መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ተወዳጅነት » ተወዳጅነት (2)

የትምህርቱ ርዕስ | ተወዳጅነት (2)

ተወዳጅ ሰዎች እነማን ናቸው?

7. ምሥጢር ጠባቂ ናቸው፦ ሰውን ሰው ከሚያሰኙ ነገሮች አንዱ ምሥጢር ጠባቂነት ነው። ምሥጢር ሊጠብቅ የማይችል ሰው ለክህነት፣ ለመንግሥታዊ ሹመት ሊበቃ አይገባውም። ይህች ዓለም ቆማ የምትሄደው በምሥጢር ነው። ምሥጢር ጠባቂ ሰዎች ለትልልቅ አደራዎች ይታጫሉ። ባለጠጎችና ባለ ሥልጣናት የቅርብ ሰው በጣም ይፈልጋሉ። መስፈርታቸውም፦ ምሥጢር ጠባቂነት፣ ታማኝነትና ንቁነት ነው። ምሥጢር ጠባቂዎች ሰፊ እውቀት ላይኖራቸው ይችላል፣ ነገር ግን በመብራት ይፈለጋሉ። በዚህ ዓለም ላይ ጓዳን የሚያሳዩት፣ የሚገለጡለት ፣ ይታዘበኛል ብለው የማይፈሩት ሰው አስፈላጊና ውድ ነው።

የጨዋ አስተዳደግ አየሁ አላየሁም፣ ሰማሁ አልሰማሁም ነው። አዋቂ የሆኑ አሳዳጊዎች ለልጆቻቸው የሚነገርና የማይነገር ነገርን ገና በጠዋቱ እየነገሩ ማሳደግ አለባቸው። በለጋነት ያልተቃናን በጉልምስና ማቃናት ከባድ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ከአስተዳደግ ያለፈውን መንፈሳዊነት ይቀርጸዋል። ለትምህርትና ለለውጥ ረፈደ አይባልም። ፈያታዊ ዘየማን ጣር ላይ ሆኖ ተለወጠ። ከመጀመሪያው የመጨረሻው የተሻለ ነው። ብዙዎች የአስተዳደግ ውጤት ናቸው፣ ምሥጢር ጠባቂነት እጅግ አስፈላጊ ነው። ምሥጢር የሚባል የለም፣ ሁሉም ነገር ገሀድ መውጣት አለበት የሚሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች የስልካቸውን፣ የባንካቸውን ፣ የኢሜላቸውን የምሥጢር ቍጥር ግን ለማንም አይሰጡም። መስጠትም የለባቸውም። በዚህ ዓለም ላይ የንግድ፣ የአስተዳደር፣ የፖለቲካና፣ የፓርቲ፣ የክህነት፣ የሙያ፣ የቅመማ፣ የወታደራዊ ዕዝ፣ የኒውክለር ምሥጢሮች አሉ። አንድ ሰው ፍጹም ራሱን ስቷል የሚባለው ሁሉንም ነገሩን አደባባይ ሲያወጣ ነው። ልብስ መልበስ ምሥጢራዊነት ነው። ቤት ማደር ፣ በር ዘግቶ በሽተኛን ማከም፣ የታካሚዎችን ምሥጢር መጠበቅ እነዚህ ሁሉ ምሥጢር ናቸው ። ምሥጢርን መጠበቅ ሕጋዊ ግዳጅም አለው። የሰሙትን ምሥጢር እንዲናገሩ ዳኛም የ ማያስገድዳቸው ባለ አደራዎች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የምሥጢር አገልጋይ የሆኑት አበ ነፍሶች ናቸው።

ምሥጢር የሚጠብቅ ሰው ተወዳጅ ነው። ተወዳጅ ሰው ለመሆን ምሥጢርን መጠበቅ መለማመድ አለብን። ሁሉም ሰው እንዲጠበቅለት የሚፈልገው ምሥጢር አለና የነገሩንን ያሳዩንን መግለጥ አይገባም። ይልቁንም ሁለት ሁነው ያወሩትና የሠሩት ለሦስተኛ አካል አይነገርም። ይህን ዱርዬም የሚጠብቀው ጨዋነት ነው። ምሥጢር ጠባቂነትን ጠባይ ስናደርግ የምንውለው በቤተ መንግሥት ከነገሥታት ጋር፣ በቤተ ክህነት ከጳጳሳት ጋር ነው።

8- አቅልለው የሚያዩ ናቸው፦ ሰዎች በግድ የለሽነት፣ ተስፋ በመቁረጥ፣ በፍልስፍና ነገሮችን አቅልለው ሊያዩ ይችላሉ። ከሁሉ በላይ ይህችን ዓለም የሚያዝባት የእግዚአብሔር ሥልጣን እንዳለ በማመን ፣ ያልኩት ሳይሆን ያለው ይሆናል በሚል እምነት ነገሮችን አቅልለው የሚያዩ አሉ። በርግጥም ይህችን ዓለም ለመቀላቀል ብርና ወርቅ ወሳኝ ቢሆን ኖሮ ዕራቁታችንን አንወለድም ነበር። የመንገድ ስንቅ መሆን ቢችል ኖሮ ዕራቁታችንን አንቀብርም ነበር። የሰው ልጅ በልደትና በሞቱ በመጀመሪያውና በመጨረሻው ምዕራፍ ፍጹም ድህነቱን ይገልጣል። ትቶት የሚሄደውም ሀብት ሰላምን አሳጥቶ ቤተሰብን ያባላል፤ ፍቅርን ነሥቶ እናትና ልጅን ያካስሳል። ስንፍናን ዘርቶ ሥራ አስቁሞ ወራሹን ሱሰኛ ያደርጋል። የውርስ ገንዘብ የሞት አዚም ስላለው ብዙም አይበላምና የእጃችንን ሥራ መመኘት ይገባል። እግዚአብሔር የእጅህን ሥራ እንጂ ውርስህን እባርካለሁ አላለም። ያልለፉበት ገንዘብ ሕይወትን ያለፋል። እነዚያን የገፋ እኛን ያቆስላል። ታዲያ ዕራቁቱን ለተወለደ ቁምጣ መች አነሰው ይባላልና ነገሮችን አቅልሎ ማየት ይገባል። በዚህ ዓለም ላይ ሐሰት የተባለው የመጀመሪያው ዲያብሎስ ሲሆን ሁለተኛው ውበት ነው ። ውበት ሐሰት ነው። ቅቡ አንጥረኛ ጋ ሲሄድ ወርቅ እንዳልሆነ ይታወቃል። እንዲሁም በኑሮ ውስጥ ቀዩ ይጠቁራል፣ ጥቁሩ ይገረጣል። ደጋ ቢሄድ ይመጠጣል፣  ቆላ ቢወርድ ይጠቁራል። ውበት ሐሰት ነው ። ከንቱና ባዶ ነው።

አቅልለው የሚያዩ ሰዎች ከችግሩ ይልቅ ለመፍትሔ ይተጋሉ። በሰማሁት ነገር ላይ የእኔ አስተዋጽኦ ምንድነው? ይላሉ። በዓለም ላይ አዲስ ነገር እንደሌለ  የታሪክ እውቀት አላቸው፣ እግዚአብሔር ነገን እንደሚያስተካክል ጽኑ እምነትን  ገንዘብ አድርገዋል። ተራራውን በእምነት ቃል ደልድለው ሲያሳዩ የተጨነቀው እፎይ ይላል። መፍትሔ አያጡምና እነርሱ በመጡልኝ ይባላሉ። አቅልለው የሚያዩ ሰዎች ቁጭ ብሎ ከማሰብ መንቀሳቀስ ለውጥ እንደሚያመጣ ያውቃሉ። ሁሉም ነገር ትልቅ የሚሆነው ተቀምጠው ሲያዩት ነው። አቅልለው የሚያዩ ሰዎች ለክብራቸው ለስማቸው ሲጋጩ የሚኖሩ አይደሉም። ሁሉንም ነገር በልኩ ያዩታል፣ ላለው አያረግዱም፣ የሌለውን አያግዱም። ሁሉንም ነገር በመጠኑ ማየትና ከልኩ አያልፍም በሚል እምነት በመጠን ይኖራሉ። ሰላማቸውን ይጠብቃሉ። የነገር እሳትን እያቀጣጠሉ ጠብን ብሔራዊ አያደርጉም። የሚጠቅምን እንጂ የሚጎዳን ነገር ለማንም አያስተላልፉም ። ተወዳጅ ለመሆን ነገሮችን አቅልለን የምናይ መሆን አለብን።

9. ንጹሕ ናቸው:- የልብ ንጽሕና ዋና ነገር እንደሆነ ሁሉ አካላዊ ንጽሕናም ወሳኝ ነው። አብዛኛው የብሉይ ኪዳን የሥርዓት ሕግጋት ከንጽሕናና የራስንም የሌሎችንም ጤና ከመጠበቅ ጋር የተያያዘ ነው። አካላዊ ንጽሕና ለጤና፣ ለነጻነት ስሜት፣ ለክብር፣ ራሳችንን ለመቀበል፣ በሌሎችም ለመወደድ አስፈላጊ ነው። ንጽሕናውን የማይጠብቅ የእአምሮ ችግር  ውስጥ እያለፈ ነው። ንጽሕናን አለመጠበቅ የጭንቀት  ስሜትን እያባባሰ ይመጣል። በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ የሚያልፉ ሰዎችን ለመርዳት ልብሳቸውን ፣ መኝታቸውን ንጹሕ ማድረግ እጅግ ወሳኝ ነው። የንጽሕና ችግር ራሳችንን እንድንጠላው ያደርገናል። ሰዎችንም ከእኛ እያሸሸ ይመጣል። አንዳንድ ጊዜም ለትዳር መፈታት እንደ ምክንያት ይሆናል። የመጨረሻው የስንፍና ጥግ የራስን ንጽሕና መጠበቅ አለመቻል ነው።

ብዙ ጊዜ የማንገነዘበው ነገር ጤናችንን የሚጎዳው የንጽሕና ችግርና የአመጋገባችን ሁኔታ ነው። ከራስ ፀጉራችን እስከ እግር ጥፍራችን ድረስ ንጽሕናን መጠበቅ ይገባናል። ንጽሕናን ለመጠበቅ ቀጠሮ ሊኖረን አይገባም። ከመኝታ ስንነሣ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል። ይልቁንም ሰዎች እስኪናገሩን መጠበቅ የመጨረሻው ሞት ነው። እግዚአብሔር ዓይንና አፍንጫን የራሳችንን የቤታችንን ንጽሕና እንድንቆጣጠርበት የሰጠን ጸጋ ነው። ውኃ የተዘጋጀው ለንጽሕና ነው።  መቆሸሽና ራስን መጣል መንፈሳዊነት አይደለም፣ ስንፍና ነው። ሰዎች እኛን እንዲወዱን ብቻ ሳይሆን ራሳችን እንድንወደውም ንጹሕ መሆን አለብን። አካላችንን፣ ልብሳችንን፣ ቤታችንን ማጽዳት ማስተካከል ግድ ነው። ይህን መሥራት ካልቻልን ምን እንሠራለን? የገጠሩ ሰው ባይታጠብ እንኳ የተሻለ ነው፣ የከተማው ሰው ግን አኗኗሩና አመጋገቡ ስለ ተበከለ ጥንቃቄ ይፈልጋል። ሰዎች አንድ ቀን በገፋቸው ቆሻሻና ጠረን ሁልጊዜ ይገምቱናልና ጎበዝ መሆን አለብን። ዋና ዋና የሚባሉ የአካል ክፍሎቻችንን በየዕለቱ ማጽዳት ተገቢ ነው። አሊያ በቁማችን መሞትና መበከልን እንለማመደዋለን። ተወዳጅ ለመሆን ንጹሕ፣ ቀልጣፋ፣ ሥነ ሥርዓት ያለው፣ የማይዝረከረክ ፣ ሞኝነትን ያራቀ ሰው መሆን ይገባል።

10- ስጦታ የሚሰጡ ናቸው:- እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለጠው አንድ ልጁን በመስጠት ነው። የክርስትና ሃይማኖት የቆመው በጸጋ ወይም በስጦታ ላይ ነው። ለወዳጆቻችን ስጦታ መስጠትን መለማመድ አለብን። ስጦታ የፍቅር መግለጫ ነው። ያንን ስጦታ ባዩ ቁጥር እኛን ያስታውሳሉ። ስጦታ አነሰ በዛ ሳይባል የሚሰጥ ነው። ዓላማው ፍቅርን መግለጫ ነው። ለስጦታ የሚረዱ አነስተኛ ፖስት ካርዶች ዛሬ ላይ እየጠፉ ነው። በሌላው ዓለም ግን አሁንም እንደ ቀጠሉ ነው። የመስቀል፣ የሥዕል፣ የመጻሕፍት ስጦታዎች አሁን አሁን እየቀሩ ነው። ራሳቸው በእጃቸው ሥዕል ሥለው፣ ጥልፍ ተጠልፈው፣ ሹራብ ሠርተው ስጦታ የሚሰጡ ወገኖች ነበሩ። በዚህ ዘመን እነዚህን ስጦታዎች አክብሮ  የሚቀበልም እየጠፋ ነው። ብቻ ስጦታ የሚሰጡ ተወዳጅ ናቸው። በዚያ ሰው ልብ ላይ በልዩ ይቀመጣሉ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 13 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ