የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ተፈውሳችኋል

“በመገረፉ ቍስል ተፈወሳችሁ ።” 1ጴጥ. 2፡25።

ቍስል የመገረፍ ውጤት ነው ። ግርፊያ አደጋ አይደለም ፣ የታቀደ ቅጣት ነው ። ግርፊያ አንድ ጊዜ የሚከናወን አይደለም ፣ የሚደጋገም ልምጥ በትር ነው ። ግርፊያ ጠል መሬትን እንደሚያረሰርስ ሕመም ውስጥ ዘልቆ እንዲሰማ የሚያደርግ ነው ። ግርፊያ ዓላማው መግደል አይደለም ፣ መከራን ማራዘም ነው ። ግርፊያ ሥልጣን ካላቸው አካላት የሚታዘዝ ነው ። ግርፊያ ገራፊው ሲገርፍ ፣ አስገራፊው ደግሞ “ድገም” እያለ የሚያዝዝበት ነው ። ጌታና ሎሌ የተስማሙበት ነው ። ግርፊያ ላይ አራት ወገኖች ይታያሉ፡- የመጀመሪያው የፈረደው ባለሥልጣን ፤ ሁለተኛው አስፈጻሚው ወታደር ፣ ሦስተኛው ተመልካቹ ሕዝብ ፤ አራተኛው ተገራፊው ናቸው ። የፈረደው ሹም ካባ ለብሶ ያዝዛል ፣ ገራፊው እጁን ሰብስቦ ፣ ልብሱን አስቀምጦ ይገርፋል ፣ ሕዝቡ በንጹሑ ስቃይ እንዲፈራ ይደረጋል ። ሕዝብም የሰጡትን የሹም ዳቦ ለመግመጥ ዝግጁ ነውና “አንድ ጥፋት ባይገኝበት እንዲህ አይቀጣም ነበር” እያለ ላሸነፈ ድጋፉን ይሰጣል ። ተገራፊው አካልም ዕርቃኑን በአደባባይ ቆሞ ይገረፋል ። ተገራፊው አካል ንጹሕ ከሆነ በፍርድ መዛባት ያዝናል ፣ ለምን በማይሉ ፍርድ አስፈጻሚዎች ጭካኔ ልቡ ይሰበራል ። በሕዝቡ መነዳትም ይገረማል ።

ግርፊያ ክብረ ነክ ነው ። ተገራፊው ልብሱን ይገፉታል ፣ ዕርቃኑን ይቆማል ። “ዓይን ይብላህ” ብለው ይጨክኑበታል ። በ “በለው” ድምፅ መንፈሱን ለማድቀቅ ያነሣሡበታል ፤ ግርፊያው ሲጀምር ቀዩ ገላ ይቀላል ፣ ጥቁሩ ይነጣል ። ሲቀጥል ቆዳው መሳሳት ፣ መሰንጠቅ ይጀምራል ። ከዚያ በኋላ ደም ይዘንባል ። ግርፊያ ሲቆም ቍስሉ ይፋፋማል ። ለሰዓታትና ለሳምንታት ጥዝጣዜው ያሰቃያል ።

ልብሰ መንግሥቱን ተገፍፎ ስለ ተገረፈ ንጉሥ አልሰማን ይሆናል ። ብንሰማና ብናይም በዚህች ዓለም እጅግ እናዝንባታለን ። የራሳችን መጨረሻም ያሳዝነናል ። ጨካኝ ንጉሥ ሲዋረድ ብናይ ፡-

አንተም ጨካኝ ነበርህ ጨካኝ አዘዘብህ ፣
እንደ ገና ዳቦ እሳት ነደደብህ ፤

እንል ይሆናል ። ክርስቶስ ግን ደግ ሳለ ተገረፈ ። የፈወሳቸው እጆች በጥፊ መቱት ፣ የሠራቸው ክንዶች ጅራፍ አወረዱበት ። በንጽሕናው ተቀጣ ። ሌሎችን በማዳኑ ቆሰለ ። ያ የሮማውያን አለንጋ ጫፉ ላይ ድቡልቡል ብረቶች አሉት ። የተሰባበሩ አጥንቶችም አዘርዝረዋል ። ብረቱ ሥጋውን ሲቀጠቅጥ ፣ ያዘረዘሩት ሹል አጥንቶች አካልን መቅደድ ይጀምራሉ ። ሲደጋገም ሥጋ እየተቦጨቀ ይነሣል ፣ ደም እንደ ጎርፍ ይወርዳል ። በጌታችን ላይ የሆነው ይህ ሁሉ ነው ።

አካላቸው በበሽታ ፣ ልቡናቸው በኀዘን የታመመባቸው ብዙዎች ናቸው ። እነርሱን ሊፈውስ ክርስቶስ ተገረፈ ። ወላጆች ልጆቻቸውን የሚገርፉት “እንዳይለመድህ” እያሉ ነው ፣ ጌታ ክርስቶስም “እኛን መውደድ እንዳይለመድህ” ተብሎ ተገረፈ ። እርሱ ጅራፍ የማያስቆመው ፍቅር ነበረውና መውደድን አልተውም ብሎ ተሰቀለ ። ቢጠላን ዓለም እርስዋን መስሏልና በጅራፍ ትለቅቀው ነበር ። እንቢ ብሎ በማፍቀሩ ተሰቀለ ። በመገረፉ ቍስል ተፈወስን ። ቍስል ማንንም የመፈወስ አቅም የለውም ። ወዳጃችን ቢቆስልልን የበለጠ ያመናል ። የአምላክ ልጅ በመቍሰሉ ግን ተፈውሰናል ። የብዙዎች አምላካቸው የሚያቆስል ነው ፣ የእኛ አምላክ ግን ለፍቅር የቆሰለ ነው ።

ብዙ በሽታዎች ተራብተውብናል ። የማያቃስት ሰው የለም ። የሥነ ልቡና ስብራት በዝቷል ። ሰው በሰው ተጎድቷል ። እናውቃለን በሚሉ ሰዎች በመጎዳታቸው ብዙዎች ልባቸው ቂም አርግዟል ። ሥጋንም ነፍስንም የሚፈውስ አንድ ቍስል አለ ። እርሱ የጌታችን የመገረፉ ቍስል ነው ። እናቶች ልጆቻቸው ሲታመሙ ይታመማሉ ፣ ግን ልጆቹ አይድኑም ። አንዳንድ ሰው ዓይኑ የታመመ ወገን ሲያይ አብሮ ይታመማል ፣ ጥርሱን ያመመው ሰው ሲያይ ታሞ ያድራል ። የሌላውን ስቃይ ይዘው የሚገቡ ሰዎች አሉ ። ታማሚውን ግን አያሳርፉትም ። እንደውም ሁለት በሽተኛ ይሆናሉ ። በመገረፉ ቍስል የፈወሰን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ነው ።

በኑሮ በአገልግሎት የተገረፍን ፣ የቆሰልን ነን ። በመገረፉ ቍስል ግን ተፈውሰናል ። የተገረፈ ብቻ የተገረፈን ያድናል ። ቅምጥሎች ሳይሆኑ የቆሰለው እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ መልስ ይሆነናል ። እርሱ በየዕለቱ አይገረፍልንም ፤ አንድ ጊዜ በሆነው መገረፉ ፈውሳችንን በእምነት እንቀበል ። የፈውስ ዘመን ይሁንልን !

ዕለተ ብርሃን 9

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 14 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ