የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትልቅ ማን ነው?

                         የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…               ረቡዕ የካቲት 26/ 2006  
  (ማቴ 11÷9-11)
ለማኙ የባለጠጋውን ቤት አልፎ የድሃዋ በር ላይ ቆሞ፡- ‹‹በእንተ ማርያም›› እያለ ይለምናል፡፡ ድሃዋም፡- ‹‹ይህን ትልቅ ቤት አልፈህ እንዴት እኔ በር ላይ ትለምናለህ?›› ይሉታል፡፡ ለማኙም፡- ‹‹አይ እሜቴ ትልቁ ቤት ትልቅ ሰው የለበትም›› አላቸው ይባላል፡፡ ድህነትን እንደ አመል በመቊጠር የባለጠጎችን ቤት ስናይ የደህና ሰው ቤት ነው እንላለን፡፡ የሰውዬውን ትልቅነት በቤቱ እንመዝነዋለን፡፡ ቤት የትልቅነት መለኪያ ሆኗል፡፡
አለቃ ገብረ ሃና እንደነገሩ ለብሰው ወደ ተጠሩበት ድግስ ይሄዳሉ፡፡ በሩ ላይ የቆመው ዘብም አላስገባም ብሎ ይመልሳቸዋል፡፡ እርሳቸውም በልብሳቸው እንደ ተመዘኑ ገብቷቸው ደህና ልብስ ለብሰው ተመልሰው ቢመጡ እጅ ነሥቶ አስገባቸው፡፡ እርሳቸውም ከእንጀራው ላይ ወጡን እያነሡ ልብሳቸውን መለቅለቅ ጀመሩ፡፡ ሰዎቹም ምነው አለቃ ምን ነካዎት? ቢሏቸው፡- ‹‹የተጠራሁት እኔ ሳልሆን ልብሴ ነው›› አሉ ይባላል፡፡ አለባበስ የትልቅነት መለኪያ ሆኗል፡፡ ከአባባሉም፡- ‹‹ኖር ለልብሱ›› ነው፡፡ እኛም ሰዎች ሲለብሱና ሳይለብሱ የማንቆጣጠረው ማንነታችን ሁለት ሰው ያደርገናል፡፡ ውሾች ሱፍ የለበሰ ላይ አይጮኹም፣ ለማኙን ደግሞ ወርረው ያጣድፉታል፡፡ ይህ ነገር ምንድነው ብዬ አንድ ወዳጄን ብጠይቀው፡- ‹‹ፍርፋሪያቸውን የሚወስድባቸው ስለሚመስላቸው ነው›› ብሎኛል፡፡ እኔስ ከእኛ ተምረው ይመስለኝ ነበር፡፡


የሚያስደስተን የሚበቃን ኑሮ ስላለን ሳይሆን ከሌሎች በመብለጣችን ነው፡፡ ትልቅነት ትልቅ መከራ እንዳለው በቃላት አይገባንም፡፡ ለትልቅነት መሥራትና ትልቅ ሥራ መሥራት ይለያያሉ፡፡ ለትልቅነት የሚሠሩ በሌሎች ላይ ይራመዳሉ፡፡ ትልቅ ሥራ የሚሠራ ግን መሥዋዕት ይሆናሉ፡፡ ብዙ ትልልቅ ሰዎች ያልበደሉ ልጆቻቸው እንኳ አገር የለሽ ሆነዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልጆችና የልጅ ልጆች ምንድነው በደላቸው? ትልቅ ኑሮ ትልቅ ጉድ እንዳለው እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል፡፡ በየመንደሩ ይዞር የነበረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየቤቱ ያለው ድብቅ ልቅሶ ይሰማው ነበር፡፡ ያለ ልቅሶ የማይኖሩ ቤቶች እንደሌሉ እርሱ ብቻ ያውቅ ነበር፡፡
ጌታ ኢየሱስ ስለ እነ እስክንድር ወይም ስለ እነ ኔሮን ታላቅነት አልተናገረም፡፡ ስለ ዮሐንስና ጴጥሮስም የትልቅነት ክርክር ዕጣ አልጣለም፡፡ ሕፃን አምጥቶ ትልቅ ይህ መሆኑን ነገራቸው (ማቴ. 18÷1-4)፡፡ ሕጻን ትንሽ መሆኑን ሁሉም ያምናሉ፡፡ የተከበሩ ሰዎች ሕጻናትን ያከብራሉ፡፡ የዛሬው ሳይሆን የወደፊቱ ማንነቱ እየታያቸው ስፍራ ይሰጡታል፡፡ ሰው እንደ አሁኑ ሆኖ አይቀርም፡፡ የሕጻን ትልቅነቱ ስህተቱን ለመቀበል አያፍርም፣ ፍቅርን ይሰጣል እንጂ ለብድር ኑሮ አይኖርም፣ መቀበል ይችላል እንጂ አይግደረደርም፣ ራሱን ዝቅ ያደርጋል፣ ለማወቅ ይጥራል፣ ያልገባውን አስመስሎ ማለፍ አይችልም፣ በደልን በቶሎ ይረሳል፣ ምን እበላለሁ? ምን እለብሳለሁ? የማይል መንፈሳዊ ነው፡፡ የትልቅነት መስፈርቱ እንደ ሕጻናት መሆን ነው፡፡
ትልቅ ለመሆን በፖለቲካ ውስጥ ብዙዎች ይሽሎኮለካሉ፡፡ ዝነኛ ለመሆን ከሰማይ ጠቀስ ፎቅና ከታወቁ ድልድዮች ብዙዎች ራሳቸውን ይጥላሉ፡፡ እስከ ዛሬ ትልቅነት ያደክም ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ይገድላል፡፡ ግን ለትልቅነት ብለው የሠሩት ትልቅ ያደርጋል? ትልቅነት እኛ እንፈልገዋለን ወይስ ይመጣል?
ዮሐንስ መጥምቅ ትልቅ ሰው እንደ ሆነ የመሰከረው ጌታችን ነው (ማቴ. 11÷9-11)፡፡ ጌታችን ዮሐንስን ትልቅ ያለው የዓለምን መመዘኛ ፍጹም በመጣል ነው፡፡ ዓለም ትልቅ ለማለት አራት ነገሮች እንደሚያስፈልጉ ታምናለች፡፡
1.        ቤት፡- ቤቱን ብቻ በማየት ይህ የትልቅ ሰው ቤት ነው እንላለን፡፡ በመላው ዓለም የተሟላ ቤት ያላቸው ትልቅ ይባላሉ፡፡ ዮሐንስ ግን ቤት ያልነበረው በበረሃ የሚኖር ሰው ነበር (ማቴ. 3÷1-2)
2.      ልብስ፡- ቀድመን የምናየው ሰውዬውን ሳይሆን ልብሱን ነው፡፡ ፕሮቶኮሉን ያልጠበቀ ሰው የማይገባባቸውና የማይሠራባቸው ስፍራዎች አሉ፡፡ ፖሊስ ቀድሞ የሚያነሣው ደህና ለብሶ የወደቀውን ነው፡፡ ዮሐንስ ግን ልብሱ የግመል ጠጉር፣ መታጠቂያውም ጠፈር ነበር (ማር. 1÷6)፡፡
3.      ምግብ፡- ሁላችንም ቆመን ብንሄድም ለየት ያለ ምግቦችን በውድ ዋጋ፣ በደረጃ የሚመገቡ ሰዎች ትልቅ ሰዎች ይባላሉ፡፡ የሕንድ ባለጠጋ ለምሳ ለንደን ይሄዳል ይባላል፡፡ የታወቁ ወጥ ቤቶች የሠሩትም ሆነ ሌላው ምግብ ክብሩ ከጉሮሮ እስኪያልፍ ነው፡፡ ዮሐንስ ግን ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ነበር (ማር. 1÷6)፡፡
4.      የንግግር ችሎታ፡- ዛሬ የዓለምን የሥልጣን በትር የጨበጡ ሰዎች በንግግር ችሎታቸው የታወቁና ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ ግን የማንንም ወዳጅነት ሳይፈልግ በደልን የሚያጋልጥ ነበር (ሉቃ. 3÷7)፡፡ ግን ትልቅ ነበር፡፡
    ታድያ ትልቅ ማን ነው?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ