መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ትንቢትና ልደተ ክርስቶስ

የትምህርቱ ርዕስ | ትንቢትና ልደተ ክርስቶስ

“ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ።” ሉቃ. 2፡3

ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ የባለጠጋው የአብ ልጅ ከአንዲት ድሀ ድንግል ተወለደ ። ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ የዳዊት ጌታ የዳዊት ልጅ ተባለ ። ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ የቅን ፈራጁ ፍትሕን ፍለጋ በጲላጦስ ፊት ቆመ ። ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ የአርያሙ ንጉሥ በከብቶች በረት ተጣለ ። ሁሉን ማየት መልካም መሆኑን አስተማረን ። ሁልጊዜ ፋሲካ የለምና ፣ ምንም በፋሲካ ብንቀጠር ሁልጊዜ ፋሲካ እንዳይመስለን ነገረን ። መሾም እንዳለ መሻር ፣ ማግኘት እንዳለ ማጣት አለ ። መርሁ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም ቢሆንም ከፍቅር ግን ሰው ይወድቃል ። የሚያፈቅሩን አንድ ቀን ሊያዩን ይንገሸገሻሉ ። አምላክ ሰው በመሆን ዝቅታን ወረሰ ። ዝቅ ብሎ ብቻ ቢቀር ምንም ጥቅም የለውም ። በዝቅታው ከፍ ሊያደርገን ዝቅ አለ ። እርሱ ዙፋኑን ሳይነጠቅ ዝቅ አለ ፣ ዝቅታ ስፍራን ማጣት አይደለም ። ራስን ማወቅ ነው ። አምላክ ዝቅ ካላለ ሰው ከፍ ማለት አይችልም ። ሰው መሆን ለእርሱ መዋረድ ፣ ለሰው ግን ክብር ነው ። ሰው መሆንን ሰው እንኳ አልተቀበለውም ። ሰው የሚመስል እንጂ ሰው የሆነ በማጣታቸው ፈላስፎች በፀሐይ ብርሃን ሻማ ለኩሰው ፈለጉ ። ሰው የለኝም የሚል ብሶት በዘመናት ተሰማ ። በዚህ መካከል ጌታ ሰው ሆነ ።

ዘመኑ የቅኝ ግዛት ፣ ችግር የሰለጠነበት ፣ አስከፊ እልቂቶች የሚያንዣብቡበት ነበር ። ወቅቱ ክረምት ፣ አየሩ ብርድ የሆነበት ቢሆንም ክርስቶስ ተወለደ ። በአስቸጋሪ ሰዓትም ቢሆን የሰጠኸውን ተስፋ ፈጽም በማለት ሊያስተምረን ይህን አደረገ ። ሰው ጣፋጭ ነገርን ሲያጣጥም መራራ ሲመጣ ይሸሻል ። የደስታ አጋር ሲሆን የመከራ ጓድ መሆን ይሳነዋል ። ጌታ ግን የጨለማው ብርሃን ለመሆን ወደ ዓለም መጣ ።

ቦታው ቤተ ልሔም ፣ እናቱ የ15 ዓመት ብላቴና ፣ ወቅቱ ክረምት ፣ ስፍራው በረት ፣ አርአያው የሕፃን ሁኖ ትኩረት በማይስብ መልክ ተገለጠ ። በዚህም ታይታንና ውዳሴ ከንቱን ድል ነሣ ። ራሳቸውን ጨረታ ያወጡ ፣ ፎቶአቸውንና ምስላቸውን ካላሳዩ መረጋጋት የማይችሉ ወገኖች እየበዙ ነው ። ጨረታ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜም ዝቅ ይላል ። አደባባይ የሚወዱ ሰዎች ዋጋቸው እየዋዠቀ የሚሰቃዩ ናቸው ። እነዚህን ሊያድን ክርስቶስ ምድራዊ መስህብን ንቆ መጣ ። ሰብአ ሰገል ከመጡ በኋላ ትኩረት እንዳይስብ ፣ አድናቂዎች እንዳይጎርፉ ፣ ጋዜጠኞች እንዳያስተጋቡ ወደ ግብጽ ተሰደደ ። አሳዳጅ ሲበዛ ሦስት ዓመት ዘወር ቢሉ መረሳት እንዳለ አስተማረን ። ሀብት ነፍስን ማዳን ቢችል ኖሮ ሀብታም ሆኖ ይመጣ ነበር ። ዝናና ከበሬታ ነፍስን ቢያሳርፍ በቤተ መንግሥት ይወለድ ነበር ። እዩኝ እዩኝ ባይነትን እንድንጸየፍ እርሱ በአርአያ ሕፃን መጣ ።

የዓለሙ ጌታ ፣ በከበሩ መላእክት የታጠረው ንጉሥ በሁለት ሰዎች መሐል ተገኘ ። እውነተኛ ወዳጅ ሁለት ከሆነ በቂ ነው ። መስቀሉ ሥርም ሁለት ወዳጆች ብቻ ተገኙ ። እነርሱም ዮሐንስና እመቤታችን ናቸው ። በበረትም በመስቀልም ያልተለየች እናቱ ድንግል ማርያም ብቻ ነበረች ። እርስዋ መስቀሉን ተሸክማ የኖረች ሰማዕት ናት ።

በበረት ውስጥ ፣ በከብቶች ሣር ላይ ብቸኛ መስሎ የተጣለው ሕፃን ምድራዊ መስህብን አንድንጥል ከጌጥ አምልኮ እንድንወጣ ይመክረናል ። እርሱን በሐር መኝታው መለየት አንችልም ። ወደ እርሱ የሚሳቡ እውነትን ብቻ የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ።

ቃሉን የማያውቁ እነ ሄሮድስ የመረጃ ሰዎች ነበሩ ። ስለዚህ ሸንጋይና ገዳይ ሆኑ ። ሸንጋይ ሰው ገዳይ ነው ። በእጁም ደም አለበት ። ነቢዩ፡- “የደም ሰዎችና ሸንጋዮች ዘመናቸው ግማሽ አይሞላም” ይላል (መዝ. 54 ፡ 23)። ቃሉን ለእንጀራ መብያ የሚያጠኑ ፣ ባለሙያ ተብለው የሚከበሩ ጻፎችና ፈሪሳውያን ይጠቅሳሉ ግን በጥቅሱ አይነኩበትም ። ቃሉን በእውነት የሚያውቁ አረጋዊው ስምዖንና ሐና ግን ወደ ክርስቶስ ይመጣሉ (ሉቃ. 2፡25 እና 36)።

መላእክት ዝማሬአቸውን ያሰሙት በሰው መዳን ተደስተው ፣ በአምላክ ትሕትና ተገርመው ፣ ከላይ ሳይጎድል በታች ሲያዩት መደነቅ ሞልቶባቸው ነው ። አሁንም ዝማሬ ያሰሙት ሰዎች ሰው የሆነላቸውን አምላክ እንዴት እንደሚቀበሉት ለማየት ጓጉተው ነው ። ሰው ግን ዋዛ አይደለምና ብቻቸውን ዘመሩ ። በእግዚአብሔር መደሰታችን አጋር ላያገኝ ይችላልና መበርታት ይገባል ።

በበረት ሲወለድ እረኞቹ ቤታቸውን ለቀው ወጥተው ነበር ። እርሱ ስፍራ ካለቀቁለት ለመሥራት አይመቸውም ። በረታቸውን የዘመናት ርእስ አደረገላቸው ። ጊዜያዊውን ሰጥቶ ዘላለሙን መሸለም ብልህነትም ነው ። ገበሬው ሲዘምር፡-

“እንግዲህ በልጅ አልሞኝም ፣
እንግዲህ በቤት አልሞኝም ፤
ወጥቼ ስመጣ አልተከተለኝም ይላል ። በሜዳ ላይ አዋጅ ያሰሙት እረኞች በቤታቸው የሆነውን እዩ ተብለው ተጋበዙ ። በቤታችን የሆነልንን አናውቀውም ። በእኛ ጉዳይ መላእክት እየዘመሩ እኛ እናኮርፋለን ። እረኛው ጌታ እረኞችን መረጠ ።

ጌታ የተወለደው በአማኞች ምድር ነው ። ግሪካውያን በሐተታ አምላክት ተመስጠዋል ፣ ሮማውያን ቄሣሮችን በማመለክ ተጠምደዋል ። አንዱን አምላክ በሚፈልጉት መካከል አምላክ ተወለደ ። በአምልኮቱ ጌታን አለመበደል መታደል ነው ። ትንቢት ከገመድ ይልቅ ይስባል ። ንጉሡ ሕዝቡን እንዲቆጥር ፣ ድንግል ማርያም ወደ ቤተ ልሔም እንድትሄድ ትንቢቱ ሳበ ። ትንቢት ብርታት ይሰጣል 128 ኪሜ መውለጃዋ ቢቃረብም በብርታት የሄደችው ትንቢት ስለሚስብ ነው ። ሰብአ ሰገል ከሩቅ አገር የመጡት ትንቢት ስቧቸው ነው ። ዛሬን የትንቢተ ገመድ እየሳበን ነው ። ይህን አባላሽኝ ጊዜ የተወለደው ጌታ ይመልሰው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 30 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ