አንድ መነኩሴ አባ አጋቶንን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡- “ትእዛዝ ታዝዤ ነበር ፣ ነገር ግን በቦታው ላይ ፈተና አለ ። በትእዛዙ መሠረት ለመሄድ ፈቃደኛ ነኝ ፤ ነገር ግን ፈተናውን እፈራለሁ ።” ሽማግሌውም እንዲህ አለው፡- “አጋቶን ቢሆን ኖሮ የታዘዘውን ፈጽሞ ፈተናውንም ድል ያደርግ ነበር ።” (አጋቶን 13)
የክርስትና ታሪክ ፈተናን ፈርተው ባልጀመሩ ዓለማውያን ፣ በፈተና ደንብረው በተመለሱ ዴማስያውያን ፣ ፈተናውን ድል ነሥተው በከበሩ ቅዱሳን የተሞላ ነው ። ከሦስቱ ሁለቱ እጅ ለክብር የሚበቃ አይደለም ።መንገዱ ጠባብ ነውና ከሦስቱ አንዱ እጅ ይተርፋል ።ብዙ ሰዎች ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ለመፈጸም ፈቃደኛ አይደሉም ። ንስሐ ለመግባት ፣ ቅዱስ ቊርባን ለመቀበል ይቸገራሉ ። ለችግራቸው መፍትሔ ለማግኘት ግን ፈዋሽ ተነሣ በተባለበት አገርና ከተማ ሁሉ ይባክናሉ ። አንዳንድ ችግሮች በንስሐና በቅዱስ ቊርባን የሚፈቱ ናቸው ።እነዚህ ሰዎች ሌሎቹን ጸጋዎች የሚያከብሩትን ያህል ንስሐን ግን ማክበር አይሆንላቸውም ። እግዚአብሔርን ለሥጋ ችግር እንጂ ለነፍስ መፍትሔ አይሹትም ።ነፍስ ስትፈወስ ሁሉም ነገር እንደሚፈወስ መቀበል አይሆንላቸውም ። ንስሐ እንዲገቡ ሲነገራቸው ፈተናውን እፈራለሁ ይላሉ ። የቆሸሸ ሰው ታጠብ ሲባል እንደገና መቆሸሹን እፈራለሁ አይልም ።እነዚህ ሰዎች ግን ትልቁ ሰይጣናዊ ፈተና ለንስሐ ጠንካራ ልብ መያዝ እንደሆነ አይረዱም ። ቃየንን ተቅበዝባዥ ፣ ዔሳውን የቁጭት ሰው ያደረገ ፤ ፈርዖንን በኤርትራ ባሕር ያሰጠመ ፣ ይሁዳን ለገመድ የዳረገ ንስሐ አለመግባት መሆኑን ገና አላወቁም ።እነዚህ ሰዎች የበደላቸው ሰው ይቅርታ ሳይጠይቃቸው ገንዘብ ስጠን ቢላቸው ይደነቃሉ ። መጀመሪያ ይቅርታ በለኝ ይላሉ ።እነርሱ ግን ይቅርታን ሳያገኙ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን ይለምናሉ ። ባልታጠበ ገላ ሽቱ መቀባት ቆሻሻውን ማጉላት ነው ። ንስሐ ባልገባ ማንነትም የሚገኝ ፈውስና በረከት የበለጠ ለመጥፋት ነው ።
ዓለማዊነት የተጫናቸውና በከንቱ ጨዋታ እንደ ሕፃን የሚታለሉ ሰዎች የቤተ ክርስቲያንን አጥር የሚዞሩ እንጂ ወደ ውስጠኛው አገልግሎት የሚገቡ አይደሉም ። ከእግዚአብሔር ጋር ለመወዳጀት ሳይሆን የከፋ ጠብ ላለመጣላት ብቻ የሚያስቡ ናቸው ። እገዚአብሔርን እወዳለሁ አይሉም ፣ እግዚአብሔርን አልጠላም ግን ሊሉ ይችላሉ ። ፍቅር ማለት አለመጥላት አይደለም ። የብዙ ሰው ንግግር ተሳልሜ ልመለስ እንጂ ንስሐ ገብቼ ፣ ቆርቤ ልመለስ የሚል አይደለም ። ዛሬ ንስሐ የሚገባ ሰው ቢበረክት አገር ሰላም ይሆን ነበር ።ምክንያቱም ንስሐ ሲገባ የበደለውን ወንድሙን ክሶ ፣ የቀማውን ንብረት መልሶ ነውና ። ዓለማዊነት ዕለት ዕለት እየበዛ ነውና ይህ የሚያሳየን ሰው ምን ያህል ተስፋ መቊረጡን ነው ። ጠንከር ያለ ሕይወት አይደለም ፣ ጠንከር ያለ ቃል መስማት የማይፈልጉ ፣ ገብስ ገብሱን ብቻ እየመረጡ የቀለለ ኑሮ የሚገፉ አያሌ ናቸው ። ሰው ንስሐ ካልገባ ፣ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም ካልቀረበ ሃይማኖቱን በገዛ ኑሮው እየተቃወመ ነውና ሃይማኖቴ ማለት አይችልም ። እርሱ ያላመነበትን እንዴት ይከራከርለታል ?
ብዙ ክርስቲያኖች ወደ እግዚአብሔር መጥተው ወደ ኋላ ተመልሰዋል ። የደነበሩበትን ነገር ሲናገሩ ቄሱ እንዲህ ሲያደርግ ፣ አገልጋዩ እንዲህ ሲፈጽም አይቼ ይላሉ ። በእግዚአብሔር ቤት ከአገልጋዮች ጋር ያለን ግንኙነት ከጸጋቸው እንጂ ከግላዊ ኑሮአቸው ጋር ሊሆን አይገባም ። መጽሐፍም ሰውን ተመልከቱ አላለም ።“ስለዚህ ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” ። ዕብ. 3፡1 ። ሌሎችም ልዩ ልዩ ፈተናና መከራ ሲመጣ ፈርጥጠው ይወጣሉ ።ክርስትናን ለመደሰቻ ብቻ መምረጥ ተገቢ አይደለም ።መስቀሉን ያላየ ትንሣኤውን አያይም ።ሌሊትን ያልታገሠ ለማለዳ አይደርስም ።ክረምትን ያልቻለ በጋውን አይመለከትም ።ዴማስ አገልግሎቱን ሸኝቶ የተመለሰ ፣ በመጀመር ጎበዝ በመፈጸም ሰነፍ የሆነ ሰው ነው ። ያላለቁ መንገዶች የታላላቅ ትካዜ መገኛዎች ናቸው ።ብዙዎች የኃጢአት ወንበራቸው ላይ ሁነው በረጅሙ ተንፍሰው ሲናገሩ ይሰማሉ፡- “ክርስቲያን ነበርሁ” ፣ “አገልጋይ ነበርሁ” ይላሉ ። ነበርሁ የሚያምረው ለኃጢአት እንጂ ለጽድቅ አይደለም ።
ብዙ የጸኑ ፣ ወንጌልን ዓላማ ፣ ክርስቶስን መሪ ያደረጉ ቆራጥ አርበኞች በክርስትና ውስጥ አሉ ።የሚልሞሰሞሱትን ዓለም ስትንቅ እነዚህን ግን መድፈር አልሆነላትም ።የሚያምርባቸውን በትክክል የለዩና ያንንም ሁነው የተገለጹ አያሌ ወታደሮችን ወንጌል አብቅላለች ። እነዚህን ስናይ እንበረታለን ።በጭብጨባ ያልቀሩ ፣ በስድብም ያልተደናቀፉ ፣ በወረትም ያልተነኑ ፣ በስህተት ትምህርትም ያልተጠለፉ ፣ እረኞቻቸውን በማነቅም ያልተባበሩ አያሌ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን ወጥተዋል ።የቤተ ክርስቲያን ውለታ የከበዳቸው ፣ ዞረው የበሉበት ሰሐን ላይ ያልተፉ ፣ ያጠመቁአቸውን ያልከሰሱ አያሌ ቡሩካን ዛሬም አሉ ። ክፉዎቹ ስለሚጎሉብን እንጂ ደጋጎቹ ጨርሰው አልጠፉም ።
ፈተናን የምናሸንፈው ባለመታዘዝ ሳይሆን በመታዘዝ ነው ። የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ፈተናን ከፈራን ሰይጣንን አከበርነው ማለት ነው ፤ ከታዘዝን እግዚአብሔርን አከበርነው ። ሰይጣን ድል የሚነሣው በቃል ግሣጼ ሳይሆን በመታዘዝ ነው ።“እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” ይላል ። ያዕ. 4፡7 ። ልብ በሉ ሰይጣን ከእኛ የሚሸሸው “ይውደም” እያልን ስለፎከርን ሳይሆን ለእግዚአብሔር በመገዛት ነው ። የዛሬው ትውልድ ቅዱሳን መላእክትን ማክበር እያቃተው ሰይጣንን ግን የሚያከብር ነው ። እንዴት የጸኑትን ትተን የወደቁትን እናከብራለን ?
የታዘዝነው ቦታ ጋ ስንደርስ የፈራነው ፈተና የለም ። ፈተናንም የምናሸንፈው በመሥራት ነው ።ተማሪ ፈተናን የሚያልፈው በማጥናት ነው ።የታዘዝነውን ስናደርግ የምንፈራውን ፈተና እናጣዋለን ።መፈተን ሰው መሆን ፣ አለመታዘዝ ግን ሰይጣን መሆን ነው ።
ጸሎት
ስምህ ቅዱስ የሆነ ፣ ግርማዊነትህ ያልተደፈረ ፣ ዳርቻዎችን ሁሉ በዓይን ጥቅሻ የምትቆጣጠር ፣ ክንድህ የሚያደቅ የይሁዳ አንበሳ በእውነት አመሰግንሃለሁ ። የመጀመር ፍርሃት ፣ የመጨረስ ጽናት እያጣሁ እናጣለሁ ።ያየህልኝን ለማየት ፣ ወደፈቀድከው ለመጓዝ ዓይኔን አብራው ።ትልቁ ፈተና አለመታዘዝ መሆኑን አሳውቀኝ ።ሁልጊዜ በማላፍርበት ደግነትህ ለዘላለሙ አሜን ።
የበረሃ ጥላ 7
ረቡዕ መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ