“እነሆ ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ።” ሉቃ. 2 ፡ 10-11 ።
ዓለም ሰበር ዜና ብላ መርዶን እንጂ የምሥራችን ተናግራ አታውቅም ። በጌታችን መወለድ ግን የምሥራች ተሰማ ። ዜናውን ለዓለም የነገረው ቅዱስ መልአክ ነው ። መልአክ በነበረው ሰይጣን የሞት መርዶ ተሰማ ፣ በቅዱስ መልአክ የመዳን ዜና ተሰማ ። ሁሉን በእኩልነት የሚያስደስት የምሥራች የለም ። የሰው ልጆች ችግር ፣ ፈተናና ፍላጎት የተለያየ ነውና በእኩልነት የሚያስደስታቸው ነገር አይኖርም ። ከሕዝብና ከአሕዛብ የተወለደው ክርስቶስ ለሕዝብ ሁሉ የምሥራች ሆነ ። የክርስቶስ ልደት ሕዝብና አሕዛብን ፣ ባሮችንና ጌቶችን ፣ ልጆችንና አዋቂዎችን ፣ እረኞችንና ነገሥታትን ፣ ሊቃውንትንና ተማሪዎችን በእኩል ያስደሰተ ነው ። ርቀው የነበሩት የቀረቡት ፣ የተለያዩት አንድ የሆኑት በልደቱ ነው ። ማደሪያቸው መክበሩን እንዲያውቁ እረኞች ተጠሩ ፣ ነገሥታት ትሕትናን እንዲማሩ ወደ ግርግም ገቡ ። በቤተ መቅደስ ቢወለድ ኖሮ አሕዛብ እንዳይገቡ የኦሪት እግድ ነበረባቸው ። ቤተ ልሔም ግን ሁሉን የምታገናኝ ሆነች ። በረት ለመገኘትም ትሕትና እንጂ አይሁዳዊ ወይም አረሚ የሚል መስፈርት የለም ። ጎዳናው ፣ አደባባዩ የማያገናኛቸው እረኞችና ነገሥታትን በግርግም ተገናኙ ። በልደቱ ብርሃን የተከለሉ ሰው እኩል መሆኑን ያምናሉ ።
ታላቅ ደስታ የክርስቶስ መወለድ ነው ። በጦርነት ድል ሲያደርጉ ሕዝቦች ታላቅ ደስታ ይሰማቸዋል ። አገራቸው በውድድር ስታሸነፍ ሕዝቦች ደስ ይላቸዋል ። አገራቸው ነጻ ስትወጣ ሕዝቦች ደስታቸውን አደባባይ ወጥተው ይገልጻሉ ። ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ደስታ ተሰማ ። እርሱም የጌታችን መወለድ ነው ። በምድር ላይ ሆነን ታላቅ ደስታ የምንልበት መጠንና ሰማይ ታላቅ ደስታ የሚልበት መጠን በጣም የተለያየ ነው ። ሰማይ ታላቅ ሲለን ስጉ ሆነን መመርመር ይገባናል ። ለሕዝብ ሁሉ የሚሆነው ታላቅ ደስታ ከሞትና ከሲኦል መዳን ነው ። ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ደስታ ከሆነ ለምን ለመላው ዓለም አይናገረውም ( ቅዱስ መልአክ መላው ዓለም የሚሰማውን መለከት በመጨረሻው ቀን ይነፋል ። የልደቱ የምሥራች ሲተጉ ላደሩ ፣ መንጋቸውን ለሚጠብቁ ባለ አደራዎች የተሰማ ነው ። ትጋትና ባለ አደራነት የልደቱን ደስታ ያካፍላል ።
ዛሬ ተወለደ ። ዘላለማዊው አምላክ ዛሬ የሚል ጊዜ ተቀጸለለት ። ከአብ የተወለደው ልደት ዛሬ የለውም ፣ ከድንግል የተወለደው ልደት ግን ዛሬ አለው ። ዘመናችንን ሊቀድስ በዘመናችን ውስጥ ገባ ። ዛሬ ብለን የጌታን ልደት እናከብራለን ። ታሪክ ሳይሆን ሕይወታችን ነውና በኃላፊ አንቀጽ አንገልጠውም ። በሃይማኖት ውስጥ ትላንት ነገ ሳይሆን ዛሬ የሚል አሁንነት አለ ። ወደ ዘላለም ቤት የምንሄደውም ዛሬ የሚል የአሁን ኑሮን ለመኖር ነው ። እግዚአብሔር በዘላለም አሁን የሚኖር አምላክ ነው ። በዓላቶቻችን የቱሪስት መስሕብ ፣ የትርኢት ማሳያ ፣ መዝናኛ አይደሉም ። የአምልኮ ክፍል ናቸውና ከታይታ ስሜት ውጭ መሆን አለባቸው ። በውጫዊ ጌጥ ሳይሆን በውስጣዊ መለወጥ ሊከናወኑ ይገባቸዋል ።
በዳዊት ከተማ ተወለደ ። ትንቢቱን ሊፈጽም ነው ። ወላጆቻችን የተወለዱበትን ስፍራ መጎብኘት ትልቅ ደስታ ይሰጠናል ። በዚያም አንድ በጎ ነገር ማድረግ እነርሱን እንደሚያከብራቸው እናውቃለን ። ጌታችን በዳዊት ከተማ የተወለደው ዳዊትን ሊያከብረው ነው ። ዳዊት በልጆች ያዘነ ነው ። ደግ ደግ አይወልድምና ። ክርስቶስ ሊክሰው ወልደ ዳዊት /የዳዊት ልጅ ተብሎ መጣ ። የዳዊት ከተማ በወሊድ ምክንያት ራሔል የሚተችበትና የተቀበረችበት ስፍራ ነው ። ያቺ የጥንቷ ኤፍራታ ዛሬም ሄሮድስ ልጆችን ያንቅባታል ። ዛሬ መድኅን ልጅ ተወለደባት ። የዳዊት ልጅ በዳዊት ከተማ ተወለደ ። የናዝሬቱ ኢየሱስ እንደ ተባለው መጠሪያ የይሁዳ አንበሳ ፣ ወልደ ዳዊት መባልም ይገባዋል ። ይህም የእኛን ሥጋ ስለ መልበሱ የተሰጠው ስያሜ ነው ።
መድኃኒት ተወለደ ። በሽታን የሚያድኑ መድኃኒቶች በዓለም ላይ አሉ ። ሞትን የሚፈውስ መድኃኒት ግን አንድ ብቻ ነው ። እርሱም ክርስቶስ ጌታችን ነው ።
ክርስቶስ ማለት የተቀባ የከበረ ማለት ነው ። ነቢይ ፣ ካህንና ንጉሥ የተቀባ የከበረ ይባላል ። ቀዳማዊ አዳም እነዚህ ሦስት ማዕረጋት ነበሩት ። ጌታችን ሰው በሆነ ጊዜ ርስቱን አስመላሽ ነውና ነቢይ ፣ ካህንና ንጉሥ ተባለ ። በነቢይነቱ አስተማረ ፣ በካህንነቱ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ ፣ በንጉሥነቱ ኃይለ አጋንንትን ቀጠቀጠ ። ዛሬም ያጽናናል ፣ ልመናችንን ይሰማል ፣ ብርታትን ይሰጠናል ።
ጌታ ነው ። በዓለም ላይ ብዙ ጌቶች አሉ ። እርሱ ግን የጌቶች ጌታ ነው ። ከሁሉ የበላይ ነው ። እርሱንም የሚያሸንፍ ጉዳይና ቋጠሮ በዓለም ላይ የለም ። “ተወልዶላችኋል” ይላል ። በርግጥም ተወልዶልናል ። ልደቱ ልደታችን ነው ። ልደቱ እኛን በሐዲስ ተፈጥሮ ፣ ለመንግሥተ ሰማያት ፣ ለውሉደ ክህነት የወለደን ነው ።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም.