የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብቻ ንቁ

“ንቁ ፥ በሃይማኖት ቁሙ ፥  ጎልምሱ ጠንክሩ ። በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን ።” 1ቆሮ. 16 ፡ 13-14 ። 
የስንብት ቃላት ልብን ያባባሉ ። ሰዎች በሰላምታ ተገናኝተው ፣ በስንብት ሲለያዩ ሆዳቸው ባር ባር ይለዋል ። አልጸና እያለ ይናወጥባቸዋል ። ስብሰባው በመግቢያ ንግግር ተጀምሮ ፣ በስንብት ሲጠቃለል በየተራ የገባው በጅምላ ይወጣል ። በመቅድም የተጀመረው መጽሐፍ በማጠቃለያ ሲሰናበት እፎይታ ይሰጣል ። በሃሌ ሉያ የተጀመረው ቅዳሴ “እትዉ በሰላም” ተብሎ ሲጠናቀቅ በረከትን ይዞ ሁሉም ወደ ቤቱና ወደ ሥራው ይፋጠናል ። በልቅሶ የተጀመረው ኀዘን ግብአተ መሬት ሲፈጸም “ከዚህ በኋላ ልቅሶ የለም” ተብሎ በመጽናናት ይጠናቀቃል ። መነሻ ያለው ሁሉ መድረሻ አለው ። የተጀመረ ነገር አንድ ዘመን ይፈጸማል ። ፍጥረት ሁሉ ወደ ፍጻሜ እየተጓዘ ነው ። በልደት የጀመረው የምድር ጉዞም በሞት ሊጠቃለል በእያንዳንዱ ቀን ወደምንጠላው ሞት እየሄድን ነው ። “ብንጠላው የምንጓዘው ወደ ሞት ነው” እንደ ተባለው ነው ። ስንብት ያባባል ፣ የተሰበሰበውን ይበትናል ። ጭብጥ አሳብ ይሰጣል ። በረከትን ያመጣል ። መጽናናት ይስገኛል ። ፍጻሜ ይሰጣል ። የሰውን መጨረሻ ያሳያል ። 
ኑዛዜ የስንብት ድምፅ ነው ። ሰውዬው ሊሞት ሲል ለቤተሰቡ ይናዘዛል ። ከሞተ በኋላም ኑዛዜው ይጸናል ። ዓለምና ፍላጎቷ ከኋላዬ ነው ብሎ በንስሐ የሚናዘዘው ተነሣሒም ኑዛዜው እንዲጸና ለተናዘዘበት ኃጢአት መሞት ያስፈልገዋል ። የመጨረሻ ቃላት የማይረሱና የአደራ ቃላት ናቸው ። ታላላቅ የሚባሉ ሰዎች በመጨረሻው ሰዓት የተናገሩት ሲወሳ ይኖራል ። የስንብት ቃል ብዙ ጊዜ እውነት ነው ። ሰው የሚዋሸው እኖራለሁ ብሎ ሲያስብ ነውና ። “ደህና እደር ልጄ” እና “ደህና ሁን ልጄ” ብለው የሞቱ ሰዎች ንግግራቸው ይመነዘራል ። “አባዬ ደህና እደር ያለኝ በሰማይ ስለምንገናኝ ነው ።” “እኔን ደግሞ ደህና ሁን ያለው በእግዚአብሔር አላምንም በፈቃዱ አልኖርምና አንገናኝም ማለቱ ነው” በማለት አንዱ ደስታን ሌላው ጸጸት ያተርፋል ። የመጨረሻ ቃላት አይረሱም ። 
ጌታችን በመስቀል ላይ የተናገራቸው ሰባቱ የመስቀል ጩኸቶች ሲታወሱ ይኖራሉ ። እነዚህን ቃላት የተናገረው በዕለተ ዓርብ ከስድስት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ነው ። የተናገረውም ባማረ መድረክ ፣ በተዋበ አትሮኖንስ ፣ በከበረ ልብስ ፣ በድምፅ ማጉያ ፣ ውኃ እየተቀዳለት ፣ እየተጨበጨበለት ፣ … አይደለም ። በጨለማው ሰዓት ፣ በመስቀል ተንጠልጥሎ ፣ እጆቹና እግሮቹ በምስማር ተቸንክረው ፣ በደም ማዕበል ተጥለቅልቆ ፣ ዕርቃኑን ሁኖ ፣ በታላቅ የጣር ድምፅ ፣ ተጠማሁ እያለ ውኃ ተከልክሎ ፣ ጠላቶቹ እየዛቱበትና ጥርሳቸውን እየነከሱበት ነው ። እነዚህ የሕይወት ቃላት ሀብተ መስቀል ሁነው ይኖራሉ ፣ አይረሱም ። በውስጣቸውም ይቅርታ ፣ ስጦታ ፣ ፍቅር ፣ የኃጢአት ዋጋ ፣ አምላክ ከሰው የሚፈልገው ፣ የድኅነት ጉዞ መጠናቀቅ ፣ ተስፋ አለ ። 
ሐዋርያው ጳውሎስ አንደኛ ቆሮንቶስን ሲጽፍ የመሰናበቻ ንግግሩ፡- “ንቁ ፥ በሃይማኖት ቁሙ ፥  ጎልምሱ ጠንክሩ ። በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን” የሚል ነው ። 1ቆሮ. 16 ፡ 13-14 ። 
“ንቁ” ይላል ። ተራቁተው የተኙትን ብቻ ሳይሆን ለብሰው ያሸለቡትንም ፣ በአልጋ የተኙትን ብቻ ሳይሆን በወንበር ያንጎላጁትንም ንቁ ይላል ። ዓይናቸውን የጨፈኑትን ብቻ ሳይሆን ገልጠው የተኙትንም ንቁ ይላል ። የማያዩትን ብቻ ሳይሆን እያዩ የማያዩትን ፣ አዚም ውስጥ የገቡትንም ንቁ ይላል ። የሞት ታናሽ ወንድም የሆነው እንቅልፍ የወሰዳቸውን ብቻ ሳይሆን ሳይነቁ የሚጓዙትንም ንቁ ይላል ። ጠቢቡ ሰሎሞን ሲተኛ ዓይኑን ገልጦ ፣ ሲነቃ ዓይኑን ጨፍኖ ነው ይባላል ። ስለዚህ ነቃ ብለው ሲሸሹት ፣ ተኛ ብለው ሲጠጉት ይኖር ነበር ። መተኛቱና መንቃቱ ያልለየ በጣም አስቸጋሪ ነው ። እኛም የሰሎሞን ዘር እንዳለብን አለብንና መተኛታችንም መንቃታችንም የማይታወቅ ወገን እየሆንን ነው ። ተኝተዋል ሲባል ዘራፍ የአክሱም ፣ የላሊበላ ሠሪዎች ነን እንላለን ። ነቅተዋል ሲባል ሰው ዘልዝለን እንሰቅላለን ። ሐዋርያው፡- “ንቁ” ይላል ። መንቃት ለራስ እንጂ እነ እገሌ ነቅተዋል እንዲባል አይደለም ። ጌታ ገብቶናል ፣ ኢየሱስን አውቀናል የሚሉ ሰዎች እኛ በርቶልናል ፣ እነ እገሌ አልበራላቸውም ይላሉ ። መንቃት በንግግር አይደለም ፣ የተኛም እየቃዠ ያወራልና ። በእንቅልፍ ልብ ተነሥቶ የሚሰብክም አይታጣም ። ንቃት መናገር መቻል ሳይሆን በትክክል መከወን ነው ። መከወንም ብቻ ሳይሆን ነቅቶ ማድረግም ነው ። ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ ከአራት ኪሎ ሰአሊተ ምሕረት የሚጓዙ ፣ በር ከፍተው በጠፍ ጨረቃ የሚወጡ አሉ ። ሲነቁ ራሳቸውን ርቀው ያገኙታል ። መሄድም መንቃት አይደለም ። ንቃት ወዴት እንደሚሄዱ ማወቅ ነው ። በእንቅልፍ ልባቸው የቤቱን ልብስ አውጥተው የሚያጥቡ አሉ ፣ ሥራቸው ግን የሚያስመሰግን ሳይሆን የሚያሳዝን ነው ። አልነቁምና ።
አጠገብ የተኛ ሰው ካለ እንቅልፍ ያመጣል ። እንቅልፍ ይጋባልና ሾፌር አጠገብ የሚቀመጥ ንቁ መሆን አለበት ። መንቃት ብቻ ሳይሆን እያጫወተና እያየለትም መሄድ አለበት ። አጠገብ የተኙ ሰዎች ካሉ መቀስቀስ ያስፈልጋል ፣ ቀጥሎ እኛም እንተኛለንና ። መሪ ይዞ መተኛት ተሳፋሪውንም ራስንም ይዞ ገደል መግባት ነው ። መዝሙረኛው፡- “ለሞትም እንዳልተኛ ዓይኖቼን አብራ” ያለው ለዚህ ነው ። መዝ. 12 ፡ 3 ። ቤት በእሳት እየነደደ ያለው እንቅልፍ ፣ ሌባ ቤት ውስጥ እየገባ ያለው አዚም አይጣል ነው ። ለዚህ ነው ዘማሪው ለሞት መንቃት እንጂ መተኛትን ተጸይፎ ዓይኖቼን አብራ ያለው ። አንዳንድ ሰዎች ተኝተሃል ሲባሉ እየሰማሁ ነው ይላሉ ። በንቃትና በእንቅልፍ መካከል ያሉ ሰዎችም ንቁ ተብለዋል ። ወታደር ሸሸ አይባልም አፈገፈገ ነው ። ተኛሁ ለማለት ያፈሩ እየሰማሁ ነው ይላሉ ። መንቂያው ሰዓት ሲደርስ በጣም የሚተኙ ሰዎች አሉ ። መነሻው ዘመን ላይ ትኩስ እንቅልፍ የያዛቸው የሕይወት ባቡር ጥሏቸው ይሄዳል ። 
ምድራችን ባልተማሩና ተምረው በደነቆሩ ተኚዎች ተጨንቃለች ። የተማሩት ጦርነት ሲፈጥሩ ፣ ያልተማሩት ይጨርሳሉ ። መንቃት ያስፈልጋል ። ሁልጊዜ ገዳይ መሆን የለም ፣ ገዳይም ሟች ይሆናልና መንቃት ይገባል ። ዘረኝነት እየወረረን ፣ የትላንቱን በአብሮነት እያስረሳን ነውና መንቃት ያስፈልጋል ። በብሶት ንግግር ያልደላንን እኛን የሚቆሰቁሱንን ነቅተን መሸሽ ይገባል ። ምስጋና እንጂ ብሶት እግዚአብሔርን አያሳይም ። የፈረድነው ነገር ሁሉ በቤታችን ገብቷል ፣ በአገራችን ሞልቷል ። በሃይማኖት ፣ በበሽታ ፣ በኃጢአት ፈረድን ፤ ሁሉንም ተከናንበን ቁጭ አልን ። ዛሬም የምንፈርድባቸው ነገሮች ነገ ዙፋን ይዘው እንዳይገዙን ፍርድን ትተን ትምህርትን ማስፋፋት ይገባናል ። ልጆቻችንን ችላ ብለን ብር የምናሯሩጥ ብር ሲገባ ልጆቹ ይወጣሉና ፣ ሕንፃው ሲደመደም ትዳሩ ይፈርሳልና መንቃት ያስፈልጋል ። የጋራ ሞትን እንደ ሕይወት የቆጠሩ መንፈሳዊ ስብስቦች መንቃት ያስፈልጋቸዋል ። ዛሬ ብሉኝ ብሉኝ የሚለው ቃለ እግዚአብሔር ነገ ላይገኝ ይችላልና ነቅተን መሰብሰብ ይገባናል ። “አጥብቀው ያሰሩትን ዘቅዝቀው ይሸከሙታል” እያሉ የሚወዱአቸውን የሚያጣጥሉ ፣ የሚያፈቅሯቸውን ሰዎች ችላ የሚሉ “የዋህ ካመረረ ፣ በግ ከበረረ” አይመለስምና መንቃት ይገባቸዋል ። ሰው ከፋ እያሉ የሚያወሩ ደጎቹን ግን አክብረው ያልያዙ የሰው ድሀ መሆን ይመጣልና መንቃት ይገባቸዋል ። 
“አገሬ ኢትዮጵያ ጠንክረሽ ተማሪ ፣ ሁልጊዜ አይገኙም ዕድልና መሪ” ይባላል ። ሁለቱ ገጥመው ከተገኙ ትልቅ ስጦታ ነው ። ሴትዬዋ፡- “አልጋው ሲገኝ ባሉ አይገኝ” እንዳለችው አንዱ ሲገባ አንዱ ይወጣልና ዕድልና መሪ በቤት ፣ በቤተ ክርስቲያን ፣ በአገር ሲገኝ መንቃትና መጠንከር ይገባል ። 
ብቻ ንቁ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ