የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ብናውቅ

“ኢየሱስ መልሶ፦ የእግዚአብሔርን ስጦታና፡- ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር አላት ።” ዮሐ. 4፡10 ።
አንድ ቀልድ ቢጤ ሲነገር እንሰማለን ። ለእግዚአብሔር ስለሚሰጡ ሦስት ዓይነት ሰዎች የሚገልጥ ነው ። አንደኛው ሰውዬ ክብ ሠራና፡- “ገንዘቤን ወደ ላይ እወረውራለሁ ፣ ክቡ ውስጥ የወደቀው የእኔ ከክበቡ ውጭ የወደቀው የእግዚአብሔር ነው” አለ ። ሁለተኛው ደግሞ መስመር አሰመረና፡- “እኔ ገንዘቤን ወደ ላይ እለቃለሁ ፣ ከመስመሩ ወዲህ የወደቀው የእኔ ፣ ወዲያ የወደቀው የእግዚአብሔር ነው” አለ ። ሦስተኛው ደግሞ “ገንዘቤን ወደ ላይ እበትናለሁ ፣ የወረደው የእኔ ፣ አየር ላይ የቀረው የእግዚአብሔር ነው” አለ ይባላል ።
እግዚአብሔርን ከሕይወታቸው ውጭ አድርገውት ነገር ግን ትንሽ ገንዘብ መጣል የሚፈልጉ ፣ በኑሮአቸው ክበብ ውስጥ ሊጋብዙት የማይሹ ብዙ ሰዎች አሉ ። እግዚአብሔር በመንበሩ ይኑር ፣ እኔም በምድር እኖራለሁ ፣ እኔን የሚያስደስተኝ ነገር እርሱን አያስከፋውም ፣ በአእምሮዬ እጠቀማለሁ እንጂ ጸሎትና ቤተ ክርስቲያን መሄድ አያስፈልገኝም ብለው የሚስቡ ሰዎች እየበዙ ነው ። እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔር የለም ለማለት አይደፍሩም ፣ ማኅበረሰቡን ይፈራሉ ። ለቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለማድረግም በጣም ስስታም አይደሉም ። ነገር ግን እግዚአብሔርን ከሕይወታቸው ክበብ ውጭ አድርገው የሚኖሩ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ዝግ በመሆናቸው የሰውን ይሰማሉ እንጂ የራሳቸውን መናገር አይፈልጉም ። ድብቅነታቸውና ውሳኔ የሌለው ሕይወታቸው ውስጥ ውስጡን ቢከነክናቸውም ወደ ፍቅር ዓለም መጠቃለል አይፈልጉም ። ለማንም ሰው ጥርሳቸውን ይጋብዛሉ ፣ ልባቸውን መጋበዝ ግን ይቸገራሉ ። የጸዳ ኑሮ የላቸውም ። እያላቸውም አኗኗርን አያውቁበትም ። ራሳቸውን መደበቃቸው ትልቁ ኩራታቸው ነው ። እነዚህ ሰዎች የወደቁ ቀን ትንሣኤ የላቸውም ። የማይደሰቱበት ቤትና ትዳር አላቸው ። ገንዘባቸውንም ስለማይጠቀሙበት ተቆልሎ ሲያዩት ደስ ይላቸዋል ። በጥሩ ቃል ቢሸኙም የሰውን ጉዳይ ጉዳዬ ነው ብለው ማሰብ አይፈልጉም ።
መስጠት መርሕ በሆነባት ሕይወት ውስጥ ሁለተኛዎቹ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ለእኩል እየተካፈሉ የሚኖሩ ናቸው ። ሙሉ ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር አይሰጡም ። መጸለይም መጨነቅም ገንዘባቸው ነው ። ዓለማዊነትም መንፈሳዊነትም ያምራቸዋል ። ወንበራቸውን አስጠብቀው ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣሉ ። በማንኛውም ሰዓት ደግሞ የሱስና የኃጢአት ወንበራቸው ላይ ይቀመጣሉ ። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በመውቀስ ወደር የላቸውም ። ጸጸታቸው ግን ዕድሜ ስለሌለው መልሰው ባስለቀሳቸው ነገር ይያዛሉ ። ሲሰበኩ በቀላሉ ይነካሉ ። ሲገሠጹ ያለቅሳሉ ። መልሰው ግን የተፉትን ይልሳሉ ። ጭቃ ላይ ተቀምጠው ስለሚታጠቡ መልሰው ይቆሽሻሉ ። ሁልጊዜ ጀማሪ ናቸው ። ብዙ መሠረት አላቸው ፣ አንድ ጉልላት ግን የላቸውም ። የተሰማቸውን እንጂ እውነት የሆነውን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም ። ከወገብ በላይ ታቦት ፣ ከወገብ በታች ጣዖት እንደሚባለው ናቸው ። አብረዋቸው ለሚኖሩ ሰዎች የሚያዳክሙ ናቸው ።
ሦስተኛዎቹ ሰዎች ሕይወታቸው ላይ የሚያፌዙ ናቸው ። እግዚአብሔር እንዳልበድል ከፈለገ ለምን በደልን ፈጠረ ይላሉ ። በሱስ ወንበር ላይ ተቀምጠው ስለ አዳም ትክክለኛነት ይሟገታሉ ። መጠጥ አትጠጡ ሲባሉ መጽሐፍ “ወይን ያስተፌስሕ” ይላል በማለት የማይገናኝ ጥቅስ ይጠቅሳሉ ። ሕይወት ከእግዚአብሔር የተቀበሉአትና በኋላም የሚያስረክቧት አደራ መሆኗን ይዘነጋሉ ። ስለ እውነት መስማት በፍጹም አይፈልጉም ። በከንቱ ጨዋታ እውነትን ይደልላሉ ። ሁሉ ዓለም እንደ ተሞኘና እነርሱ ብቻ እየኖሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል ። ወጣትነት የመበደል መብት እንደሆነ ይናገራሉ ፣ ለንስሐ እርጅና ዘመን ላይ እንደሚደርስ ያስባሉ ። እርሱም ቢሆን ሐሰታቸውን እንጂ እውነታቸውን አይደለም ። ብዙ ሰው ስለሚስቅላቸው ልክ የሆኑ ይመስላቸዋል ። እነዚህ ሰዎች በድንገት በታላቅ ጭንቀት ውስጥ ይወድቃሉ ። አእምሮአቸው ይጣላቸዋል ፣ ራሳቸው የሚያመልጣቸው መስሎ ይሰማቸዋል ። እነዚህ ሰዎች ብዙ ጊዜ ሲሰበሩና በታላቅ ፈተና ውስጥ ሲገቡ እግዚአብሔርን ይፈልጋሉ ።
ሕይወት ከእግዚአብሔር የመቀበልና ለእግዚአብሔር የመስጠት ሂደት ናት ። ሕይወት ከሰዎች የመቀበልና ለሰዎች የመስጠት ባሕል ናት ። ለመስጠት ከሰሰትን አንቀበልም ። ፍቅርን ፣ ቸርነትን ፣ እውቀትን … መስጠት ካቆምን አይጨመርልንም ። ካልተጨመረልን የያዝነውን እንጨርሳለን ።  በመጨረሻም ባዶ እጃችንን እንቀራለን ። የዚህ ሁሉ ችግር አለማወቃችን ነው ። እግዚአብሔር ማን መሆኑን አላወቅንም ። በመለመኑ ውስጥ መስጠት ፣ በመጠየቁ ውስጥ መልስ ያለው መሆኑን አልተገነዘብንም ። እግዚአብሔር ሕይወታችንን የሚጠይቀን አበጃጅቶ መልሶ ሊሰጠን ነው ። ትንሹን ገንዘብ የሚጠይቀንም ትልቁን ጸጋ ሊሰፍርልን ነው ።
ሳምራዊቷ ሴት ጌታችን ውኃ ሲጠይቃት እርሷ ብዙ ጥያቄ አነሣች ። ውኃ የሚጠይቃት የውኃው ፈጣሪ መሆኑን አልተገነዘበችም ። የሕይወት ባለቤት የሆነው ጌታ ሕይወታችንን ሲጠይቀን ፣ የጊዜ ባለቤት ጊዜአችንን ሲለምነን ፣ የገንዘባችን ምንጩ አሥራት በኩራታችንን አምጡ ሲለን አልገባንምና እሺ አላልነውም ። እርሱ እኛነታችንን ሲጠይቀን እኛ ስለ ሕዝቡ መጎሳቆል እናወራለን ፣ እርሱ ገንዘባችንን ሲጠይቀን እኛ ታማኝ አገልጋይ የለም እንላለን ። በቀጥታ እየመለስን ሳይሆን አፍራሽ ጥያቄዎችን እያቀረብን ነው ። ጊዜያዊ መከታ ካገኘን እንጽናናለን እንጂ እኔን የሚመለከተኝ የቱ ነው አንልም ። የሚለምነን ሰው ስናይ አለው አይደለም ወይ ? እንላለን ። ራበኝ የሚለንን ዘሩ ምንድነው ? በማለት እንጠይቃለን ። ሃይማኖት እየለየንም ደግ ነገር እናደርጋለን ። ቀጥተኛ ሕይወትና መልስ የለንም ። ደህና ነህ ወይ? ስንባል እገሌ ደህና ነው ፣ ምን ይሆናል ብለህ ነው እንላለን ። ንስሐ ግቡ ስንባል ፈረንጆቹ ይህን ሁሉ እየሠሩ በጥሩ ይኖራሉ እንላለን ።
ብታውቂ በማለት ጌታ ተናገረ ። የዘላለም ውኃ የሚሰጠውን ባለማወቅ አጉላላችው ። የፈጠረው ሳይከለክላት የተቀበለችው ከለከለችው ። የቤተ ልሔም ሰዎች በበረት የተወለደውን ጌታ አላወቁም ። ቢያውቁ ኑሮ እነርሱ በበረት አድረው ጌታን በቤታቸው ያስተናግዱት ነበር ። ቢያውቁ ኑሮ በእንግዶች ማረፊያ ያረፈውን ሰው በሙሉ አስወጥተው እርሱን ያስገቡት ነበር ። አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር” ተባለ ። 1ቆሮ. 2፡8 ። አለማወቅ ሰቃልያነ እግዚእ ያደርጋል ። አለማወቅ ለሰጪው እንዲከለክሉ ያደርጋል ፣ አለማወቅ ንጉሡን ደጅ ያስጠናል ፣ አለማወቅ የሰማይ የምድሩን ጌታ በበረት ጥሎ ሰውን በቤት ያስተኛል ።
ዛሬም አለማወቅ እየበዛ ነው ። ሰው ስለመሰብሰብ እንጂ ስለመስጠት አያስብም ። የሰበሰበውን እንደሚበላው ግን እርግጠኛ አይደለም ። ስግብግብነት እየበዛ መጨካከን እየነገሠ ነው ። ሁሉን ለእኔ የሚባል የልጅነት ጠባይ በዕድሜ የገፋነውንም እየተሟገተን ነው ። ብዙ ሰው የራሱን ደሴት ሠርቶ መኖር የሚፈልግ ነው ። በዙሪያው ሰው ሳይሆን ውኃ ብቻ እንዲኖር የሚፈቅድ አያሌ ነው ። ዝግ ልቦች የፈጠሩአቸው ብዙ ዝግ ቤቶች አሉ ። የመጠባበቅ ሕይወት እየነገሠ ነው ። ካልደወለ አልደውልም የሚል ድምፅ በየቀኑ ይሰማል ። የብድር እንጂ የነጻ ፍቅር እየተሸኘ ነው ።
የራሱ ጉዳይ የሚሉ ድምፆች ትዳርንና ወዳጅነትን ጠቅጥቀን እንድንሄድ እያደረጉን ነው ። ራስን ብቻ ማዳመጥ ለማንም ሰው ስሜት እንዳንጠነቀቅ እያደረገን  ነው ። በአጭር ቃል አብደናል ። የማያደርስ መንገድ ላይ ጉዞ ጀምረናል ። ይሮጣል ይሮጣል ፣ ብዙ ሰው ግን ግቡን አያውቀውም ። እናውቃለን እንላለን ፣ የቅጥፈት እንጂ የእውነት እውቀት እየተለየን ነው ። ዝምድናን አብሮ መኖርን ስናፈርስ ትንሽ እንኳ ቅር አይለንም ። ቤት ለመሥራት አገር ማፍረስ አለማወቅ ነው ። ልጅን ለማሳደግ የትምህርት ቤት መሥሪያን መስረቅ በእውነት አለማወቅ ነው ። የእርዳታ እህል መዝረፍ በእውነት ትልቅ የአእምሮ ድህነት ነው ። ከሬሳ መዝረፍ ከሰውነት ተራ መውጣት ነው ። የደከመውን ይህን ሕዝብ መግረፍ በእውነት ጀግና የማያሰኝ ነው ።
“ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” ይላል ። ሆሴ. 4፡6 ። ትንቢት በማጣቱ ጠፋ አይልም ፣ እውነትም ይሁን ሐሰት እተነብያለሁ የሚል ብዙ አለ ። ፈዋሽ በማጣቱ ጠፋ አይልም ፣ ሐኪም ቤት እናዘጋለን የሚሉ ፈዋሾች በዝተዋል ። የጠፋነው እውቀት በማጣት ነው ። እግዚአብሔር በእውቀት ይባርከን ።
የለህም ያሉህን ባለመኖር የሸኘህ ፣ የተገዳደሩህን በጣትህ የረታህ የማመልክህ ብሩህ ጌታ አመሰግንሃለሁ ። የመረጥክልኝን ትቼ የመረጥኩትን ሳሳድድ ፣ ደርሼም ገና እፈልጋለሁ ። ያልከው በሕይወቴ ይሁን ። ሁለንተናዬን ሰጥቼ ላከብርህ እሻለሁ ። እጆቼን በእጆችህ ያዛቸው ። አገሬ እስክገባ አጥብቀህ ያዘኝ ። የእኔ ባልሆነው ዓለም እንዳልደናገር ምራኝ ። ጣዕም ባለው ስምህ ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 21
ግንቦት 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ