የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትምክሕቴ አንተ ነህ

 “የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው ።” 1ቆሮ. 1፡30-31
በጥበቤ እንዳልመካ ጥበቤ ይዘነጋኛል ፣ በጉልበቴ እንዳልመካ ጉልበቴ ይከዳኛል ፣ በሀብቴ እንዳልመካ ሀብቴ እንደ በረዶ ይሟሟል ፣ በዝናዬ እንዳልመካ ተረኛ ዝነኛ ይነጥቀኛል ፣ በኃይሌ እንዳልመካ ኃይሌ ይዝልብኛል ፣ በሰራዊት እንዳልመካ ይበተንብኛል ፣ በውበቴ እንዳልመካ ውበቴ ይበላሽብኛል ፣ በፍቅሬ እንዳልመካ ፍቅሬ በጥላቻ ይለወጣል ፣ በአገልግሎቴ እንዳልመካ የገነባሁትን ላፈርሰው እችላለሁ ፣ በወዳጅ እንዳልመካ ከስፍራው አጣዋለሁ ፣ በትላንት እንዳልመካ አልፎ ተረት ይሆንብኛል ፣ በዛሬ እንዳልመካ ባሰብሁበት መዋል ያቅተኛል ፣ በነገ እንዳልመካ ቀን የሚያመጣውን ማወቅ ያቅተኛል ፣ በቅድስናዬ እንዳልመካ አንዱን ስደፍን አንዱ ያፈስብኛል ።
የምመካበት ያሳፈረኝን ፣ የምመካበትን የፈራሁትን ፣ የምመካበት ያጣሁትን እኔን ልጅህን ትምክሕት ልትሆነኝ ሰው የሆንህ ፣ በቀራንዮ የዋልህ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ ተመስገን ። ጽድቅ ለሌለኝ ጽድቅ ፣ ቅድስና ለሌለኝ ቅድስና ፣ ጥበብ ለሌለኝ ጥበብ የሆንከኝ አንተ ነህ ። ቤዛ ማቅረብ ለማልችል ቤዛ የሆንከኝ ፣ ከሞትም ያዳንከኝ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ ምስጋናዬ ይድረስህ ። ከሚያባርረኝ ጠላት ፣ ከሚያሳድድ ሕሊና የተማጸንሁብህ የደኅንነቴ ቀንድ አንተ ነህ ። የማትደፈር ምሽግ ሁነህ ከሁሉ የምታድነኝ አንተ ነህ ። የዘራሁት ሲመክን ፍሬን የምትሰጠኝ ፣ የሠራሁት ሲፈርስ አዲስ ገንብተህ የምታኖረኝ አንተ ነህ ።
አንተ ትምክሕቴ ነህ ። የደኅንነቴም ራስ ነህ ። ለሚያልፈው ዓለም ብቻ ሳይሆን ለማያልፈው ዓለምም እሻሃለሁ ። አንተ ካላቅኸኝ የሚያሳንሰኝ ፣ አንተ ከወደድከኝ ከንቱ የሚለኝ ማንም የለም ። ቢኖርም ሐሰተኛ ነው ። ዛሬን ያየሁብህ ትምክሕቴ ተመስገን ። በማይፈጸም ዘመን ለዘላለሙ አሜን ። የሚሰማ ሁሉ በልቡ ያክብርህ ፣ በአንደበቱ ይዘምርልህ ፣ በጉልበቱ ይስገድልህ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ