ተወዳጅነት በብዙ መንገዶች ሊመጣ ይችላል። እውነተኛ ተወዳጅነት ግን ዋጋ የሚያስከፍል፣ ግላዊ መለወጥን የሚጠይቅ ነው:: ሁላችንም ተወዳጅ መሆን እንፈልጋለን፤ ተወዳጅነት የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመክፈል ግን ፈቃደኛ አይደለንም። መቼም በሕይወት ውስጥ ሁሉም ሰው ይወደኛልና ሁሉም ሰው ይጠላኛል ብሎ ማሰብ ሁለቱም ጤናማ አይደለም:: ይህ ዓለም በግና ተኩላ እኩል ተሰማርተው ያሉበት ዓለም ነው:: ስለዚህ ሁሉም ሰው ሊወደን አይችልም። የጉዞ መመሪያዎችም ከሰዎች ተጠበቁ፣ ተጠንቀቁ የሚሉ ናቸው ። እግዚአብሔር ወዳጅ ነውና ወዳጅ ይሰጣል። የሚወዱን ሰዎች ስጦታዎቻችን ናቸው:: አጥብቀን፣ አክብረን ልንይዛቸው ይገባል። ሁሉ ይወደኛል ብሎ መዘናጋት፣ ሁሉ ይጠላኛል ብሎ መስጋት ተገቢ አይደለም። ሁሉ ቢወደን ሞትን አያስቀርልንም፣ ሁሉ ቢጠላንም መኖር የአንድ አምላክ ፈቃድ ነው:: ሁሉ የሚጠላቸው የምድር ገዢዎች አምሮባቸው ይታያሉ። እግዚአብሔር ለጥላቻ ድል ስለማይሰጥ አይጎዱም። የተረገሙ ሰዎች ሲለመልሙ የሚታዩት እኛው ፍርድ ሰጪ ፣ ቅጣት ሰንዛሪ ስለሆንን ነው።
ተወዳጅ ሰዎች እነማን ናቸው?
1- ሰዎችን የሚወዱ ናቸው:- ፍቅር እግዚአብሔር ነውና ክንፎቹ በጣም ሰፊ ናቸው። ስለዚህ ሁሉን መውደድ እንችላለን። ሁሉን በመውደድ ክርስቶስን እንመስለው ዘንድ “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” አለን። ጾታ፣ ዕድሜ፣ ወገን፣ ቋንቋ፣ የኑሮ ደረጃ፣ የትምህርት ወረቀት ሳያዩ ሁሉን የሚወዱ ሰዎች ተወዳጅ ናቸው። መሬት ካልዘሩባት አታበቅልም፣ ሰው መሬት ነውና ፍቅርን ካልዘራንበት አይሰጠንም። ካልወደድን የሚወደን የለም። ተወዳጅ ለመሆን ቀድመን መውደድ አለብን።
2. ትሑታን ናቸው፦ ትዕቢተኛ ሰዎችን በሩቅ አይተን እንጠላቸዋለን። በአረማመዳቸው መሬት አይንካን የሚሉትን ለመተናኰል እንፈልጋለን። ትሑታን ካልሆንን እኛም የሚያየን ሁሉ ይጠላናል፣ ይተናኰለናል። ትሕትና የራሱን ክብር የሚፈልግ ሰው ለሌላም ክብር የሚሰጥበት ነው። ትሕትና በእውቀት ሙሉ የመሆን ውጤት ነው። አላዋቂ የበታችነት ስለሚሰማው ትዕቢተኛ፣ ዋስትና ስለማይሰማው ተንኰለኛ፣ ሁሉን ስለሚጠላ ቀማኛ ይሆናል። አላዋቂ ከገዛ አባት እናቱ ጉቦ ይቀበላል:: ትሑት ሠርቶ የሚያሠራ፣ ሁሉን በቋንቋው የሚያናግር፣ ያለውን ገንዘብ፣ ሙያና እውቀት ለመስጠት የማይሰስት ነው ። ትሑታን ስንሆን ሰዎች ይወዱናል፤ ጉረኛ፣ ራሳችንን የምንቆልል ፣ መስፈርት የምናበዛ ሰዎች ስንሆን መጠላትን እናተርፋለን።
3. የማይታዘቡ ናቸው፦ ሰዎች ተናደው ስለ ልጃቸው፣ ስለ ትዳራቸው መጥፎ ንግግር ቢናገሩን እንዴት ልጁን እንዲህ ይላል? ብለን መታዘብ አይገባንም። ሰው አለ ብለው ወደ እኛ ሲመጡ ሰው ሆነን መገኘት አለብን። በዚህ ዓለም ላይ እጅግ ክፉ ሰዎች የሚታዘቡ ናቸው። ሰዎች የልባቸውን፣ ለማን ልንገር ? የሚሉትን የቤታቸውን ጉድ፣ ውስጣቸው የበገነበትን ኑሮአቸውን ሲነግሩን አብረን እያለቀስን ልንካፈላቸው ይገባል። ዛሬ ለእኛ እሑድ ፋሲካ ቢሆን ፣ ለእነርሱ ዓርብ ነውና ልናግዛቸው ይገባል። የእኛም ዓርብ እየመጣ ነውና። ተወዳጅ ሰዎች ሳይታዘቡ፣ ያዩትን ለማሳየት ሳይጥሩ የተቆጣውን ያበርዳሉ፣ እንባን ያብሳሉ። ተወዳጅ ለመሆን አለመታዘብ ይገባል ::
4. የሚረዱ ሰዎች ናቸው፦ ፊትን አንብበው ያንን ሰው ያረጋጉታል። ያልመጣው ስላልተመቸው፣ ያልሰጠኝ ስለሌለው ነው ብለው ያምናሉ። በጎ፣ በጎውን ስለሚያስቡ ጤነኛ አእምሮ አላቸው:: የራሳቸውን ድርሻ ይወጣሉ እንጂ በኑሮአቸው ፉክክር ውስጥ አይገቡም። አንዳንድ ሰዎች ስልክ ለመደወል ሰነፍ ናቸው፣ ያንን ድካማቸውን ተረድተው ራሳቸው ይደውላሉ። በመጠባበቅ ፍቅርን አያከስሙም። ተወዳጅ ሰዎች ለመሆን ሰዎችን መረዳት አለብን። ሰዎች የሚረዳቸውን ሰው በጣም ይወዳሉ። የትም ሄደው ቢመጡ እንደ ክርስቶስ እንደሚቀበላቸው ያምናሉ።
5. አይፈርዱም፦ እንደ ማኅበረስብ ፈራጅ ተብለን ብንፈረጅ ተገቢ ይመስላል:: በአገራችን ትልቁ ኃጢአት ፈራጅነት ነው። ሳያጣሩ በለው ማለት፣ በማይመለከተን የሰው ጉዳይ ላይ ጊዜ ማባከን፣ የራሳችን አሮብን የሰውን ማማሰል ፣ እንዴት ይህን ያደርጋል ? ማለት የቀን ውሎአችን ነው:: እንሰርቃለን፣ ሌባ ይገደል እንላለን። እናመነዝራለን፣ አመንዝራ ይጥፋ እንላለን። ኃጢአትን አንጠላም፣ ኃጢአተኛን እንጠላለን። ተወዳጅ ሰዎች የወደቀውን ለማንሣት የሚጥሩ፣ ፍቅርን የሚሰጡ፣ እጃቸውን የሚዘረጉ ናቸው:: እግዚአብሔር ለፍርድ ቢነሣ የማይታሰር የለም። ፍርድን ለእርሱ መተው፣ ባወቅህ ማረን ማለት ተገቢ ነው::
6. በመንገዳቸው ላይ ናቸው:- ዓላማቸውን፣ ሃይማኖታቸውን ፣ ራእያቸውን አይቀያይሩም። “እኛስ የሃይማኖት ለዋጮችን ሥራቸውን እንጸየፋለን” እንደ ተባለ ተለዋዋጭ ሰው የተጠላ ነው። በአቋው የጸና የተወደደ ነው። በሌላው መስመር ላይ የማይገቡ፣ የሚመለከታቸውን ለይተው ያወቁ ፣ ዋዛ ፈዛዛን ሳይሆን ቁምነገርን የሚፈልጉ ተወዳጅ ናቸው። የሌላውን ዓላማ አይቃወሙም፣ በኃይል ወደ እኔ ላምጣው አይሉም። በዚህ ምክንያት ተወዳጅ ፣ መስሕብ ያለው ሰው ይሆናሉ። ተወዳጅ ለመሆን በዓላማችሁ፣ በሃይማኖታችሁ ጽኑ !
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም.