የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

“ተወልዶላችኋል”/ ክፍል 2 (ሉቃ. 2÷11)፡፡

                      እሁድ፣ ጥር 6 2004

            የቤተ ልሔሙ ሕጻን  የናዝሬቱ ኢየሱስ
ሁሉም ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ÷ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ (ሉቃ. 2÷3-5)፡፡
ሉቃስ የዘገበልን የክርስቶስ የልደቱ ነገር በውስጡ ብዙ ተአምራትን የያዘ ነበር፡፡ ኢየሱስ የተወለደው በግብፅ፣ በፋርስ፣ በባቢሎን፣ በግሪክ የአገዛዝ ዘመን ሳይሆን በሮም የአገዛዝ ዘመን ነው፡፡ ይህንን የአገዛዝ ዘመን ለምን እንደመረጠ ባለፈው ጽሑፍ ተመልከተናል፡፡ በነቢዩ በዳንኤል ትንቢት እንደተገለጠው ከባቢሎን መንግሥት በኋላ የፋርስና የሜዶን ጥምር መንግሥት ከዚያም የግሪክ መንግሥት የሚነሣ ሲሆን የመጨረሻው መንግሥት ግን የሮም መንግሥት ነበረ (ዳን. 2÷36-45)፡፡ በሮም መንግሥት ዘመን ግን የመሢሑ መንግሥት በአማንያን ልብ ተመሠረተች፡፡ የመንግሥቱ ወንጌልም በዓለም ሁሉ ተሰበከ፡፡ ሕዝቦችም ለነገሥታት በጉልበታቸው ሲገዙ ኖረው፣ ለክርስቶስ ግን በልባቸው ተገዝተዋል፡፡ በልባቸውም ላይ አንግሠውታል፡፡ ባለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ተንሠራፍታለች፡፡ የመንግሥቱም ኤምባሲ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለምድራውያን ነገሥታት የመጨረሻው ንጉሥ የተባለው የሮም መንግሥት ነው፡፡ ለዘመናት የጸናውና የሕዝቦችን ልብ ዙፋን ያደረገው የክርስቶስ መንግሥት በምድር ላይ የተመሠረተው በሮም የአገዛዝ ዘመን ነውና፡፡ ጌታችን በሮም የሥልጣን ዘመን መወለዱ የሚያስተምረን ነገሮች አሉ፡-
1ኛ- የሮም መንግሥት የሥላሴን መንግሥት በትንሹ ያብራራል፡- የሮም አገዛዝ ስልት ንጉሠ ነገሥቱ ከሮም መንበሩ ሳይናወጥ ዓለምን በመልእክተኛ እንደሚገዛ እንዲሁም እግዚአብሔር አብ ከስፍራው ሳይናወጥ ቃሉን መንፈሱን እየላከ ዓለምን ይገዛል፡፡ ስለዚህ ጌታችን የሥላሴን መንግሥት በትንሹ በሚገልጠው በሮም አገዛዝ ዘመን ተወለደ፡፡ የሮም መንግሥት እንደ ግብፅ አገዛዝ ባሪያ አድርጎ የሚያስጨንቅ፣ እንደ ፋርስ አገዛዝ ዘርን የሚበክል/የሚቀይጥ፣ እንደ ባቢሎን ከትውልድ አገር አፍልሶ ነገር ግን አንደላቆ የሚያኖር፣ እንደ ግሪክ መንግሥት አእምሮን በፍልስፍናና በዘመናዊነት በመቆጣጠር በርኩሰት የሚገዛ መንግሥት አይደለም፡፡ የሮም መንግሥት ሕዝቦችን ባሉበት ስፍራ በቋንቋቸው፣ በባሕላቸው፣ በሃይማኖታቸው ሆነው የንጉሠ ነገሥቱን ሥልጣን እንዲቀበሉ ብቻ የሚያደርግ መንግሥት ነበር፡፡ እንዲሁም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መንግሥት ከቋንቋ፣ ከወገን፣ ከዘር፣ ከነገድ ዋጅቶ ሕዝቦች ባሉበት ስፍራ ሆነው ጌትነቱንና አዳኝነቱን ተቀብለው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፡፡ የክርስቲያን ሃይማኖት የባሕል ተጽእኖ የለበትም፡፡ እንደውም ባሕላችንን ለእርሱ ክብር እንድናደርገው ይመክረናል፡፡
ዛሬ እንደምናያቸው ሚስዮናውያን ሐዋርያት ባሕላቸውን ይዘው ወደ ዓለም አልወጡም፡፡ ዛሬ እየተሰበከ ያለው ወንጌል ብቻ አይደለም የፈረንጆችም ባሕል ጭምር ነው፡፡ ሕዝባችን ከፕሮቴስታንት ጋር ያልተስማማው በኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን የሌሎችን ባሕል ባለመፈለግ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ብናይ በአገራችን ያሉ የሉተራውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕንጻቸው ቀጥሎ እንዳለው ቅርጽ ^ ከላይ ግጥም ሆኖ ቅጥነቱን እንደጠበቀ በረጅሙ ወደ ታች የሚወርድ ነው፡፡ ይህ አሠራር የሚጠቅመው በረዶ ለማንሸራተት ነው፡፡ ወንጌል ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ግን የሕንጻ ጥበቡም አብሮ መጥቶ በረዶ በሌለበት አገር የበረዶ ቤቶች ተሠርተው እናያለን፡፡ ወንጌል ግን የራሷ ባሕል የላትም፡፡ የሕዝቦችን ባሕልና ቋንቋ ለእግዚአብሔር ክብር እንዲሆን የምታበረታታ ናት፡፡  
2ኛ- የመጨረሻው መንግሥት መሆኑን ለመግለጥ ነው፡- የሮም መንግሥት በክርስቶስ መምጣት ዋዜማ ላይ ያንሠራራ መንግሥት ነው፡፡ በክርስቶስ ልደት ይህ መንግሥት ገናና እንደነበረ፣ በመጨረሻው ዘመን በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዋዜማም የሚያንሠራራ መንግሥት ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግሥት በምድር ላይ ከተመሠረተ ሁለት ሺህ ዓመታት ሆነውታል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክም የእግዚአብሔር መንግሥት ታሪክ ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን በልደቱ መንግሥቱን በመመሥረት የሮማን መንግሥት የመጨረሻ እንዳሰኘው በዳግም ምጽአቱም የነገሥታት ንጉሥ ሆኖ በመገለጥ የአጽናፈ ዓለሙ ንጉሥ በመሆን ምድራውያን ነገሥታትን ለዘላለም ያሳልፋቸዋል፡፡ ስለዚህ ጌታችን በሮም የአገዛዝ ዘመን መወለዱ ልዩ ትርጉም አለው፡፡
ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከንጉሠ ነገሥት ትእዛዝ በወጣበት ዘመን ጌታችን መወለዱ የምድራችን ዜጋ ሆኖ ለመቆጠር መፈለጉን ያሳያል፡፡ የንጉሠ ነገሥቱም አዋጅ ሁሉም ወደ ትውልድ ስፍራው ሄዶ እንዲቆጠር ያዝዝ ነበር፡፡ ይህም የእግዚአብሔር ጥበብ ነበረበት፡፡ ይኸውም እመቤታችን ማርያምና ጠባቂዋ ዮሴፍ ይኖሩ የነበረው በሰሜን እስራኤል በገሊላ ናዝሬት ነበረ፡፡ እመቤታችን ወሯ ገብቶ መውለጃዋም ተቃርቦ ነበር፡፡ ጌታችን መወለድ የነበረበት እንደ ትንቢቱ በቤተ ልሔም ነው(ሚክ. 5÷2)፡፡ የንጉሥ አዋጅ ካልመጣ በቀር ድርስ እርጉዝ ያንን ረጅም መንገድ በድፍረት አትጓዝም፡፡ እግዚአብሔር ልጁ የምድር ዜጋ ሆኖ እንዲቆጠር የቆጠራ አዋጅ እንዲነገር አደረገ፤ ልጁ በቤተ ልሔም ተወልዶ ትንቢትን እንዲያሟላ ሁሉም በትውልድ አገሩ ይቆጠር ብሎ ብርቱ አዋጅ አስነገረ፡፡ እመቤታችንም ወደ ቤተ ልሔም ተጓዘች፡፡
ቤተ ልሔም የስሟ ትርጓሜ የእንጀራ ቤት ማለት ነው፡፡ ይህች ቤተ ልሔም ግን ድህነት ያጠቃት ከስሟ ትርጓሜ ርቃ የምትኖር የረሀብ ምድር ነበረች፡፡ እነ ኑኃሚን በረሀብ ምክንያት ወደ ሞዓብ የተሰደዱት ከዚህች ቤተ ልሔም ነው (ሩት. 1.)፡፡ ዳዊት የተወለደው ከቤተሰቡም ጋር በድህነት የኖረው በዚህች ቤተ ልሔም ነው (1ሳሙ.16)፡፡ ነቢዩ ሚክያስም ይህችን ቤተ ልሔምን ባያት ጊዜ ጐስቋላ ነበረች፡፡ የስሟን ትርጓሜ የምታገኝበት፣ ውርደቷም በክብር እንደሚለወጥ ትንቢት ተናገረላት (ሚክ.5÷2)፡፡ 
በእውነት ዓለሙን ሁሉ ያጠገበው ኅብስተ ሕይወት ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተ ልሔም ተወለደ (ዮሐ. 6÷35)፡፡ ሰዎች ተመርረው የተሰደዱባት ቤተ ልሔም፣ ነገሥታት ሳይቀር ከሩቅ ምሥራቅ መጥተው ለመሢሑ ሰገዱባት፡፡ ዛሬ ቤተ ልሔም እስላሞች፣ ክርስቲያኖች፣ አይሁዶች ትገባናለች እያሉ ይጋደሉበታል፡፡ ዛሬም እንኳ የሚማርክ መልክአ ምድራዊ ውበት የሌላት ናት፡፡ ጌታ ግን ስለተወለደባት ዋጋዋ አልወደቀም፡፡ የሚማርክ ውጫዊ ማንነት ባይኖረን፣ መልካችን ለዓይን የማይገባ ቢሆን እንኳ ጌታ ግን በልባችን ከተወለደ ዋጋችን ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
የበኲር ልጅ
“በዚያም ሳሉ የመወለጃዋ ወራት ደረሰ የበኲር ልጅዋንም ወለደች በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው”  (ሉቃ. 2÷ 6-7)፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ያለ ድካም እንደ ተወለደ፣ ከድንግልም ያለ ሕማም ተወለደ፡፡ የደረሰው የክርስቶስ የመወለጃ ጊዜ ብቻ አይደለም፡፡ የዓለሙ የፈውስ ልደትም ደርሶ ነበር፡፡ በዘመናት ሲጠበቅ የኖረው የትውልዶች ናፍቆት ክርስቶስ የሚወለድበት ጊዜ ደረሰ፡፡ የጌታችን መወለድ የሰይጣን የሞት ቀኑ ነበር፡፡ ለእኛ ግን የልደት ቀናችን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ በምድር የበኲር ልጅ ነው፡፡ ለአብ ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የበኲር ልጅ እንደሆነ ሁሉ ለድንግልም ተቀዳሚና ተከታይ የሌለው የበኲር ልጅዋ ነው፡፡ እርሱ በእያንዳንዳችን ልብ በእምነት ሲወለድም የመጀመሪያና የመጨረሻው ሕይወት ይሆንልናል፡፡ ብዙ ዘመን ያሳለፍን ቢሆን እንኳ ዕድሜአችንን የምንቆጥረው ክርስቶስን ካገኘንበት ጊዜ አንሥቶ ነው፤ የሕይወት አልፋ እርሱ ነው፡፡ እርሱን ካገኘን በኋላም ሌላ እስከማያምረን ድረስ ፍጹም እናርፋለን፤ የሕይወት ዖሜጋ እርሱ ነውና፡፡
በኲር የሚለው ቃል የመጀመሪያ የሚለውን የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን አቻ የለሽነትንም የሚያመለክት ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ በኲር ነው ስንል ቢያንስ በኲርነቱ በሦስት ነገሮች ተገልጿል፡፡ ይኸውም፡-
1.  በድንግልና በመወለዱ
2.                 በተዘጋ መቃብር በመነሥቱ
3.                 በተዘጋ ቤት ገብቶ ሰላምን በመስበኩ ነው፡፡
በእነዚህ ሦስት ነገሮች ኢየሱስ አቻ አልተገኘለትም፡፡ ከእርሱ በቀር በድንግልና የተወለደ ማንም የለም፡፡ ዘር ምክንያት ሳይሆነው ከድንግል ተወልዷል፡፡ በእኛም ሕይወት የተገኘው ምክንያት ሳይፈልግ ነው፡፡ ራሱን ብቻ ምክንያት አድርጎ አድኖናል፡፡ እኛ እግዚአብሔር እንደሚያደርግልን እናምናለን፡፡ ነገር ግን መያዣ እንፈልጋለን፡፡ ኢየሱስ ግን ያለ ምክንያት በሕይወታችን ይሠራል፡፡
ጌታችን እንዳይነሣ በትልቅ ቋጥኝ መቃብሩ ተዘጋ፣ የሮም ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆሙ፣ ከዚህ አልፎ ቢነሣ ትንሣኤውን የሚያሳብሉ የሐሰት ምስክሮች ባሉበት መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ዛሬም ለእኛ የሚነሣው ቋጥኝ ተንከባሎብን፣ እንዳንንቀሳቀስ ዘብ ቆሞብን፣ በገንዘብ የተገዙ ወሬኞች ሐሰት እያወሩብን ሳለ ነውር በበኲራችን በክርስቶስ ደስ ይበለን!
ኢየሱስ ክርስቶስ በዝግ ቤት ገብቶ ሰላምን በመስበክ በኲር ነው፡፡ ዛሬ ብዙ ዝግ ቤቶች ውስጣቸው ግን ፍርሐት እንደሚያናውጠው እርሱ ያውቃል፡፡ ለመናገር የሚከብዱ ጭንቀቶች ሰዎችን እንደሚወዘውዙ እርሱ ያውቃል፡፡ ለማን ልንገር ብለው አፍ እያላቸው የታፈኑትን አእላፋት እርሱ ያውቃል፡፡ በዝግ ቤት ገብቶ ሰላምን በመስበክ አቻ የለውምና ወደ እርሱ እንቅረብ፡፡ በዝግ ልብ በምንጨነቅበት ጉዳይ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ቁልፍ በልባችን ገብቶ ሰላምን ይሰብክልናል፡፡ ያለ ድምፅም የሚያጽናናን ትልቁ መምህር ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
እርሱ የቤተ ልሔሙ ሕጻን፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው፡፡ ቤተ ልሔም የተናቀች፣ ናዝሬት መልካም አይወጣባትም ተብላ ተስፋ የተቆረጠባት ከተማ ናት፡፡ ለተናቁት ክብር፣ ለኃጢአተኞች ተስፋ ሊሆን በቤተ ልሔም ተወለደ፣ በናዝሬት አደገ፡፡ እናንተንስ አንገት ያስደፋችሁ ምን ይሆን? ከሰው ቁጥር ያራቃችሁስ ምንድነው? አይዟችሁ ኢየሱስ ተወልዷል፡፡ እንጸልይ፡-
ጌታዬ ሆይ ታሪኬ አያምርም፣ ራሴ ራሴን የምጠየፍበት ነውር አለብኝ፡፡ እባክህ በልቤ ተወለድና አክብረኝ፤ በናዝሬት ሰውነቴ አብብና የናዝሬቱ ኢየሱስ የኃጢአተኛው ወዳጅ ተብለህ በእኔ መለወጥ ምስጋናን ተቀበል፡፡ አሜን!
                         -ይቀጥላል-
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ