የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትልቅ ተአምር

 አንድ ሰው መጥቶ ለአንድ ቅዱስ አባት ጥያቄ አቀረበለት፡- “ተአምር መሥራት እፈልጋለሁ ፣ እንዴት ላድርግ ?” 

ቅዱሱ አባት መለሰለት:-

 

“አንድን ሰው ወንጌል እንዲያነብ ካስተማርከው ዓይን አበራህ ማለት ነው ፣ 

ድሆችን እንዲረዳ ካስተማርከው ሽባውን አዳንህ ማለት ነው ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንዲችል ካደረግህ አንካሳውን ፈውሰሃል ፣ ሙት ማንሣት ከፈለግህ ደግሞ ንስሓ እንዲገባ አድርገው ያኔ የሞተ ሰውን አስነሥተሃል ማለት ነው ፤

በል ሂድና ተአምር ሥራ!”

. . .

ጸሎትን እንደ ወታደር ማሰልጠኛ ካምፕ መጠቀም የሚፈልጉ ፣ ሰባት ቀን ዘግቼ ብወጣ አጋንንትን አርበደብዳለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ። ጸሎት ግን የእግዚአብሔርን ፊት የምንፈልግበት እንጂ ከአጋንንት ጋር ነጻ ትግል የምናደርግበት አይደለም ። አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊነት በጣም ሲሰማቸውና ብርቱ ጸሎት ያቀረቡ ሲመስላቸው እነርሱ ባለፉት ሁሉ ሰው የሚወድቅ ፣ በተሳፈሩበት ሠረገላ ሁሉ አጠገባቸው ያለው የሚጮኽ ይመስላቸዋል ። ጸሎት ጸልየን ስንነሣ ሰላማዊ ጌታ ጋ ደርሰን ስለመጣን ፣ ሰዎችም የእኛ ሰላምና ዕረፍት ያገኛቸዋል ብለን ማሰብ እንጂ ፣ እነርሱ ክብራቸውን ጥለው ሲጮኹ የእኛ ቅድስና የሚገለጥ ከመሰለን ይህም በመልካሙ ነገር መበደል ነው ። ምዕራባዊ ቅኝት ያላቸው ስብከቶች ክብረ ነክ የሆኑ ፣ የሰውን ልዕልና የሚንዱ ናቸው ። በዚህ ቅኝት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰውን በጣም ትኩር ብዬ ሳየው ታሪኩ ይገለጥልኛል ፣ ሳፈጥበት መንፈሱ ይጮኻል የሚል አስተሳሰብ አላቸው ። እግዚአብሔር ሰውን እንዴት እንደሚያከብረው ለመረዳት በአርአያው መፍጠሩን ፣ ከነጻነት ጋር ማበጀቱን ፣ ለእርሱ ሲል በመስቀል ላይ መሞቱን ፣ የሚያስገድዱ ኃያላንን ሳይሆን የሚሰብኩ ሐዋርያትን መላኩን ማስታወስ ያስፈልጋል ። መንፈሰ እግዚአብሔር ባለበት ሁሉ ክብር አለ ። እግዚአብሔር መንግሥት ነው ፣ በቤተ መንግሥት ደግሞ ክብር አለ ። 

ተአምራት የማድረግ ጸጋ ከስብከት ጸጋ ይልቅ የሚፈለገው ብዙ ተከታይ ስለሚያተርፍ ነው ። ሰዎችን ለእግዚአብሔር የሚመኙ ማስተማርን ሲፈልጉ ፣ ሰዎችን ለራሳቸው ደጋፊነት የሚሹ ተአምራትን ይፈልጋሉ ። ተአምራትን የማድረግ ፍላጎት ብዙ ገንዘብ የመሰብሰብ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ፣ በሰው ቍስል የሚነግዱበት ዘዴ ነው ። ጌታችን በሽተኞችን ፈውሶ ለማንም እንዳይናገሩ እንዳዘዘ የሚናገር ወንጌል ይዘን ፣ ቪድዮ ቀራጺ አቁመን ተአምራት ለማድረግ እንሞክራለን ። ጌታችን የዳነው ሰው እንኳ ዝም እንዲል ሲናገር ፣ አሁን ግን የዳነው ዝም ብሎ ፈወስን የሚሉ ሰዎች ይለፈልፋሉ ። ከልብ ስናጤነው ለማስታወቂያ እንጂ ለሰዎች መዳን አንጨነቅም ። ዝናችንን ለማግነን የሰውን ዝና መናድ ተገቢ አይደለም ። ሐኪም በር ቆልፎ እያከመ ፣ የሥነ ልቡና ባለሙያ ምሥጢርን ጠብቆ እያማከረ መንፈሳዊ ጸጋ አለን የሚሉ ግን ቪድዮ እየቀረጹ ሰው ያስጮኻሉ ። አብዛኛውን ሰው የሚያስጮኸው የጤፍ ዋጋ አምስት ሺህ ብር መግባቱ ነው ። ሌላ ቦታ ቢጮኹ መንግሥትም ዝም አይልም ። እየተከፈላቸው የሚወድቁ ፣ መምህሬ እንዳያፍር እያሉም በየዕለቱ የመገንደስ አገልግሎት የሚያደርጉ ሰዎች አሉ ። የእግዚአብሔር ቤት መሆኑ ቀርቶ የእኛ ቤት ሲሆን ይህን ብናስብ የሚመጥነንን አስበናል ። ተአምራት ግን አጋንንትም በምትሐት ያደርጋሉና በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው ። ዋናው ሕዝብን ማስጨብጨብ ነው ብለው የሚያስቡ ፣ ነፍሳቸውን በድለው ለሥጋቸው ያደሩ በጥንቆላ ሳይቀር ትርኢት ለማሳየት ይሞክራሉ ። ለስብከት የሚደክመው ሕዝብ ለተአምራት አለሁ ይላል ። በዐውደ ምሕረቱ ተገኝቶ የማይማረው በካምቦሎጆ ተገኝቶ የአንድን ሰው ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል አየሁ ይላል ። ለቅዳሴው የማይመቸው በየሰርጡ የራሱን ተአምር አድራጊ ያስሳል ። እረኝነት የማይፈልገው እረኛ የሌላቸውን እረኞች ያከማቻል ። ለእውነተኛ አገልጋይ እጁ የሚታሰረው ለትርኢት አቅራቢዎች ግን ሠረገላ ይሸልማል ። ሁሉም ቢጤውን ይወዳል ። ሁላችንም ግን ውሸት ሞገስ በማታገኝበት የሥላሴ ዙፋን ፊት አንድ ቀን እንቆማለን ። 

ተአምራትን በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሚያከናውን ሰው የተአምራቱን ክብርና ባለቤትነት ራሱ የሚወስድ ከሆነ ፣ ተአምሩም በእርሱ ስም የሚጠራ ከሆነ አደገኛ ነገር ነው ። መንፈሳዊ ጸጋ የሚጠበቀው በመንፈሳዊ ፍሬ ነው  ። ተአምራት የቤተ ክርስቲያን አንድ አገልግሎት እንጂ ሁሉንም የሚጠቀልል አገልግሎት አይደለም ። ተአምራት የማድረግ ጸጋ አለኝ ብሎ ብቻውን ተገንጥሎ የሚወጣ ሰው ፣ እጅ ራሴ በቂ ነኝ ብላ ከሌሎች የአካል ክፍሎች ተነጥላ ለብቻ ለመኖር እንደመወሰን ነው ። እግር የሌለው እጅ ፣ ዓይን የሌለው እጅ ከአንድ የዛፍ ዝንጣፊ የሚለይ አይደለም ። በቤተ ክርስቲያን አምልኮ ፣ ምሥጢራት ፣ ጸጋ ፣ ፍሬ ፣ ኅብረት በአንድ ጊዜ የሚከናወኑ ናቸው ። ይህ ማለት ከቅዳሴ ከዝማሬ በኋላ ምሥጢራት ይፈጸማሉ ። ድሆችን በማሰብ ፣ የተጣሉትን በማስታረቅ መንፈሳዊ ፍሬ ይከናወናል ። ከክርስቲያን ወንድሞች ጋርም የኅብረት ማዕድ ይቆረሳል ። እነዚህ ነገሮች በአንድነት ፣ በአንድ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸሙ ናቸው ። አንዱ ተነጥሎ ከወጣ አደጋ አለው ። አምልኮ ብቻ ብለው ይዘው የወጡ ምሥጢራትን አቃለው ፣ የወጣትነት ጉልበት ያለበት ዝማሬ ለማቅረብ ይሞክራሉ ። ምሥጢራትን ብቻ ይዘው የወጡ ስብከትን ይጥላሉ ። በጎ አድራጎትን ብቻ ይዘው የሚወጡ የእርዳታ ተቋም ይሆናሉ ። ኅብረትን ብቻ ይዘው የሚወጡ መንፈሳዊ ዕድር ያቋቁማሉ ። ተአምራትን ብቻ ይዘው የሚወጡ የራስ ገዝ አስተዳደር ይሆናሉ ። የራስ ገዝ ናቸውና የራሳቸው ፖሊስ ፣ የራሳቸው እስር ቤት ፣ የራሳቸው የስላላ ጓድ አላቸው ።

ዓይነ ሥውሩ ዲዲሞስ፡- “ዓይንህ ባለማየቱ ኀዘን ይሰማሃል ወይ?” ብለው ቢጠይቁት፡- “ማየት የምፈልገው አንድ እግዚአብሔርን ነው ፤ የሥጋ ዓይኖቼ መጥፋት ደግሞ እርሱን ከማየት ከልክሎኝ አያውቅም” ብሏል ። ሰው ውስጣዊ ዓይኑ ካልበራ የላይኛው ቢበራ ጥቅም የለውም ። እግዚአብሔር የሚታየው በጎሉ ዓይኖች ሳይሆን በንጹሕ ልብ ነው /ማቴ. 5፡8/ ። ቤተ ክርስቲያን በጸሎትዋ፡- ሀበነ እግዚኦ አእይንተ አእምሮ ፣ ወትረ ኪያከ ይርአያ ፤

          አቤቱ የልቡና ዓይኖቻችን አብራልን ፣ 

          ዘወትር አንተን ያዩህ ዘንድ” በማለት ትጸልያለች ። ትልቅ ተአምር አለ ። በወንጌል የሰውን ልቡና ካበራን ዓይን አበራን ማለት ነው ። ወንጌል ሲሰበክ ሰው የራሱን ልክና የእግዚአብሔርን ምሕረት በቅጡ ያያል ። 

በዚህ ዓለም ላይ እጅ ለሌላቸው እጅ መሆን ፣ እግር ለሌላቸውም እግር መሆን የሚያስደስት ነገር ነው ። ደስታ ከሥጋ ፈንጠዝያ ፣ ከአእምሮ ጨዋታ ራቅ ያለ ነው ። ደስታ መንፈሳዊ ነው ። በሌሎች ጉድለት ውስጥ የእኛ ደስታ ተቀምጧል ። ድርሻቸውን ስንሰጣቸው ደስታችንን  ይለቁልናል ። ድሆችን ስለ መርዳት መስበክ ወንጌልን መስበክ ነው ። እጅ እግር የሌለው የዛሬው ክርስትና ፣ ድነናል በሚል የሚያደነቁረን ከንቱ ጩኸት ፣ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አይደለም ። ሽባ ከመተርተር በላይ ድሆችን እንዲረዱ ምእመናንን ማነሣሣት የበለጠ ተአምር ነው ። ተአምር በየዕለቱ አለ ። የሚያስገርም ክስተት በዙሪያችን ሞልቷል ። የሚጠበቅብን እጃችንን  መዘርጋት ብቻ ነው ። 

ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ በግርድፉ እንኳ ብናየው ቦታ መለወጥ ፣ በዛፎች ሥር ተቀምጦ በነጻ ንጹሕ አየር ማግኘት ፣ የተከፈተ በርን ሳያንኳኩ መግባት ፣ ማነህ ሳንባል ዘው ማለት ፣ አልቅሰን ለምነን ብንወጣ የካርድ ክፈሉ የማንባልበት ነው ። ከዚያ ሁሉ በላይ ጠለቅ ባለ ምሥጢር ስንመለከተው ለአምልኮተ እግዚአብሔር መታደም ፣ የመላእክትና የቅዱሳን የምስጋና ተባባሪ መሆን ፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፈውሰ ሥጋ ወነፍስ ማግኘት ነው ። 

አንድን ሰው ከመቃብር ከማሥነሣት በላይ ለንስሐ እንዲበቃ መርዳት ከዘላለም ሞት ማዳን ነው ። የሚበልጥ ተአምር በእጃችን እያለ የሚያንሰውን መፈለግ ተገቢ አለማወቅ ነው ። የአንድ ሰው ከመቃብር መውጣት ፈቃደ እግዚአብሔር ያስፈልገዋል ፣ የአንድ ሰው ንስሐ መግባት ግን የተገለጠ አምላካዊ ፈቃድ ነው ። የአንድ ሽባ መተርተር ሊሆንም ላይሆንም የሚችል ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት መሄድ ግን የእግዚአብሔርና የአማንያን ደስታ ያለበት ነው /መዝ. 121 ፡ 1/ ። በአገልግሎታችን ዓይን የማብራት ተአምራት አላከናወንን ይሆናል ። ሰውን ግን ከዘላለም ጨለማ በወንጌል ካተረፍን የሚበልጥ ተአምር ሆኖልናል ። ተአምር ማድረግ ልፋት የለውም ፣ እውቀት መስጠት ግን መሥዋዕትነት ይጠይቃል ። እግዚአብሔር ተአምራዊ የሆነ ኑሮን በየዕለቱ እንድንኖር አላደረገም ፣ መደበኛውን ኑሮ ከነ ትግሉ በጸጋው እንድንወጣ ግን ፈቃዱ ነው ። የቤተ ክርስቲያን ቋሚ አገልግሎት ወንጌልን መስበክ ነው ። እምነት ከመስማት እንጂ ከተአምራት አይደለም ። የምንሰማውም የእግዚአብሔርን ቃል ነው /ሮሜ. 10፡17/ ። 

ጌታ ሆይ መረሳታችን እየቆጨን ተአምር ማድረግን ስንለምንህ እባክህ አትስጠን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

መስከረም 6 ቀን 2013 ዓ.ም.

https://t.me/Nolawii

እባክዎ ይህን ቻናል ይቀላቀሉ፣  ለሌሎች ወገኖቻችንም ያስተዋውቁ

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ