የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

‹‹ተወልዶላችኋል››(ሉቃ. 2÷11)፡፡

                                                        ሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 2004 ዓ.ም.
የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን ቀን፣ ቀኑን በሙሉ በዝማሬና በምሥጋና ያከብሩታል፡፡ የክርስቶስ መወለድ በሚዘከርበት ዕለት መብልና መጠጥ ማዘጋጀት ክልክል ነው፡፡ ለምን? ስንል ሥጋዊው ደስታ መንፈሳዊውን ምሥጢር እንዳይጋርደው በማሰብ ነው፡፡ በማግሥቱ ግን መብልና መጠጥ ማዘጋጀት ይፈቀዳል፡፡ የጌታችን መወለድ የሰው ዘር እንደገና የተፈጠረበት ቀንና ምሥጢሩም ታላቅ በመሆኑ በቁሳዊ ነገር እንዳይሸፈን ቤተ ክርስቲያን መከልከል አለባት፡፡ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መንፈሳዊ ግዳጃቸውን በመወጣት ጌታችን የተወለደበትን ቀን በአምልኮና በምሥጋና ብቻ ያከብራሉ፡፡ በእኛ አገርና በሌሎችም አገሮች የክርስቶስን ልደት ሥጋዊ ደስታ ጋርዶት እናያለን፡፡
የክርስቶስን ልደት ስናነሣ ትዝ የሚለን ነገር ሰው የመሆኑ ምሥጢር አይደለም፡፡ ፈረንጆቹ ስለ ገና አባትና ስለ ገና ዛፍ ስለ በረዶ ያስባሉ፡፡ በአገራችንም ስለ ገና ጨዋታ ይታሰባል፡፡ በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትም ገና የሕፃናት ነው ተብሎ ለሕፃናት ከረሜላ በማደል ይጠናቀቃል፡፡ የክርስቶስ ልደት ግን የመላው የሰው ዘር እንደገና የወለደበት እንጂ ተራ የሕፃን በዓል አይደለም፡፡ የልደትን በዓል ማክበር ብቻውን ክርስቲያን አያሰኝም፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች የሆኑት የፍልስጤም አስተዳዳሪዎች ቀድሞ ያሲን አራፋት አሁን ደግሞ ማሕሙድ አባስ በቤተ ልሔም ተገኝተው ያከብሩታል፡፡ የእኛ አከባበር ከዚህ የላቀ ካልሆነ ድካም ብቻ ነው፡፡ የተወለደውን ሕጻን በቁሳቁስ ሳይሆን በሕይወታችን ልናከብረው፤ ደስታችንም በመብልና በመጠጥ ሳይሆን በፍቅሩ ሊሆን ይገባዋል፡፡ 

ብዙዎች እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን እያሉ ይዘፍናሉ፣ ይጨፍራሉ፣ ይሰክራሉ፡፡ ክርስቶስ ግን የተወለደው ዘፈን፣ ኃጢአትና ዝሙት ከተባሉት የጨለማ ሥራዎች ሊያድነን መሆኑን ገና አላወቁም፡፡ ይልቁንም ቃሉ፡- “የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ÷ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና” ይላል (ዘፀ. 20÷7)፡፡ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ መጥራት ማለት በስሙ በተሰየሙ ቀናት ኃጢአትን መሥራት ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔርን የኃጢአታችን ተባባሪ ማድረግ ነው፡፡ ፍርዱም ከፍ ያለ ነው፡፡  
  
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለዱ የዓለምን ታሪክ ለሁለት የከፈለ ነው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ የሚያምነውም ሆነ የማያምነው ዓለም ዘመንን ሲቆጥር ከክርስቶስ ልደት በፊት ከክርስቶስ ልደት በኋላ እያለ ይቆጥራል፡፡ ለምን? ስንል ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ዘመን ለሁለት ስለከፈለው ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኵነኔ ሲባል ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን ግን ዓመተ ምሕረት ተብሏል፡፡
የጌታችን መወለድ ሰማይና ምድር የተገናኙበት፣ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት፣ ሕዝብና አሕዛብ በአዲሲቱ ዓለም በቤተ ክርስቲያን አንድ የሆኑበት፣ ሰማያውያንና ምድራውያን በአንድነት የዘመሩበት ነው፡፡ የጌታችን ልደት የዓመት በዓል ሳይሆን የየዕለት ርእስ ነው፡፡ የሰው ልጆችም የነጻነትና የሰላም ቀን ነው፡፡ እግዚአብሔር አማኑኤል የሆነበት ወይም ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስን ነሥቶ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነበት ትልቅ ደስታ ነው፡፡ እግዚአብሔር ከተዋህዶ በፊት ከሕዝቡ ጋር በረድኤት፣ በተአምራት፣ በድንቅ፣ በምልክት አብሮአቸው ነበረ፡፡ በክርስቶስ ሰው መሆን ግን በሥጋና ደም ቋጠሮ ተዛምዶን ከእኛ ጋር ሆነ፡፡ የጌታችን መወለድ ከእግዚአብሔር ጋር ቤተ ዘመድ የሆንበትን የተዋህዶን ምሥጢር የምናስብበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን ብለን ዛሬ አንመራረቅም፡፡ አማኑኤል ማለት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ማለት ነው (ማቴ. 1፡23)፡፡ እግዚአብሔር በውድ ልጁ ከእኛ ጋር ለዘላለም ሆኗል፡፡
ጌታችን ከሰማይ ርቀን የነበርነውን ሊያቀርበን እርሱ ምድራዊ ሆነ፡፡ እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ሊያደርገን እርሱ የሰው ልጅ ሆነ፡፡ ውድቀት ልማዱ የሆነውን ሥጋ ለብሶ ጠላትን ድል ነሣበት፡፡ በጎውን ሥራ ለመሥራት የተፈታን ሕዝቦች እንድንሆን በመወለዱ ነጻነትን ሰጠን፡፡ የክርስቶስ ልደት እግዚአብሔር ለእኛ ትልቅ ሥራ የሠራበት ሳይሆን እኛን ለትልቅ ሕይወት የሠራበት ቀን ነው፡፡ የሰው መነሻ የሆነው አዳም ያለ ወንድ ዘር ከድንግል መሬት እንደ ተገኘ፣ የዳነው ዓለም መነሻ የሆነው ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ በአዳም የሰው ልጆች ተብለን ነበር፣ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች ተባልን፡፡ አዳም የተፈጠረው በዚያች በመካከለኛዋ ምሥራቅ በምድረ እስራኤል ነበር፡፡ በክርስቶስ መወለድ እንደገና የተፈጠርነውም በቤተ ልሔም ነው፡፡
የጌታችንን ልደት ከብሥራት አንሥቶ በሰፊው የተረከልን ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ነው፡-          “በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች”በማለት የልደቱን ዘገባ ይጀምራል፡፡ በወቅቱ ዓለምን ሁሉ የምትገዛው ሮም ነበረች፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ቄሣር በሚል መዐርግ ይጠራ ነበር፡፡ መንበሩም ያለው በሮም ሲሆን ዓለሙንም የሚያስተዳድረው በአጥቢያ ነገሥታት በኩል ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ዓለሙን የሚገዛው ከመንበሩ ሳይንቀሳቀስ ነው፡፡ በመልእክተኞቹ አማካይነት ዓለሙን ይገዛል፡፡ ጌታችን የተወለደው ከዘመን መርጦ በሮም አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ የሮም አገዛዝ ለእግዚአብሔር መንግሥት ገላጭነት አለው፡፡ ይኸውም፡- እግዚአብሔር አብ ከሥፍራው ሳይናወጥ ይኖራል፡፡ መልእክተኛውን ቃሉን ወይም ልጁን እንዲሁም መንፈስ ቅዱስን ግን እየላከ ዓለምን ይገዛል፡፡ ወደዚህ ዓለም በሥጋ የመጣው እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ እርሱ ካረገ በኋላም መንፈስ ቅዱስ መጥቷል፡፡ ክርስቶስ በትምህርቱ፣ በቤዛነቱ ዓለሙን ገዛ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በጸጋው በተአምራቱ እንዲሁም በክርስቶስ ቃሎች ዓለምን ይገዛል፡፡ እንዲህ ሲሆን ግን የሥላሴ መንግሥት አንዲትና እኩል ናት፡፡
ጌታችን በሮም አገዛዝ ዘመን ብቻ ሳይሆን ዓለሙ ሁሉ እንዲቆጠር ትእዛዝ በወጣበት ሰሞን ተወለደ፡፡ ይህንንም ያደረገው የዓለሙ ዜጋ ሆኖ ለመቆጠር ነው፡፡ እርሱ የዓለም መዝገብ ጭምር የሚያውቀው ነው፡፡ ብዙዎች ክርስቶስ ደግ ሰው እንደነበረ፣ ትልቅ የሞራል አብዮትም በምድር ላይ እንዳመጣ ይናገራሉ፡፡ መለኮታዊነቱን ግን አይቀበሉም፡፡ እርሱ ግን በታሪክ ውስጥ የተከሰተ ብቻ ሳይሆን ታሪክንም የለወጠ የድል ጌታ ነው፡፡ ዓለም ደግ ሰው ነው ካለ ደግ ሰው ማለት ግን እውነትን የሚናገር ነው(መዝ. 11÷1)፡፡ ታዲያ ደጉ ክርስቶስ፡- “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት ተናግሯልና ከአብ ጋር እኩል መሆኑን ልንቀበል ይገባናል (ዮሐ.10 ÷30)፡፡
                                                                                  ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ