አይደሉም፡፡ ጌታችን እነዚህ ሰዎች እስኪመጡ አልጠበቀም፡፡ በመካከላቸው ሊኖር ያሉበት ድረስ ሄደ፡፡ ይህንን ድንዳኔ፣ ዕድሜ የማይለውጠውን፣ ያለፈው ዘመን ታሪክ ልቡን የማይነካውን ማንነት በፍቅሩ የሚለውጥ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ታላላቅ ተአምራትን እያዩ አለመነካት በእውነት ለደስታ ሩቅ መሆን ነው፡፡
በመንፈሳዊ አገልግሎትም የእግዚአብሔር ሠራዊት የሚያገሳውን ዮርዳኖስን ሲጠጋ ማዶ ሆነው የሚያዩ ባሕሩ ተከፍሎ ሲሻገሩ ማዶ ሆነው የሚያዩ ለእግዚአብሔር ሥራ የእኔነት መንፈስ የሌላቸው የዮርዳኖስ ማዶ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ከሆንን እግዚአብሔር ያስበን! በማዶ ሆኖ ባሕር አይከፈልም፣ ዮርዳኖስ ሲረግጡት ይከፈላል። በማዶ ሆኖ ለምጽ አይነጻም፣ ሰባት ጊዜ መጥለቅ ወይም ፍጹም መሰጠት ይፈልጋል። በማዶ ሆኖ የተጠመቀውን ክርስቶስ ማግኘት አይቻልም፣ በንስሐ መጠመቅ ያስፈልጋል። በገደብ ግንኙነት እግዚአብሔር አይገኝም። ራሳችንን በመስጠት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል። እናንተስ ያላችሁት ማዶ ነው?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ