መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ተወዳጅነት » ተወዳጅነት (3)

የትምህርቱ ርዕስ | ተወዳጅነት (3)

ተወዳጅ ሰዎች እነማን ናቸው?

11- አመስጋኝ ናቸው:- ኑሮአቸው አነስተኛ ቢሆንም ያመሰግናሉ ። ለማመስገን ማመስገን ብቻ ምክንያት ይሆንላቸዋል። አመስጋኝ ሰዎች ተወዳጅ ናቸው። በምስጋና ውስጥ ኃይል አለ፣ ጳውሎስና ሲላስ ሲያመሰግኑ የወኅኒው ደጃፍ የተከፈተው ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለመላው እስረኛ ነው። ስናመሰግን አጠገባችን ያሉት ሰዎች በኃይል መሞላት ይጀምራሉ። የኃይል ምክንያት የሚሆነውን ሰው የማይወድ የለም፣ ዓለሙ የሚያደክም ነውና። አመስጋኝ ሰዎች እግዚአብሔርን ብቻ ሳይሆን ውለታ የዋሉላቸውን ሰዎችም ያመሰግናሉ። ብዙ ጊዜ ከምንረሳቸው ነገሮች አንዱ አለማመስገን ነው። ወላጆቹን የሚያመሰግን ጥቂት ነው። ብዙ ዓመታት ተሸክመውት ሳለ አንድ ሳምንት በቤቱ ለማስተናገድ የሚታክት ብዙ ውለታ ቢስ አለ። ሌላው ወገን ከትዳሩ ጀምሮ ሲያድግና ሲያደርግ እንደ ወደዱት ይረሳል። የማይወደደውንና ምንም ማድረግ የማይችለውን ትንሹን ማሙሽ የወደዱትን መርሳት እንዴት ይቻላል? እኩዮቻችንን አናመሰግንም፣ ለእኛ ጊዜና ፍቅር የሰጡ ናቸው። በዘወትር ትግላችን የሚያደምጡን ናቸው። ወዳጆችን ፣ ያገዙንን፣ መምህራንን ማመስገን እየረሳን ነው። ከሁሉ በላይ እግዚአብሔርን ለማመስገን ረስተናል።

ምስጋና ቢስ ሰው ከእባብ ስለታም ጥርስ በላይ የሚጎዳ ነው። ምስጋና ቢስ ልጅ ፣ ምስጋና ቢስ ወዳጅ ይጎዳሉ። ሰው የምስጋና ዕዳውን ካልመለሰ በነፍሱ የታሰረ ነው። ብዙ አስከፊ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ከምስጋና ቢሶች በላይ ግን አስከፊ የለም። ምስጋና የዘወትር ሕይወት የሆነላቸው ሰዎች ተወዳጅ ናቸው። በሰዎች ዘንድ ተወዳጅ እንድንሆን ማመስገንን፣ ባለን ነገር መደሰትን ዘይቤ ማድረግ አለብን። አማራሪ ስንሆን ሰዎች ይርቁናል። አንድ ቀን ምርር ስንል የሰሙን ሰዎች በሚገርም ሁኔታ እስከ ዛሬ ድረስ አላገኘናቸውም።

12- ታማኝ ናቸው፦ ታማኝነት ለራስ ነው፣ ታማኞች በየትኛውም ዘመን ዋጋቸው አይወርድም። ታማኞችን የሚፈልጉ ብዙ ባለጠጎችና ባለሥልጣናት አሉ። በአብዛኛው ሰው ደጅ የሚያድረው ቤት ጠፍቶ አይደለም፣ መተማመን ስለ ጠፋ ሁሉም ቤቱን ዘግቶ ነው። ብዙ ቤቶች አይጥ እየጨፈረባቸው ነው። ሰው ለማስጠጋት ግን ፍርሃት አለ። የሥራ ዕድሎችም ሙሉ በሙሉ የተዘጉ አይደሉም፣ ታማኝ ሰዎች ግን እየጠፉ ነው። ታማኝነት ቢኖር ኖሮ የኑሮ ዋጋ ይቀንስ ነበር ። ለጥበቃ፣ ለካሜራ፣ ለ ፖሊስ የሚወጣው ወጪ ስለሚቀር ሸቀጡ በርካሽ  ዋጋ ይገዛ ነበር ። በአከራይና በተከራይ መካከል መተማመን እየጠፋ ነው፣ ወደፊት ቤት በጣም ሊወደድ፣ ካለው በላይ ሊጨምር ይችላል። ሰዎች ከማከራይ በሰላም ብኖር ይሻለኛል ወደሚል ስሌት ይገባሉ። ታማኝነት በጎደለ ቍጥር ኑሮ ከባድ ይሆናል። ታማኝ ሰው በጊዜው ግዳጁን የሚወጣ፣ አክባሪዎቹን የሚያከብር፣ ወዳጅነት ለነገም ስንቅ መሆኑን የሚያስብ ነው።

ውሻ ከሰው ይልቅ ታማኝ እየሆነ ነው። በከፍታም በዝቅታም ከባለቤቱ አይለይም። በዚህ ዘመን ሰዎች የረሀባቸውን መድኃኒት፣ ወድቀው ያነሣቸውን ፣ እንጀራ የዘረጋላቸውን ደግ እየከዱ ነው። ከውሻ ባነሰ የሞራል ዝቅታ እየወረዱ ነው። ታማኝነቱን ያጎደለ ሰው ቢሄድም የሚጓዘው ወደ ተሰበረ ድልድይ ነው። የተከዳው ሰው ግን ነገን በማትረፉ ደስ ሊለው ይገባል። ዘላለም አብሮት የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው። ከዳተኛ ሰዎች አታላይ ጠባይ አላቸው፣ መጀመሪያ ላይ ለስላሳ፣ አፍቃሪ መሳይ፣ ፍጹም የሚጠጉ መስለው ስለሚቀርቡ ከዛሬው ክዳት በላይ እንዴት ትላንት ተታለልሁ ? ብለው የተከዱ ሰዎች ይበሳጫሉ። ኤልያብ መልኩ አታላይ ስለ ነበር ነቢይን አሳስቷል። እንደ ላዩ ውስጡ ያማረ አልነበረም። ከዳተኛ ሰዎች ብዙ ጊዜ ቆንጆና መለሎ ናቸው፣ የክዳታቸው ምክንያቱም ሁሉም ሰው ለጊዜያዊ ነገር ስለሚወዳቸው ነው። ሁሉም ሰው የሚወደው መጨረሻ ላይ ወዳጅ አልባ ይሆናል። ብዙ ሙያ ያለው ስለማይረጋጋ በረሀብ ይሞታል። ሁሉ የሚፈልገው በቅምሻ ያልቃል። ብቻ ተወዳጅ ለመሆን ታማኝነት ወሳኝ ነው።

13. ተጫዋች ናቸው፦ አለቃ ገብረ ሃና ተጫዋችና ደስተኛ ሰው ስለ ነበሩ በዚያም ላይ ሊቅ ስለሆኑ በሦስት ነገሥታት ቤተ መንግሥት ኖረዋል። ጨዋታ አስፈላጊ ነው፣ ሳቅም የጤና ምንጭ ነው። ሁልጊዜ መጫወት ግን ቁም ነገሩን ሊጋርድ ይችላል። በጊዜው መጫወት ግን ሳቢ ሰው ያደርጋል። ዓለም ያላስለቀሰው ሰው የለም ፣ የሚያስቀውን በርግጥ ይፈልጋል። ጨዋታ የሚለው ቃል ጨው፣ ጨዋማ፣ በጨው የተቀመመ፣ ጣዕም ያለው ንግግር ማለት ነው። እኛ የምንወዳቸው ሰዎች እነማን ናቸው? ለምን ወደድናቸው? ያንን ካወቅን ተወዳጅ ሰው እንሆናለን።

14 – በንግግር አያስቀይሙም፦ በንግግር የሰውን ክብር የማይነኩ፣ በሃይማኖት በጎሣ ልዩነት መናገርን የማይወዱ ሰዎች ተወዳጅ ናቸው። ሁለም ሰው ሃይማኖቱንና የወጣበትን ነገድ ሲነኩበት ደስ አይለውም። ለውበት የተፈጠረው ልዩነት ለመናናቅ ሲውል እግዚአብሔርም ያዝናል። ታዲያ ሳት ብለን የሰውን ሃይማኖትና ጎሣ  ስንነቅፍ ጥላቻን እናተርፋለን። ከሁሉም ቦታ ደግና ክፉ ሰው አለና እገሌ ጎሣ ደግ ነው፣ እገሌ ክፉ  ነው ማለት ልፋት ነው። ዛሬ እንዲህ ምስኪን ሆነው የምናያቸው ነገ ላይ ትልቅ ቦታ ይደርሳሉና ተስፋ የሚያስቆርጥ ንግግር እንዳንናገር መጠንቀቅ ይገባል። ዞር ብለው “ጌታዬ አንተ ነህ የምታሰድበኝ፣ ብትሰጠኝ ኖሮ የንግግር መለማመጃ አልሆንም ነበር” ብለው ያለቅሳሉ። በእኛ ንግግር ፈጣሪ እንዲወቀስ እናደርጋለንና በደሉ ከፍ ያለ ነው፣ ፍጡርን በፈጣሪ ላይ በጠላትነት ማነሣሣት ከባድ ወንጀል ነው። ደግሞም  ሐሜት ወዳጅን ያሳጣል፣ በሚቻለን አቅም ልናስወግደው ይገባል።

15 – ግልጾች ናቸው፦ ተወዳጅ ሰዎች ተገቢ የሆነ ግልጽነት አላቸው። ሲደስቱም ሆነ ሲቀየሙ በግልጽ ይናገራሉ። ከተናገሩ በኋላም ቂም አይዙም ። ግልጽ  ሰዎችን እንወዳለን፣ እኛ ግን ድብቆች መሆናችን ይገርማል ። ተወዳጅ ለመሆን እነዚህን 15 ነጥቦች ማየት ተገቢ ነው። ለመውደድና ለመወደድ ካልሆነ የምንኖርበት ሌላ ምክንያት የለም።

ተመስገን ጌታዬ ሁሉ ካንተ ነው!

ተፈጸመ

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 15 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ